ዋዜማ- በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ መራዊ ከተማ 11 መምህራን ባለፈው ሳምንት መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም በታጣቂዎች የጅምላ ግድያ እንደተፈጸመባቸው ዋዜማ ሰምታለች።
ታጣቂዎቹ ግድያውን የፈጸሙት፣ በአካባቢው የተጠራነውን የሥራ ማቆም አድማ ተላልፋችኋል በማለት እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል።
በታጣቂዎቹ የጅምላ ግድያው የተፈጸመባቸው መምህራን፣ በመራዊ ከተማ በሚገኙት ”ኮሎኔል ታደሠ ሙሉነህ መሰነዶ ትምሕርት ቤት” እና ”በበላይ ዘለቀ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” የሚያስተምሩ መምህራን እንደነበሩ ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል።
በርካታ የቡድኑ ታጣቂዎች ሐሙስ’ለት ወደ ከተማዋ ዘልቀው በመግባት፣ መምህራኑን ከየቤታቸው አፍነው መውሰዳቸውን፣ ከዚያም ወደ ሐሙሲት ከተማ ይዘዋቸው በመሄድ በጅምላ እንደገደሏቸውና በማግስቱ ዓርብ አስከሬናቸው ለቤተሰብ እንዲመለስ ማድረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
የሟች መምህራን አስከሬን የደረሳቸው ቤተሰቦች አራት ያህሉን መምህራን በመራዊ ከተማ በምትገኘው ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው እንዲፈጸም ማድረጋቸውንና፣ ቀሪዎቹ ደሞ በየአቅራቢያቸው በሚገኙ አቢያተ ክርስቲያናት ሥርዓተ ቀብራቸው እንዲፈጸም መደረጉን ዋዜማ ተረድታለች።
ሁሉም መምህራን ቤተሰብ የመሰረቱና ልጆች ያሏቸው መሆናቸውን ያስረዱት ምንጮች፣ በመንግሥት በኩል ወደ ሥራችሁ ተመለሱ በሚልና በታጣቂዎቹ በኩል ደሞ ሥራ አቁሙ በሚል አጣብቂኝ ውስጥ እንደነበሩም ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ ድርጊቱን በፈጸሙበት ዕለት የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የክልሉ ፖሊስና ሚሊሻ እንዲሁም የአድማ ብተና አባላት በከተማዋ እንደነበሩ፣ ሆኖም በዕለቱ ወደ ከተማዋ የገቡት የታጣቂ ቡድኑ አባላት ቁጥር ከፍተኛ ስለነበር የጸጥታ አካላቱ ማፈግፈጋቸውን ዋዜማ ተረድታለች።
በዕለቱ ለተወሰኑ ሰዓታት ከተማዋ በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር እንደነበረች የተገለጸ ሲሆን፣ ከጊዜያት በኋላ በመከላከያ ሠራዊት አባላት ቁጥጥር ስር መግባቷንም ምንጮች ተናግረዋል። ባሁኑ ወቅት በከተማዋ ከፍተኛ ውጥረት መኖሩንና ከዚያ ቀን ጀምሮ የመማር ማስተማር ሥራው ሙሉ ለሙሉ መቆሙንም ምንጮቹ አስረድተዋል።
በተለይ በከተማዋ ዙሪያ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች በየዕለቱ በከፍተኛ የጦር መሳሪያ የታገዘ የተኩስ ልውውጥ እንደሚደረግ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ምንጮች አክለው ገልጸዋል። ምንጮቹ፣ ከዚህ ቀደምም በከተማዋ ባንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ስብሰባ ላይ በነበሩ መምህራን ላይ በታጣቂዎቹ በተወረወረ የእጅ ቦንብ በርካታ መምህራን አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፥ ከትላንት በስቲያ በባህርዳር ከተማ በተዘጋጀ አንድ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ክልሉ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 7 ሚሊየን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ቢያቅድም፤ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተመዘገቡት ተማሪዎች 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብቻ መሆናቸውን ተናግረው ነበር። ሰሞኑን በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እንደገና አገርሽተዋል። [ዋዜማ]
የዋዜማን ዝርዝር ዘገባዎች በዩቲዩብ ከታች ይከታተሉ-