Airport design

የኢትዮጵያ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማዕከል የሆነውን ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያን የሚተካ ሌላ ግዙፍ አየር ማረፊያ ለመገንባት ማቀዱን አስታውቋል፡፡

ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ ፕሮጄክት እንደሚሆን የሚነገርለት ይኸው ፕሮጄክት አሁን ባለው መነሻ ግምት እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር ድረስ እንደሚፈጅ ተግመቷል፡፡ ስራው በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት እንደሚጀመር እና ሙሉ በሙሉ እስከሚጠናቀቅም አስር ዓመታት እንደሚወስድም እየተነገረ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የአዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ዕቅዱ ሀገሪቱን የአፍሪካ አቬሽን ማዕከል ለማድረግ እንደሚያስችላት እየገለፀ ይገኛል፡፡ በእርግጥም እንደታሰበው ከተጠናቀቀ ሀገሪቱ ሁለት ግዙፍ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያዎች ባለቤት ትሆናለች ማለት ነው፡፡

(የቻላቸው ታደስ ዝርዝር የድምፅ ዘገባን ከታች ያድምጡ)

አማራጭ ቦታዎችን እንዲያጠና የተመረጠው አንድ የፈረንሳይ አማካሪ ድርጅትም በዱከም፣ ሞጆ እና ጅማ በር በኩል ሦስት አካባቢዎችን መርጦ ለውሳኔ ያቀረበ መሆኑን የትራንስፖርት ሚንስትሩ በመስከረም ወር መጨረሻ አዲስ አበባ ላይ በተካሄደ አንድ ዓለም ዓቀፍ ስብሰባ ላይ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ከአዲስ አበባ ውጭ የሚገነባ በመሆኑ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ማረፉ የግድ ይሆናል፡፡
ሆኖም ግን ባለፉት ዓመታት የፌደራሉ መንግስት እና በፌደራሉ መንግስት ስር የምትተዳደረው አዲስ አበባ ከአጎራባቿ ኦሮሚያ ክልል ጋር በመሬት ባለቤትነት እና በግዛት ወሰን መስፋፋት ሳቢያ አለመግባባቶች አልፎ አልፎም ግጭቶች ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ አንፃር የግዙፉ ዓለም ዓቀፍ ኤርፖርት ዕቅድ እና ተግባራዊነቱ በኦሮሚያና በፌደራል መንግስቱ ግንኙነት ላይ ምን ዓይነት ፖለቲካዊ እንድምታ እንደሚኖረው ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡
በ1950ዎቹ አገልግሎት ላይ የዋለውን የቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚተካ የሚጠበቀው ይኸው ኤርፖርት ለመጭዎቹ መቶ ዓመታት እንዲገለግል ታስቧል፡፡ ከመንግስት ባለስልጣናትና ተቋማት የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አየር ማረፊያው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት ቢያንስ ሰባ ሚሊዮን መንገደኞችን ሊያስተናግድ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ከሲቪል አቬሽን የሚወጡ መረጃዎች ደግሞ ቁጥሩን እስከ መቶ ሃያ ሚሊዮን ያደርሱታል፡፡
ከአስር አመት በፊት የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በአመት ከአንድ ሚሊዮን ያነሱ መንገደኞችን ሲያስተናግድ የነበረ ሲሆን በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2014 ግን ቁጥሩ ወደ ሰባት ሚሊዮን ደርሶ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እንደሚሉት አዲሱ ኤርፖርት የተለያዩ አግልግሎት መስጫ ተቋማትን የያዘ አነስተኛ የኤርፖርት ከተማ፣ እና አራት የአውሮፕላን ማኮብኮቢያዎችና ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የመንገደኞች ተርሚናሎች ወይም ማስተናገጃዎች ይኖሩታል፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለው ቦሌ ዓለም ዓቀፍ ኤርፖርት ግን ለዓለም ዓቀፍ በረራዎች የሚያገለግል አንድ ሰባት በሮች ያሉት ተርሚናል ብቻ ይዟል፡፡

