ዋዜማ ራዲዮ- በኤርትራ ላይ የሚከተለውን የውጭ ፖሊሲ እየከለሰ መሆኑን ደጋግሞ ሲገልጽ የከረመው ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት እንደገና ውስጣዊ የጸጥታና ፖለቲካ ቀውሱን ባለፈው ሳምንት በኤርትራ መንግስት አሳቧል፡፡ ባለፈው መጋቢት 8 የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ አሠፋ አብዩ በሰጡት መግለጫ ነበር በኤርትራ መንግስት ላይ የተለመደው ውንጀላ የቀረበው፡፡ ባለፈው ሕዳር ወር ግድም ኤርትራና ግብጽ በሱማሌዎችና ኦሮሞዎች መካከል የብሄር ተኮር ግጭትና ጅምላ ግድያ እንዲካሄ ጸረ-ሰላም ሃይሎችን ደግፈዋል በማለት ባንድ ሰነዱ ጠቅሶ ተጠያቂ ካደረጋቸው በኋላ ጣት ከመቀሰር ተቆጥቦ ነበር፡፡ እንዲያውም ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባንድ ንግግራቸው “ከእንግዲህ በውጭ ኃይሎች ማላከካችን መቆም አለበት” እስከማለት ደርሰው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሰሞኑን መንግስት እንደገና ፊቱን ወደ ኤርትራ ማዞሩ በውጭ ፖሊሲው ረገድም ሆነ የሀገር ውስጡን ቀውስ የያዘበት መንገድ ፖለቲካዊ ቀውሱን ለመፍታት የሚያግዝ አይደለም፡፡ [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]
በገጠመው ከባድ ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ ከውዥንብር ያወጣው ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት በአቋሙ ሊረጋ አልቻለም፡፡ ከወራት በፈት “የሀገሪቱን ሕዝባዊ ተቃውሞና ቀውስ በውጭ ሃይሎች ማሳበብ ትቼ ወደ ውስጥ መመልከት ጀምሬያለሁ” ካለ በኋላ ሰሞኑን ደሞ አቋሙን እንደገና ቀይሮ ማባሪያ ለሌለው ፖለቲካዊ ቀውስ፣ ተቃውሞና ብሄር-ተኮር ግጭት ኤርትራን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ የኤርትራ ስም የተነሳው እንደ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር ያሉ ጸረ-ሰላምና አሸባሪ ቡድኖችን አሰልጥና እና አስታጥቃ አስርጋብኛለች በሚል ውንጀላ ነው፡፡
የአቋም ለውጡ መንግስት ስለ ሕዝባዊ ተቃውሞው ሀገር በቀል ባህሪ እና በኤርትራ ላይ በሚከተለው ፖሊሲ ገና ከውልውል አለመውጣቱን ነው ያረጋገጠው፡፡ በተለይ ሀገሪቱ በመከላከያ ሠራዊቱ የበላይነት በሚመራ ማዕከላዊ ዕዝ (command post) እየተመራች ሳለ በኤርትራ ላይ ውንጀላውን ያቀረቡት የፌደራል ፖሊስ አዛዡ አሠፈ አብዩ መሆናቸው ምናልባትም በሕወሃት ብሎም በኢሕአዴግ ውስጥ ኤርትራን ተጠያቂ የማድረጉ አካሄድ ሙሉ ስምምነት የሌለበት መሆኑን ሊጠቁመን ይችላል፡፡ የኤርትራው መንግስት ቃል አቀባይ የማነ ገብረ መስቀልም ለብሉምበርግ ድረ ገጽ ሲናገሩ የተለመደው ውስጣዊ ውስብስብ የጸጥታ ችግሮችን ማስቀየሻ ዘዴያቸው ነው በማለት ነበር ፈጥነው ውንጀላውን ያጣጣሉት፡፡ የአቋም ለውጡን በተቃርኖ የተሞላ ያደረገው ደሞ አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የሀገሪቱ ሰላም በከፍተኛ ደረጃ መሻሻሉን ማዕከላዊ ዕዙ (Command Post) እየገለጸ ባለበት ወቅት መሰማቱ ነው፡፡
በውጪ ሀይሎች ማሳበቡ ይበቃል
ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ባንድ ወቅት “ኢሕአዴግ የሀገሪቱን ውስጣዊ ቀውስ በውጭ ሃይሎች እያሳበቡ መቀጠል እንደማያዋጣ ተረድቷል” በማለት ገዥው ድርጅት ወደ ራሱ መመልከት መጀመሩን ተናግረው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚህ ሳቢያ መንግስታቸው በኤርትራ ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ ጭምር ከመሰረቱ ሊቀይረው መሆኑ መዘገብ ጀምሮ ነበር፡፡ መግለጫው በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት መታጀቡ ደሞ የቋም ለውጡ አንጻራዊ አመኔታ እንዲያገኝ አስችሎት ነበር ማለት ይቻላል፡፡
