(ዋዜማ ራዲዮ)- ብዙዎችን ከመጽሐፍ አንባቢነት ወደ ሐያሲነት እያሸጋገረ ያለው የበዕውቀቱ ‹‹ከአሜን ባሻገር›› ገበያው ይዞለታል፡፡ በፋር ኢስት ትሬዲንግ አታሚነት፣ በማንኩሳና በደራሲው በራሱ አሳታሚነት፣ በአይናለም መዋ አከፋፋይነት ወደ መጽሐፍ በደረቴዎች የሚደርሰው ይህ ጥራዝ ኦሪጅናሌ ዋጋው 70 ብር ቢሆንም በደረታቸው መጽሐፍ ደርድረው፣ በኪሳቸው ፓኮ ቶፓዝ ምላጭ የማያጡት የመጽሐፍ ‹‹ቀሻቢዎች›› (ገዢው ፓርቲ-‹‹ስግብግብ ነጋዴዎች››- ቢላቸው አይጠላም) ‹‹ገበያው ላይ አርተፌሺያል እጥረት በመፍጠር›› ዋጋውን ወደ 150 ብር አሸጋግረውት ከርመዋል፡፡
ይህ የበዕውቀቱ መጽሐፍ ለመጀመርያ ጊዜ አንባቢ እጅ የደረሰው ጥር 27 ረፋድ ላይ ነበር፡፡ አየር ጤና ከሚገኘው ፋር ኢስት ማተሚያ በሦስት ቫን ተጭኖ የደረሰው 20 ሺ ቅጂ መክሰስ ሰዓት እንኳ ሳይደርስ ተሸጦ አልቋል፡፡ ይህ ማለት በዕውቀቱን 6 ሰዓታት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ግማሽ ሚሊየን ብር ወደ ኪሱ ያስገባ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ደራሲ ሳያደርገው አልቀረም፡፡ ለ20ሺ ኮፒ የተከፈለ የሕትመት ወጪ 440ሺ ብር ሲሆን ከዚህ ውስጥ ዋና አከፋፋዩ 2 መቶ ሺ ብር የትርፍ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ በሹክሹክታ ተወርቷል፡፡
መጽሐፉ ከገበያ ሊጠፋ እንደሚችል ቀድመው የጠረጠሩ የመጽሐፍ ቀሻቢዎች እጃቸው የገቡ ቅጂዎችን ደብቆ በማቆየት የመጽሐፉ ፈላጊ አማራጭ ሲያጣ እያወጡ መቸብቸብ ያዙ፡፡ ‹‹ጋሼ ከሌላ ቦታ ላምጣልዎት? ዋጋው ግን ይወደድብዎታል›› በማለት ደንበኛን ካግባቡ በኋላ ‹‹መጣሁ›› ብለው ለጥቂት ደቂቃዎች ከዕይታ ከተሰውሩ በኋላ መጽሐፉን ከጀርባ መዥርጠው በመቶ ፐርሰንት ትርፍ ይሸጡታል፡፡ ይህ ሁኔታ ላለፉት 15 ቀናት በመቀጠሉ ደራሲው እጅ ሊገባ ይችል የነበረ እስከ አራት መቶ ሺ ብር የሚደርስ ገቢ አየር ላይ ቀርቷል፡፡ ገዝቶ ሊያነብ ይችል የነበረ ተደራሲ በመዋዋስ ሲያነብ፣ ቀሪውም በማኅበራዊ ሚዲያ አስተያይቶች ጉጉቱን እየቆረጠ ስንብቷል፡፡ ደራሲውና አሳታሚው ከመነሻው ስለምን በዚህ ትንሽ የሕትመት ቁጥር ወደ ገበያ ለመግባት እንደወሰኑ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል፤ በተለይ ለመጽሐፍ ሻጮች፡፡
መጽሐፉ ለድጋሚ ሕትመት ያመራው ወደ ፋርኢሰት ማተሚያ ቤት ሲሆን 30 ሺ ድጋሚ ቅጂ ታትሞ ለመውጣት ሁለት ሳምንታትን ወስዶበታል፡፡ ማክሰኞ ዕለት የካቲት 15 ቀን ረፋድ ላይ ይህ 30 ሺ ቅጂ ከማተሚያ ቤት ሲወጣ ብሔራዊ ትያትር ጀርባ የሚገኘው የአይናለም መጽሐፍ መደብር ኮንቴይነር በመጽሐፍ ነጋዴዎች ተወሮ ለፖሊስ ያስቸገረ ግርግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ የግርግሩ መነሻ ብዙ ፓኬት መጽሐፍ ቀድሞ ለመግዛት የተደረገ ሽኩቻ ሲሆን በዚህ ትርምስ አከፋፋዩ የተወሰኑ ፓኬቶችን መሰረቁን ተናግሯል፡፡ ‹‹ግርግሩ ሥርዓት እስካልያዘ ድረስ መጽሐፍ አንሸጥም›› በማለት መጽሐፉን የጫነው መኪና ተመልሶ ወደ መጋዘን እንዲሄድ ከተደረገ በኋላ የነጋዴዎች ግርግር ሲበርድ ማምሻውን ለሁሉም ፈላጊ ውስን ቅጂዎችን ለማዳረስ ተሞክሯል፡፡ 30 ሺ ቅጂ በዚህ መንገድ ተሽጦ በሦስት ቀናት ውስጥ ተጠናቋል፡፡ ይህም የደራሲውንና የአሳታሚውን የአራት ቀናት ትርፍ ለአንድ ሚሊየን ሩብ ጉዳይ እንዳደረሰው ይታመናል፡፡
አሁን ለሦስተኛ ሕትመት ረቂቁ ወደ ፋርኢስት ማተሚያ ቤት በድጋሚ የተላከ ሲሆን የኮፒውን ብዛት ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም፡፡ የደራሲው ወኪሎች የመጽሐፉ ረቂቅ ከአንድ ማተሚያ ቤት ውጭ የትም ቦታ እንዳይታተም በማስጠንቀቃቸው መጽሐፉ በአንድ ጊዜ በተለያዩ ማተሚያ ቤቶች በብዛት እንዳይታተም እንቅፋት ሆኗል፡፡ ይህ የደራሲው ውሳኔ መጽሐፉ በሐሰት ቅጂዎች እንዳይባዛ ከመስጋት የመነጨ እንደሚሆን ይገመታል፡፡
ለሕትመት ዘርፍ ቅርብ የሆኑ እንደሚገምቱት ‹‹ከአሜን ባሻገር›› በኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅጂ ታሪክ አዲስ ክብረ ወሰን መስበር ይቻለው ነበር፡፡ ተሸራርፎ መታተሙ ግን ገበያውን እንደጎዳውና ግፋ ቢል ከመቶ ሺ ቅጂ በላይ እንዳይሄድ ሳያደርገው አልቀረም፡፡ ባልተረጋገጡ አሀዞች በእስከዛሬ የመጽሐፍ ሕትመት ታሪክ ‹‹ዴርቶጋዳ›› የተሰኘ ልቦለድን ያህል ከፍ ባለ ቁጥር የታተመ መጽሐፍ የለም፡፡ ቁጥሩም ወደ 250 ሺህ ይጠጋል፡፡
አይዳ ተማም ለዋዜማ ሬዲዮ
[የአዘጋጁ ማስታወሻ– ይህ የዋዜማ ጠብታ ደግሞ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ምን አልፏል? ምን ተርፏል? ብለን በአደባባይ የዋሉትንም ሆነ በጓዳ የተሸሸጉ ጉዳዮችን ከናንት የምንጋራበት ነው። ማዋዣ ጠብታ ነገር]