ተቀማጭነቱ እንግሊዝ ለንደን የሆነው ዓለም ኣቀፉ ስካይትራክስ የተሰኘው የኤርፖርቶች ደረጃ አውጪና ሸላሚ ድርጅት እኤአ በ2014 ባወጣው የዓለም ዓቀፍ ኤርፖርቶች ምዘና ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ከአስሩ ምርጥ የአፍሪካ ኤርፖርቶች ተርታ መድቦታል፡፡ ድርጅቱ እኤአ በ2012 እና በ2013 ባወጣው የአፍሪካዊያን ኤርፖርቶች ደረጃ ምደባም ከአስሩ ምርጦች ሰባተኛ ደረጃ ላይ ነበር፡፡ ከአንድ መቶ የዓለማችን ምርጥ ኤርፖርቶች ተርታ ግን መካተት አልቻለም፡፡
ከሌሎች ሀገሮች የሚነሱ ዓለም ዓቀፍ በረራዎች ሁሉ መናሃሪያቸው የአዲስ አበባው ኤርፖርት ብቻ ስለሆነ ሌሎች ኤርፖርቶቻችን ከዓለም ዓቀፉ የአቬሽን ገበያ ጋር አልተሳሰሩም፡፡ ለዚህም ችግር ዋነኛው ተጠቃሽ ምክንያት ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ያላቸው ከተሞቻችን ዕድገታቸው እጅግ ኋላ ቀር መሆኑ ነው፡፡ የጠቅላላው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ስርጭትም ሚዛናዊ አለመሆኑ ሌላኛው ዋነኛ ችግር አድርጎ መጥቀስ ይቻላል፡፡
እንደሚታወቀው የመንግስት ፖሊሲ ለሀገር በቀል የግል አየር መንገዶች አመቺ ባለመሆኑ ቢያንስ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከውስጥ ለማስተሳሰር የሚችሉ ጠንካራ ሀገር በቀል የግል አየር መንገዶችም የሉም፡፡ በመሆኑም በሀገሪቱ ኤርፖርቶች ሁሉ የሚናኘው በመንግስት ይዞታ ስር ያለው ገበያውን በብቸኝነት የተቆጣጠረው ብርቅዬው አየር መንገድ ብቻ ሆኗል፡፡
የአዲሱ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ጉዳይ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሌሎች ሀገሮች ጋር በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያውና ዓለም ዓቀፍ ህግ እሰጥ አገባ ውስጥ የሚያስገባ አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር ከአዋጭነቱ አንፃር ሲታይ መንግስት ለግንባታው የውጭ ብድር ለማግኘት ላይቸገር ይችላል፡፡ መቼም ተጨማሪ ሜጋ ፕሮጄክት በሀገር ውስጥ የገንዘብ አቅም ብቻ ሊገነባው እንደማይችል መናገር አይከብድም፡፡
መዋጥ ከሚችለው በላይ የሚጎርሰው ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ከ1997ቱ ምርጫ ወዲህ ትኩረቱን በግዙፍ ፕሮጄክቶች ላይ አድርጓል፡፡ በከተማዎች አካባቢ ሽንፈት ከደረሰበትና ህዝባዊ ምሬት ስር እየሰደደ መሆኑን ከተገነዘበ ወዲህም ድሃ ተኮር እና ገጠር-ተኮር የነበረውን ፖሊሲውን ወደ ከተማ-ተኮር ልማትና ሀገራዊ ኢኮኖሚያው ዕድገት በመቀየር ከገበሬው ጋር የነበረውን አጋርነት ገሸሽ አድርጎ ፊቱን ወደ ባለሃብቶች አዙሯል፡፡
እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ጥያቄ ግን መንግስት እስከመቼ በድፍረት እየተበደረ ይቀጥላል? የሚለው ነው፡፡ የሀገሪቱ የውጭ ዕዳ እንደሆነ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ.ኤም.ኤፍ ማስጠንቀቅ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ እንደ ድርጅቱ ከሆነ የሀገሪቱ የውጭ ዕዳ አንድ ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ሆኖም መንግስት ከእነ ወለዱ እየተከማቸ ያለው ብድር እንደማያሳስበው እየገለፀ ነው፡፡ ዕዳው ግን ሀገሪቱን ለከባድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊዳርጋት እንደሚችል የዘርፉ ሙያተኞች ማስጠንቀቅ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