- ኢትዮጵያበ2015 ዓ.ም 30 ሚሊየን ኩንታል ወደ ውጪ የመላክ የማድረግ እቅድ የነበራት ቢሆንም በአመት ከ20 ሚሊየን ኩንታል በላይ ወደ ሀገር እየገባ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ
ዋዜማ- ከውጭ የሚገባ ስንዴ ተጨማሪ እሴት ታክስ መከፈል አለበት በሚል በጅቡቲ ወደብ ላይ ተይዘው የነበሩ ስንዴ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ያለምንም ተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ እንዲገቡ የገንዘብ ሚኒስትር ጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ለጉምሩክ ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ ተገልጿል።
በሀገሪቱ የስንዴ ምርቶችን ማምረት የሚችሉ በቂ ፋብሪካዎች በመኖራቸው መመረት የሚችልን ያለቀለት የስንዴ ዱቄት ምርት ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገባበት ወቅት ተጨማሪ እሴት ታክስ መከፈል አለበት በሚል ጅቡቲ የደረሱ ተሽከርካሪዎች ተይዘው ቆይተው ነበር።
በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ዱቄትና የዱቄት ውጤቶች አምራቾች ማህበር ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ስንዴ የተጨማሪ እሴት ታክስ አከፋፈል በተመለከተ በስንዴ ግብይት ላይ አሉታዊ ተጽህኖ የተፈጠረ መሆኑን ገልፆ ለችግሩ መፍትሄ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ የነበረ መሆኑን የማህበሩ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ስንዴ ተጨማሪ እሴት ታክስ ጉዳይን በተመለከተ ለጉምሩክ ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ መሰረት ማህበሩ ለጠየቀው ጥያቄ ምላሽ መስጠቱን ዋዜማ የተመለከተው በሚኒስትሩ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ተፈርሞ የወጣው ደብደቤ ይገልጻል።
እንደ ደብዳቤው ገላጻ ከሆነ ማህበሩ “ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ስንዴ የተጨማሪ እሴት ታክስ ይከፈልበታል በሚል ስንዴ ከጅቡቲ ጭነው የመጡ በርካታ ተሽከርካሪዎች በተለያዩ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ቆመው የሚገኙና በዚህ ምክንያት በስንዴ ግብይት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፈጠሩን” በመግለጽ ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጠው መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ለሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጠይቋል።
ለጥያቄው ምላሽ የሰጠው ሚኒስቴር መስሪያቤቱም” “በፍትህ ሚኒስቴር የተመዘገበው ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የሆኑ ዕቃዎችን ለመወሰን የወጣው መመሪያ መሰረት ስንዴን ጨምሮ እህል እና ጥራጥሬ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ መሆናቸው እንደሚቀጥል የሚገልጽ በመሆኑ ስንዴ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ሲገባም ሆነ በአገር ውስጥ ሲሸጥ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ መሆኑ እንዲታወቅ እና በእንጥልጥል ላይ ያሉ ጉዳዮች በዚሁ መሠረት እልባት እንዲሰጥ” በማለት ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ማሳሰቢያን ተመርኩዞ የጉምሩክ ኮሚሽን በስሩ ላሉት ስምነት የስራ ክፍሎች እንዲሁም የጅቡቲ እና ታጁራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶችን ጨምሮ ለ18 የክልልና የፌደራል ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በላከው አቅጣጫ መሰረት የስንዴ ዱቄት ያለተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲገቡ መፈቀዱን በደብዳቤው ተገልጿል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ፈጣን ምላች ያስደሰታቸው የማህበሩ ምንጮቹ እንደሚሉት ከሆነ መንግስት 15 በመቶ እሴት ታክስ ልጨምር ቢል በአሁኑ ወቅት አንድ ኩንታል ስንዴ እየተሸጠ ያለበትን 5100 ብር እስከ 6ሺ ብር ሊደርስ ስለሚችል በዚህም ምክንያት ደግሜ አንድ ዳቦ በትንሹ 15 ብር ከመግባቱ በፊት ታክስ ክፍያው እንዲቀነስ የተጠየቀ ነው” ብለዋል
ኢትዮጵያ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ስንዴ ማስገባት ከጀመረችበት ሁለት አመታት ውስጥ በአመት ቢያንስ 20 ሚሊየን እስከ 30 ሚሊየን ኩንታል ከውጭ እንደምታስገባ እና ለዚህ የስንዴ ግዢም በየዓመቱ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደምታደርግ መረጃዎች ያሳያሉ።
በተጨማሪም በ2015 ዓ.ም ከአሜሪካ፣ ከዪክሬን እና ከሮማኒያ 30 ሚሊየን ኩንታል የሚደርስ ስንዴ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን የኢጂ ፍሎው መረጃ ያሳያል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት 70 በመቶ ያህል የአገር ውስጥ ፍላጎቷን የምታመርት ሲሆን፣ 30 በመቶ ያህሉን ደግሞ ከውጭ ታስገባ ነበር።
ኢትዮጵያ በ2015 ያላትን የስንዴ ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት ለሟሟላት እና ከባሕር ማዶ የምታስገባውን ለማስቀረት አቅዳ እየሰራች መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
ይህንንም ለማሳካት በመላ አገሪቱ ለሦስት ዓመታት 1.3 ሚሊዮን አርሶ አደሮች በ30 ሺህ ክላስተር ተደራጅተው እንደነበር እና የ2015 ዓ.ም የመንግሥት መረጃ እንደሚያሳየው የአገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር ከ30 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ወደ ውጭ የመላክ አቅም ላይ መደረሱ ሲገለጽ ነበር።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር ግንቦት 2022 የቡድን ሰባት አገራት ሚኒስትሮች በጀርመን ባካሄዱት ስብሰባ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት፣ አክንዊሚ አዲሲና ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ስንዴ ከውጪ እንደማታስገባ መናገራቸውም የሚታወስ ነው። [ዋዜማ]