ዋዜማ ራዲዮ- በሰሜኑ ጦርነት ከደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ ባሻገር በኢኮኖሚውና በመሰረተ ልማት ተቋማት ላይ ያሰከተለው ውድመት እጅግ ከፍተኛ ነው። 

ከነዚህ ጉዳቶች ለማገገምና ወደነበሩበት ለመመለስ በርካታ ዓመታትን ይፈጃል። ዋዜማ ራዲዮ በተመረጡ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶችና የህዝብ አገልግሎት ላይ የደረሱ ጉዳቶችን እና መስተጓጎሎችን ለመመልከት ሞክራለች። አንብቡት

መንገድ

በጦርነቱ ሳቢያ የፌደራል መንገዶች ባለሥልጣን ሊሰራቸው አቅዶ ያስቀመጣቸው እና 64 ጅምር ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንደተቋረጡበት እና የፕሮጀክቶች አጠቃላይ ወጪ ከ150 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ዋዜማ ከባለሥልጣኑ ሰምታለች፡፡ 

ከ64ቱ ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱት አምስት ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፣ እነሱም ከላሊበላ-ሰቆጣ፣ ኮምቦልቻ ዋና መስመር፣ ጋሸና፣ ገላንታ መንገድ እንዲሁም ከደጎሎ-ዓለም ከተማ ያሉ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ከደጎሎ-ዓለም ከተማ የሚወስደው መንገድ በአካባቢው ከሌሎቹ የተሻለ አንጻራዊ መረጋጋት ስለታየበት በከፊል ወደ ሥራ የተገባበት ሲሆን፣ ከግጭቱ በኋላ መልካም ጅማሮ የታየበት ፕሮጀክት እንደሆነ ከባለሥልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ 

ባለሥልጣኑ ሰላም እና መረጋጋት ባገኙ አካባቢዎች በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንዳይገባ እንቅፋት ከሆኑበት ጉዳዮችች መካከል በዋናነት፣ ግጭቱን ተከትሎ ብዙ ንብረቶች መውደማቸው እና መንገዶችን ለመስራት ዓለማቀፍ ጨረታዎችን አሸንፈው ወደ ሥራ የገቡ የውጭ ተቋራጭ ኩባንያዎች ያነሷቸው የካሳ ክፍያ ጉዳዮች እንደሆኑ ለዋዜማ ተናግሯል፡፡

ግጭቱን ተከትሎ የወደሙ ንብረቶችን እና የአሠራር ሂደት  የሥራ ደንቦችን እንዲሁም አጠቃላይ በጦርነቱ ምክንያት ለደረሱት ጉዳቶች ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ሕጋዊ ጉዳዮችን የሚያይ እና የንብረት ውድመቱን መጠን የሚያጠና ከራሱ ከባለሥልጣኑ የተውጣጣ የጥናት ቡድን ተቋቁሞ ሥራውን እንደጀመረ እና በአማካሪ መኻንዲስ እየታየ እንደሆነ ዋዜማ ካገኘችው መረጃ ተረድታለች።

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት

 ጦርነቱ ካስተጓጎላቸው የትላልቅ ፕሮጀክቶች ባለቤቶች አንዱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ነው። ተቋሙ በመሠረተ ልማቶቹ ላይ ከባድ ውድመት እና ዝርፊያ እንደተፈጸመበት ይናገራል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮምንኬሽን ክፍል ኃላፊ መላኩ ታዬ፣ “በተቋሙ ላይ የደረሰው አንዳንድ ጥቃት በሙያተኞች የተደገፈ ነው። በተለይ ዝርፊያዎቹ የተካሄዱት በትክክል ሙያውን በሚያውቁ ሰዎች አማካኝነት ነው” በማለት ለዋዜማ ተናግረዋል። 

መላኩ ጨምረውም፣ “በተለይ ትላልቅ የኃይል ማስተላለፊያ ትራንስፎርመሮች የሚሰሩት እና የማይሰሩት እየተለዩ ነው ተነቅለው የተወሰዱት። እናም እንደ ተቋም እኛም የጦርነቱ ሰለባ ሆነናል” ሲሉ ተቋሙ የደረሰበትን ውድመት ሊያጠና የተላከው ቡድን ያመጣውን ሪፖርት በመጥቀስ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአፋር እና አማራ ክልሎች ብቻ ባካሄደው ጥናት፣ ከ1.1 ቢሊዮን ብር  በላይ የሚገመት የመሠረተ ልማት ውድመት ሲደርስበት፣ በአፋር ክልል ደሞ ስድስት የአገልግሎት መስጫ ቢሮዎች ሙሉ ለሙሉ ወድመውበታል። በአማራ ክልል በአምስት ዞኖች ስር በሚገኙ 30 አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ላይ ውድመት የደረሰ ሲሆን፣ ከእነዚህ ዞኖች ግዙፎቹ ሁለቱ ዞኖች በደሴ እና በወልዲያ ከተማ ላይ የሚገኙት መሆናቸውን ዋዜማ ከተቋሙ ያገኘችው መረጃ ያሳያል፡፡