መንግሥት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሲያውጅ ፍትሃዊ የሆኑትን የሕዝብ ጥያቄዎች ጥቂት የሀገር ውስጥ ጸረ-ሰላም ሃይሎች ቀልብሰው የሀገሪቱን ሰላም በማደፍረሳቸውና ማንነትን ማዕከል ያደረጉ ግጭቶችና መፈናቀሎች በመበራከታቸው መሆኑን ጠቅሶ አዋጁን ካወጀ ከአንድ ወር በኋላ ነው እንደ አዲስ በኤርትራ ላይ ጣቱን የቀሰረው፡፡
ለውንጀላው እንደ ማስረጃ የቀረበው በደቡባዊ የሀገሪቱ ድንበር ሕገ ወጥ ጦር መሳሪያዎች በብዛት ሲገቡ መያዙን ነው፡፡ መቼም የጦር መሳሪያ ዝውውር በየደረጃው ያሉ ጸጥታ ሃይሎችና የመንግስት አካላት ተሳታፊ ሳይኑበት ሊካሄድም ሆነ ከእይታቸው ሊሰወር አይችልም፡፡ ሆኖም በኤርትራ ላይ የሚቀርበውን ውንጀላ አሳማኝ ለማድረግ በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች ወይም የመንግስት ሃላፊዎች መካከል አስረጅ ሆኖ የቀረበ የለም፡፡
በሌላ በኩል የቦረና ኦሮሞ አርብቶ አደሮች በብዛት በሚኖሩበት በዚህ አካባቢ ደሞ የጸጥታ ቀጥጥሩ አስቸጋሪ መሆኑና የሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩም ከፍተኛ ስለመሆኑ የክፍለ አህጉሩ ድርጅት ኢጋድ ጭምር ብዙ ሲያጠናውና ቀጠና-ዐቀፍ ፖሊሲ ሲቀርጽለት የኖረ ጉዳይ እንጅ አዲስ ክስተት አለመሆኑም መረሳት የለበትም፡፡ መንግስት በደፈናው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ በኋላ የሕገ ወጥ ጦር መሳሪ ዝውውር ጨምሯል ይበል እንጅ የጦር መሳሪያው መነሻ፣ የመሳሪያው አቀባባይ ወገኖች ማንነት፣ ሰንሰለቱ እና ለምን አላማ እንደታሰበ አብራርቶ መናገር አልቻለም፡፡ እንዲህ ያሉ የደፋፈኑ መግለጫዎች ናቸው እንግዲህ ውንጀላው ከጸጥታና ከሀገር ሉዓላዊነት ይልቅ ፖለቲካዊ ግብ ያው ያላቸው መሆኑን የሚያጋልጡበት፡፡
እዚህ ላይ “መንግስት ለምን አሁን ኤርትራን ተጠያቂ ማድረግ ፈለገ?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ለዚህ ሁለት ለእውነታው የቀረቡ መላ ምቶችን መጥቀስ ይቻል ይሆናል፡፡ ባንድ በኩል የአሜሪካ መንግሥትን ጨምሮ ምዕራባዊያኑ መንግሥታት አዋጁን ስለተቃወሙት እንዲሁም በቶሎ እንዲነሳ መንግሥትን በመጎትጎት ጥረታቸው ስለገፉበት በሀገሪቱ ብሄራዊ ደኅነነትና ሉዓላዊነት ላይ አደጋ እንደተደነቀረ ለማሳየት አስቦ ሊሆን እንደሚችል መናገር አያዳግትም፡፡
ኦነግ የማያረጅ የመጫወቻ ካርድ
በሌላ በኩል ደሞ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ዜጎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከዕቁብ ሳይቆጥሩ በአድማው ስለገፉበትና የትራንስፖርትና ንግድ አገልግሎቶችም በከፊል ስለተስተጓጎሉበትና መከላከያ ሠራዊቱ ለጸጥታ ጥበቃ መሰማራቱን ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሽፋን ለመስጠት ጭምር እንዲጠቅመው በማሰብ ጭምር ሊሆን ይችላል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ያላባራው ተቃውሞ ከኦነግ መረብ ጋር የተቆራኝ መሆኑን በመስበክ ሕገ መንግስታዊውንና ሰላማዊውን የተቃውሞ መዋቅር ማፈራረስ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኦነግ ታጣቂዎች በኬንያ በኩል ሰርገው መግባታቸውን ተደጋግሞ መጠቀሱ ለዚሁ አካሄዱ በቂ ማስረጃ ይሆናል፡፡ ኦነግ ነፍጥ ያነሳ ድርጅት መሆኑ ብቻ ሳይሆን የመገንጠል አላማን የሚራምድ መሆኑ ሙግቱን አሳማኝ ለማድረግ ሊጠቀምበት የፈለገ ይመስላል፡፡
ለመሆኑ ለአሁኑ ኢሕአዴግ የትኛው አማራጭ ይሻለው ይሆን? የሚል ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል እንደሚፈልግ አሳይቷል፡፡ በሲቪል ማኅበራትና ግለሰቦች አማካኝነት በቅርቡ ሃሳቦች ሲቀርቡ አይተናል፡፡ የአሁኑ አካሄዱ ግን እየከለስኩት ነው ያለውን ፖሊሲውን ላይ በረዶ የሚቸልስ ነው፡፡ ለሰላምና እርቅም እጁን እንደገና ለመዘርጋትም ይቸግረዋል፡፡
