የ50ዎቹና የስልሳዎቹ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በበርካታ የዓለም የጃዝ ባንዶች አማካኝነት ተደማጭነቱን ቀጥሏል። በ50ዎቹና በስልሳዎቹ በኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ባለሞያዎች ተሰርተው የዘመናቸውን ትውልድ ሲያዝናኑ የነበሩትና እስካሁንም ድረስ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዋነኛ መገለጫ ተደርገው የሚቆጠሩት የሙዚቃ ስራዎች እንደ አንድ የተለየ የሙዚቃ ዘርፍ ተቆጥረው በተለያዩ የዓለም አገራት ተቀባይነትን አግኝተዋል። ዋነኛውንም የሙዚቃ ስራ መለያቸውንም የኢትዮጵያ ሙዚቃ መጫወት ብቻ ያደረጉ የሙዚቃ ባንዶችም ተፈጥረዋል።
(እስቲ የመዝገቡ ሀይሉን የድምፅ ዘገባ ያድምጡት)
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ታትሞ ለገበያ የበቃው Beyond Addis የተባልውና በዚሁ ዘመን በተደረሱ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች የተቃኘው አልበም ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የተውጣጡ የ15 ባንዶችን ስራ የያዘ ነበር። ከነዚህ የሙዚቃ ቡድኖች መካከል 2 ኢትዮጵያውያንን የያዘው አንዱ ባንድ ብቻ ነው። ይሁንና አንዳንዶቹ ባንዶች የመጠሪያቸውን ሳይቀር የአማርኛ ስም ያደረጉ ናቸው።
ለምሳሌ ያህልም አካሌ ውቤ የተባለው መቀመጫውን በፈረንሳይ ዋና ከተማ በፓሪስ ያደረገው ባንድ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በመጫወት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ባንድ ነው። አካሌ ውቤ አጀማመሩ ላይ በፈረንሳዊው ፍራንሲስ ፋልሴቶ የተሰበሰቡትንና ኢትዮፒከስ በመባል የሚታወቁትን ተከታታይ አልበሞች ለመጫወት የተዋቀረ ነበር። ባንዱ ከኢትዮፒከስ ስራዎች በኋላም የኢትዮጵያን ሙዚቃ መጫወት ቀጥሎ የራሱን 3 አልበሞች አሳትሟል። ባለፈው መስከረም ወርም ይከኸው ባንድ ለ 30 ዓመት ሙዚቃ መጫወት አቁሞ በታሪክ ብቻ ስሙ ሲነሳ የነበረውን ግርማ በየነን እንደገና ወደመድረክ እንዲመጣ በማድረግ አድናቂዎቹን አስደንግጧል።
ሌሎችም እንደ አካሌ ውቤ ሁሉ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ብቻ የሚሰሩ ባንዶችም አሉ። የስዊዙ ኢምፔርያል ታይገር ኦርኬስትራ፣ በአሜሪካ የሚገኙት ትዝታና ደቦ ባንዶችም እንዲሁ በተለይ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ብቻ የሚጫወቱ ባንዶች ናቸው። ከነዚህ መካከል ኢትዮያውያን ያሉበት ደቦ ባንድ ብቻ ነው። የደቦ ባንድ የሚመራውም በኢትዮጵያዊ አሜሪካዊው ሳክስፎን ተጫዋች በዳኒ መኮንን ነው።ከዳኒ በተጨማሪ በድምጽ የሚጫወተው ብሩክ ተስፋዬ ከመኖሩ በቀር ሌሎቹ 9 የቡድኑ አባላት ኢትዮጵያውያን አይደሉም።
ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ባይጫወቱም በሚሰሯቸው ሙዚቃዎች ውስጥ ሁሉ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ለዛ እንደንሸጣ የሚጠቀሙበት ብዙ ባንዶች መኖራቸውም ይስተዋላል። Beyond Addis ተብሎ በተሰየመው አልበም ውስጥ ከተካተቱት ባንዶች መካከል የአሜሪካውን ቡንዶስ ባንድ እዚህ ጋር ሊጠቀስ የሚችል ነው። አንድም ኢትዮጵያዊ በቡድኑ ባይኖርም የኢትይዮጵያ ሙዚቃ ተጽእኖ በስራዎቻቸው ላይ መኖሩን ይናገራሉ። ድንገት ሙዚቃውን ለሚሰማውም ሰው ይህን ማስተዋል አያዳግትም።
እነኚህና ሌሎችም በርካታ ባንዶች መነሻቸውን የሚያደርጉት አወድሰው በማይጠግቡት የ50ዎቹና የ60ዎቹ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ነው። የዚህም ዘመን የሙዚቃ አባት ተደርጎ የሚቆጠረው ኢትዮጵያዊው ሙላቱ አስታጥቄ በእያንዳንዷ የሙዚቃ ምት ስሙ እንዲጠራ ያደረገውን አሻራውን በግልጽ አሳርፎበታል።
የሙዚቃን ድምበር የማይገድበው ባሕርይ በሚያሳይ መልኩ የኢትዮጵያውያንን ትንሽ እንኳን ጥረት ሳይጠይቅ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በአፍሪካውያን፣ በአውሮፓውያን፣ በሰሜንና ደቡብ አሜሪካውያን ባንዶች አማካኝነት ጉዞውን ቀጥሏል። በየምንሔድበት አገር ከልባችን ምት ጋር የተሳሰረው ይህ የሙዚቃ ቃና ቀድሞ ይጠብቀናል። ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ባይኖሩም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ድምበር አቋርጦ ይሔዳል