የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳ ንፅፅር ሪፖርትን እዚህ ማንበብ ይችላሉ– CLICK
በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ልምምድ አንድም ወደተሻለ አልያም ወደባሰ ምስቅልቅል ሊወስደው ይችል ይሆናል፡፡ ምርጫው የሚካሄደው በትግራይ ክልል ደም አፋሳሽ ጦርነት እየተካሄደ፣ በቀሩት የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ብሄር ተኮር ግጭት፣ መፈናቀልና ውጥረት ያለመረጋጋት ስሜቱን አንሮት ባለበት ወቅት ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝም በምርጫው ሂደት ላይ እንዲሁም በዕለታዊ ኑሯችን ላይ ያስከተለውና እያስከተለ ያለው ጫና በዋዛ የሚታለፍ አይደለም፡፡
መሠረታቸውን በኦሮሚያ ክልል ያደረጉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ ፓርቲዎች የቅድመ-ምርጫው ሂደት ነጻና ፍትሃዊ አይደለም በማለት ከወዲሁ ከክልላዊው እና ከሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ከወዲሁ ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ የምርጫው ድባብ የጦርነትና የስብዓዊ ቀውስ ያረበቡበት ቢሆንም፣ ከሦስት ዓመት በፊት በገዥው ኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠረው ቀውስና በሕዝብ አመጽ ወደ ሥልጣን ለመጡት ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አሕመድ ቅቡልነት ወይም ቢያንስ ሕጋዊ መሠረት ያለው መንግሥት ለመሆን ምርጫው ቁልፍ ርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ የሀገሪቱን መጻዒ ዕድል በመወስን በኩልም ምርጫው መካሄዱ ጉልህ አንድምታ እንደሚኖረው ይገመታል፡፡
ዋዜማ ራዲዮ በዚህ ውጥንቅጥ የፖለቲካ ድባብ ውስጥ የሚደረገው ጠቅላላ ምርጫ የትኞቹን ቁልፍ የሕዝብ አጀንዳዎች አንስቷል? በተለይ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሽኩቻ ዋና ማጠንጠኛ የሆኑት የብሄር ፌደራላዊ አወቃቀር ጉዳይ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፣ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ እና በአዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነትና አስተዳደር ጥያቄዎች ላይ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን አቋም አላቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች በንጽጽር ተመልክታለች፡፡ ሀገሪቱ ብዙ ተግዳሮቶች ተጋርጠውባት ባለበት በዚህ ወቅት፣ ዋዜማ ሬዲዮ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የፖለቲካ ፕሮግራሞችና ርዕዮተ ዓለማዊ መስመሮች ምን እንደሆኑ በዚህ ሪፖርት በአንድ ላይ ተጨምቀው መቅረባቸው በታሪክ ተመዝግበው እንዲቀመጡ ለማድረግ ይረዳል የሚል እምነት አላት፡፡
ይህ ሪፖርት በማናቸውም መንገድ በምርጫው ሂደትም ሆነ ውጤት ላይ ፍርድ ለመስጠት ያለመ አይደለም፡፡ የሪፖርቱ ዐላማም አይደለም፡፡
ዋዜማ ራዲዮ ገለልተኛ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡ በኢሜይል አድራሻ wazemaradio@gmail.com እንገኛለን፡፡
መልካም ንባብ