ባጠቃላይ ላለፉት ሁለት ዐመታት መንግስት የሀገራዊ ቀውሱን ውስጣዊ ምክንያቶች እየሸፋፈነ ጣቱን በኤርትራ እና ግብጽ ላይ መቀሰሩ ውሃ የሚቋጥር አልሆነለትም፡፡ በሌላ መንግስት የተቀነባበረ መሆኑን የሚሳያይ በቂና አሳማኝ ማስረጃም አቅርቦ አያውቅም፡፡ ግጭት አጥኝ ድርጅቶችም ሆኑ ሌሎች አካላት ውንጀላውን እንደ ተራ ፖለቲካዊ ፕሮፓጋንዳ ስለሚወስዱት ዋጋ ሰጥተውት አያውቁም፡፡ በዐለም ዐቀፍ መገናኝ ብዙሃንም ክብደት የማይሰጡት ዜና ከመሆን አልፎ አያውቅም፡፡ በጥቅሉ ውንጀላው ያስገኘለት ትርጉም ያለው ፋይዳ ስለመኖሩም መናገር ያስቸግራል፡፡
ቶሎ ቶሎ ተለዋዋጭ ከሆነው የአፍሪካ ቀንድና ቀይ ባህር አካባቢ ጅኦፖለቲካ አንጻር ሲታይም በኤርትራ ላይ ያለ በቂ ማስረጃ ነባሩን ፖሊሲ ይዞ መንገታገቱ ተጎጅ እንደሚያደርገው ጥርጥር የለውም፡፡ የኤርትራ መንግስት ከግብጽና የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ ጋር ለሚያደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ስጋት ስለሚገባው እየተከታተለ ምላሽ ሲሰጥ መኖሩ የሚያሳየውም ይህንኑ ስጋቱን ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት የሚከተለው የአጭር ጊዜና በደንብ ያልተጠና ፖለቲካዊ ግብ ሌላ መዘዝ ጎትቶ የሚያመጣ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ባንድ በኩል መግለጫው ኤርትራ ውስጥ የመሸገው ኦነግ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከኦሮሚያው አመጽ ጀርባ እንዳለበት መንግስት በይፋ እንዳመነ ያስቆጥርበታል፡፡ ይህ ደሞ በመሬት ላይ ትጥቅ ትግል ለማድረግ አቅም ያለው ስለመሆኑ ለዐመታት በተግባር ማስመስከር ላልቻለው ተገንጣዩ ኦነግ ገጽታውን የሚገነባ፣ ከሰማይ የወረደ መና ነው የሚሆንለት፡፡
ከወራት በፊት ኦነግ “የኦሮሚያውን አመጽ የምመራው እኔ ነኝ” የሚል መግለጫ ሲያወጣ ከብሄሩ መብት ተሟጋቾችና ከሀገር ውስጡ ተቃዋዎች ዘንድ እምብዛም ዋጋ አልተሰጠውም ነበር፡፡ የሰሞኑ የመንግስት የመግለጫ ጋጋታ ግን የኦነግ ተሰሚነት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ እንዲጨምር ሊያደርግ የሚችል ነው፡፡
መቼም የፌደራሉ ጸጥታ ሃይል በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ እየወሰደ ያለው ማባሪያ ያጣው የሃይል ርምጃና ግድያ ሰላማዊውን ሕዝብ አሁን እንደገና እየተነቃቃ ወደሚመስለው ኦነግ ወይም ወደ ኦነግ አስተሳሰብ ሊገፋው እንደሚችል ያጣዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በተለይ ኦሕዴድ ለሕዝቡ ቃል የገባቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች እንዳይፈጽም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና በገዥው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ ታፍኖ መያዙ ደሞ ሕዝቡን ተስፋ እንደሚያስቆርጠውና አማራጭ እንደሚያሳጣው አንድና ሁለት የለውም፡፡
እንግዲህ በቅርቡ እንደሚመረጥ የሚጠበቀው ጠቅላይ ሚንስትርም ለሀገራዊ ቀውሱ ፍተ ካርታ ሳይቀመጥለት በውጭ ሀገራት የተሳበበ ቀውስ ተረክቦ ለመቀጠል ይገደዳል ማለት ነው፡፡ ችግሮቹን ወደ ውስጥ ማየት ጀምሮ የነበረው መንግስት እንደገና በውጭ ሀገር መንግስት ማሳበብ በጀመረበት ሁኔታ ለሀገሪቱ ውስብስብ ቀውሶች እንደምን ዘላቂ ምላሽ መስጠት እንደሚችል ግራ የሚያጋባ ሆኖ ቀጥሏል፡፡[ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ ]
https://youtu.be/wcZ2eQ8FVj4