ዋዜማ- በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ‘’ጋቸነ ሲርና’’ ወይም የሥርዓት ዘብ በሚል በበርካታ አካባቢዎች ነዋሪዎች “በግዳጅ” ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ እያደረገ መሆኑን ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች እንዳሉት፣ መመሪያው ከክልሉ የወረደ መሆኑና ለሥልጠናው ነዋሪዎችን “በግዳጅ” የሚመለምሉት በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
ለሥልጠናው የሚመለመሉ ሰዎች በብዛት አርሶ አደሮች፣በንግድ ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች፣በፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
ለአብነትም በዞኑ በሚገኘው ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የሚሰሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች “በግዳጅ” ሥልጠናውን መውሰዳቸውን የፋብሪካው ሰራተኞች ለዋዜማ ገልጸዋል።
ወቅቱ የእርሻና የተለያዩ የግብርና ሥራዎች የሚከወኑበት ቢሆንም ከላይ የመጣ መመርያ ስለሆነ ሥልጠናውን “የግድ መውሰድ አለባችሁ” ተብለው ከሥራቸው መስተጓጎላቸውን ነዋሪዎች ለዋዜማ ገልጸዋል።
በዞኑ አቤ ዶንጎሮ፣አባይ ጮመን፣አሙሩ፣ሀባቦ ጉዱሩ፣ጃርቴ ጃርደጋ እንዲሁም በዞኑ ዋና መቀመጫ በሆነችው ሻምቡ ከተማ ሥልጠናው በስፋት እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ጠቁመዋል።
በምሥራቅ ወለጋ ዞንም በተመሳሳይ ‘’የጋቸነ ሲርና’’ ሥልጠናን መውሰድ በዞኑ ገጠራማ ቀበሌዎች ግዴታ ነው የሚሉት ነዋሪዎች ሥልጠናውን አንወስድም ያሉ ሰዎች የተለያዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደማይችሉ አብራርተዋል።
ከነዚህም መካከል የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ከመከልከል ጀምሮ ሌሎች መንግሥታዊ አገልግሎቶችን እስከ መገለል የሚደርስ ተግባር በመንግሥት የሥራ አመራሮች እንደሚፈጸም አውስተዋል።
በተለይም በዞኑ ሳሲጋ።ሲቡ ሲሬ፣ሊሙ ሀሮ እንዲሁም ኤበንቱ ወረዳዎች ሥልጠናው በስፋት እንደሚፈጸም ገልጸዋል።
ለሥልጠናው የሚመለመሉ ሰዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው፣ሰዎች በብዛት በሚሰበሰቡባቸው ለቅሶ ቤት፣ሠርግ፣ገበያ፣የሐይማኖት ተቋማት እንዲሁም ማኅበራዊ ጉዳዮች ከሚከወኑባቸው ስፍራዎች እንደሚወስዷቸው አክለዋል።
በሌላ በኩል ስብሰባ ብሎ በመጥራት፣ መጥታችሁ ማዳበሪያ ውሰዱ በማለት አርሶ አደሮችን ከጠሩ በኋላ ሲሰበሰቡ ሥልጠናው ወደሚሰጥበት ስፍራ በግዳጅ እንደሚወስዷቸው ጠቁመዋል።
በተለይ አርሶ አደሮችን የእርሻ ሥራ እየከወኑ ባሉበት ወቅት ይዘው ወደ ሥልጠናው ስፍራ እንደሚወሰዱ ያብራራሉ።
አርሶ አደሮችም ይህን ሽሽት በተለይም ምሽት ላይ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ራሳቸውን በመሰውር ሌላ ቦታ እንደሚያድሩ ገልጸዋል።
ከሰልጣኞቹ መካከል በእድሜ የገፉ ሰዎች፣አቅመ ደካሞች፣ሴቶች የሕክምና ማስረጃ ያላቸው ሕሙማን፣ በጀርባቸው ህጻናት ያዘሉ እናቶች ጭምር በግዳጅ ሥልጠናውን እንደሚወስዱ ዋዜማ መረዳት ችላለች።