ባለፈው ዓመት በርቀት ሥፍራ ላይ ከሚገኙ ትላልቅ የኃይል ማስተላለያዎች (ትራንስፎርመሮች) ኤሌክትሪክን ተቀብሎ በጸሃይ ብርሃን ለተገልጋዮች የማቅረብ ፕሮጀክትን የጀመረው ተቋሙ፣ እቅዱን ሲያወጣ ከተካተቱ ስምንት ቦታዎች መካከል በትግራይ ክልል አርአይ በተባለው አካባቢ ሊገነባ የታሰበው ፕሮጀክት አንዱ ነበር። ሆኖም በክልሉ ባለው ግጭት ሳቢያ ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ሳይከናወን ቀርቷል። በጋምቤላ ክልል አልባስ በተባለው ቦታ የተጠናቀቀው ፕሮጀክት ደሞ አካባቢው ላይ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ ሥራ መግባት አለመቻሉን ዋዜማ ከተቋሙ ተረድታለች።

ፌደራል መንግስቱ ትግራይ ክልልን በተቆጣጠረበት ወቅት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እስከ አዲግራት ከተማ ድረስ በመሄድ ሕዝቡ የተቋረጠበትን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ ሞክሯል። 

“በወቅቱ እስከ አዲግራት የሄድነው ተቋሙ አገራዊ ተቋም ስለሆነ ነው” የሚሉት መላኩ፣ “የመንግሥት መሠረተ ልማትን ከፖለቲካ በጸዳ መንገድ ነው የሠራነው። እንደ ተቋም የደረሰብን ኪሳራ ቢኖርም፣ ኃላፊነታችን ግን ባግባቡ ተወጥተናል” በማለት ለዋዜማ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመጭዎቹ ሦስት ዓመታት መላው ኢትዮጵያን አስተማማኝ በሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል አዳርሳለሁ ብሎ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የገለጹት መላኩ፣ አስተማመኝነቱን እና ተደራሽነቱን ለማረረጋገጥ ግን  የኔትወርክ ማሻሻያ እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ እና ለዚህም ስምንት ዋና ዋና ከተሞች ተመርጠው ሥራው ሲከናወን እንደቆየ ገልጸዋል። ከተመረጡት ከተማዎች መካከል የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ስትገኝበት፣ ባለፈው ዓመት ደሞ ተቋሙ ተጨማሪ ስድስት ከተሞችን ሲጨምር አዲግራት ከተማን አካቷል። ሆኖም ባለው ግጭት ምክንያት ከተሞቹ ተደራሽ መሆናቸው አጠራጣሪ ሆኗል።። 

የማሕበረሰብ ጤና አገልግሎት

ጦርነቱ ፕሮጀክታቸውን ካስተጓጎለባቸው መንግሥታዊ ተቋማት ሌላኛው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነው። ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ምርምሮችን አገር ውስጥ ባለው የሰው ኃይል ለመስራት እና በየጊዜው የሚመጡ እና ከሕዝቡ ጋር አብረው በቆዩ በሽታዎች ላይ ምርምር እና ቁጥጥር ለማድረግ እንዲያስችለው የካቲት 28፤ 2012 ዓ፣ም ከዓለም ባንክ እና ከዓለም ዓቀፉ የልማት ማኅበር በተገኘ የ150 ሚሊዮን ዶላር ብድር በሀገሪቱ አንድ ደረጃ- 1 ባዮሴፍ ላብራቶሪ እና 15 ባዮሴፍ ደረጃ- 2 ላቦራቶሪዎችን ለመገንባት ሥራዎችን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል። 

ሆኖም በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ ክልል ማይጨው እና ሑመራ ከተሞች ሊገነባ የታቀደው ባዮሴፍ ደረጃ- 2 የምርምር ላቦራቶሪ ሳይገነባ እንደቀረ የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ የላቦራቶሪ አማካሪ ጎንፋ አየና ለዋዜማ አስረድተዋል። ለሕዝብ ክፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ባዮሴፍ ላቦራቶሪ በዕቅዱ መሠረት ሳይገነባ መቅረቱ አሳዛኝ መሆኑንም አማካሪው ጨምረው ገልጸዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]