ከነዚህ ሰልጣኞች መካከል የተወሰኑትን መሳሪያ እንደሚያስታጥቋቸው ያስረዱት ነዋሪዎች፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ፈረቃ ወጥቶላቸው ሌሊት እየዞሩ ጥበቃ እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል።
በምስራቅ ሐረርጌ፣በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣በሰሜን ሸዋ እዲሁም አዲስ በተዋቀረው የሸገር ከተማ አስተዳደር በሁሉም ክፍለ ከተሞች መሰል ድርጊት እንደሚፈጸም ዋዜማ ከደረሳት መረጃ ተረድታለች።
የሥልጠናው መስረታዊ ዓላማም ሥርዓቱን እና የአካባቢያችሁን ሰላም መጠበቅ ነው፣ የሚል እንደሆነም ነዋሪዎች ለዋዜማ አስረድተዋል።
ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የኦሮሚያ ሰላምና ጸጥታ ቢሮን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ያደረገችው ጥረት ሊሳካ ባለመቻሉ ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።
የኦሮሚያ ክልል “ጋቸነ ሲርና” የተሰኘውን የጸጥታ መዋቅር ለማጽደቅ በቁጥር 245/2014 ያወጣውን አዋጅ ዋዜማ የተመለከተች ሲሆን፣አዋጁም የጸጥታ መዋቅሩን ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው፣ የኦሮሞ ሕዝብ ነቅቶ ተደራጅቶና ታጥቆ የራሱን ሰላም በራሱ ማስከበር እንዳለበት ስለታመነ እንደሆነ ይገልጻል።
በተጨማሪም “ጋቸነ ሲርና” የሕግ የበላይነትን ለማስከበር፣ከሌሎች የመንግሥት የጸጥታ መዋቅሮች ጋር በመናበብ እንደሚሰራ ተገልጿል።
“ጋቸን ሲርና” ተጠሪነቱ ለቀበሌ አሥተዳደር እንደሆነ የሚያትተው አዋጁ፣ በጸጥታ መዋቅሩ ውስጥ የሚሳተፉት አባላት ዕድሜያቸው ከ 18 እስከ 56 ያሉ እንደሆኑ ተደንግጓል።
በጸጥታ መዋቅሩ ውስጥ ያላንዳች የጾታ ልዩነት ሥልጠናው እንደሚሰጥና፣ እድሜያቸው ከላይ በተጠቀሰው ውስጥ ያሉ እንስቶችም ሥልጠናውን መውሰድ እንዳለባቸው አዋጁ ያዛል።
ለጋቸነ ሲርና የሚመለመሉ አባላት የሚከተለውን መስፈርት ማሟላት እንዳለባቸውም አዋጁ ያብራራል።
- የክልሉ ነዋሪ የሆነ(የሆነች)፣የክልሉን የሥራ ቋንቋ በአግባቡ መናገር የሚችል፣ እንዳስፈላጊነቱ ቋንቋውን ማንበብና መጻፍ የሚችል፣የማኅበረሰቡን ወግና ባሕል የሚያከብር(የምታከብር)።
2. በሌሎች የጸጥታ መዋቅር ውስጥ አገልግሎ የማያውቅ።
3. በጋቸነ ሲርና ውስጥ አባል ሆኖ ለማገልገል የማያስችል የጤና እክል የሌለበት።
4. ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ የሌለበት እንዲሁም ከየትኛውን አይነት ደባል ሱስ የጸዳ ወይም የጸዳች።
አዋጁ እንደሚለው የጋቸነ ሲርና ወታደራዊ ሥልጠና፣ በክልሉ ፖሊስ እንዲሁም በሌሎች የክልሉ የመንግሥት የጸጥታ መዋቅሮች እንደሚሰጥ ይጠቅሳል።
ከትጥቅ ጋር ተያይዞ ለተመረጡ የጋቸነ ሲርና ሰልጣኞች የክልሉ መንግሥት የሚያስታጥቃቸው ሲሆን ወይም ራሱ ሰልጣኙ የጦር መሳሪያ ካለው ሕጋዊ ፈቃድ በማውጣት መታጠቅ እንደሚችል በአዋጁ ተደንግጓል።
የጋቸነ ሲርናን የሥራ አፈጻጸምና ክንውን በበላይነት የሚከታተለው ከክልል ጀምሮ በየደረጃው ያለው የጸጥታ ምክር ቤት መዋቅር መሆኑንም አዋጁ በውስጡ አካቷል።
በዚህም መሠረት፣ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በቁጥር 245/2014 የቀረበለትን ጋቸነ ሲርና የተሰኘውን የጸጥታ መዋቅር አዋጅ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁንና ወደ ሥራ መግባቱን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። [ዋዜማ]