ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የገንዘብ አስቀማጮች የመድን ፈንድ (Deposit insurance fund) ሊያቋቁም እንደሆነ ገልጿል። ለኢትዮጵያ በአይነቱ አዲስ የሆነው ተቋምን ለማቋቋምም የህግ ሰነዶች መዘጋጀታቸውን የብሄራዊ ባንኩ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር ) ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ አንስተዋል።
የገንዘብ አስቀማጮች የመድን ፈንድ ባንኮችን ለአደጋ የሚዳርግ የገንዘብ ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜ ገንዘባቸውን በባንክ ያስቀመጡ ቆጣቢዎች ገንዘባቸውን እንዳያጡ የሚረዳ የመድን ተቋም ነው።
ይህ ተቋም ለገንዘብ አስቀማጮች ደህንነት ሲባልም ከባንኮች ለአስቀማጮቻቸው የቁጠባ ዋስትና እንዲሆን አረቦን የሚቀበል ይሆናል።መሰል ተቋማት ለሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ጤናማነት ዋስትና የሚሰጡ ናቸው። እስካሁን ባለው አሰራር የኢትዮጵያ ባንኮች ከባድ አደጋ ውስጥ ቢወድቁ የገንዘብ አስቀማጮች እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን በአስተማማኝ የተመለሰበት ሁኔታ የለም።
የገንዘብ አስቀማጮች የመድን ፈንድን የሚያቋቁመው የህግ ሰነድ በጠቅላይ አቃቤ ህግ አስተያየት አልፎና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆም የፈንድ ተቋሙ ወደ ስራ እንደሚገባም ይጠበቃል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከ2013 አ.ም በጀት አመት የመጀመርያ ሶስት ወራት ለውጭ ከተላኩ ምርቶች 832 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘቷን ከብሄራዊ ባንኩ የተገኘ መረጃ ያሳያል። ከወጪ ንግድ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ15 በመቶ እድገት አሳይቷል። ለዚህም ከወርቅ የተገኘው ምንዛሬ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወርቅ የመግዣ ዋጋውን ከፍ ካደረገ በኃላ የሚቀርብለት የወርቅ መጠን መጨመሩን የባንኩ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶክተር) ገልጸዋል፡፡
የባንኩ ገዥ ከዚህ ቀደም እንደገለጹት ብሄራዊ ባንኩ ወርቅን ከአቅራቢዎች የሚገዛበት ዋጋ ላይ የመቶኛ ጭማሬ በማድረጉ የሚቀርብለት ወርቅ ከጎረቤት ሀገራትም የመጣ ሳይሆን እንዳልቀረ የሚያስጠረጥሩ ምልክቶች ታይተዋል። በሌላ በኩል የኮሮና ቫይረስ ሲከሰት ኢትዮጵያ የየብስ ድንበሮቿን ስለዘጋች ወርቅ በኮንትሮባንድ ከሀገሪቱ የሚወጣበትን መንገድ ዘግቶት መቆየቱም ከወርቅ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ አሳድጎታል።
ለገቢ ሸቀጦችም በሶስቱ ወራት 3.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላርን ኢትዮጵያ ወጪ ያደረገች ሲሆን ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲታይ በሰባት በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ቢሆንም ግን የንግድ ሚዛን መዛነፉ አሁንም ከመስተካከል ርቆ ለመገኘቱ ማሳያ ነው።
መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጪውን ለመሸፈን እንደ ዋነኛ አማራጭ ከወሰደው የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ወደ 33.46 ቢሊየን ብር በሦስት ወራት ውስጥ ሰብስቧል ብሏል ብሄራዊ ባንኩ።
የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭን እንደ አዲስ ለማስጀመር ሲወጠን በገበያ እንዲመራ በማድረግና ባንኮችን ጨምሮ ብዙ ተቋማት እንዲሳተፉበት መደረጉ በቂ ሀብት ለመሰብሰብ እንዳስቻለም ብሄራዊ ባንኩ ገልጿል። ከዚህ ቀደም መንግስት ወጪውን ለመሸፈን ብሄራዊ ባንኩን ገንዘብ እንዲያትም በሚደርግ መልኩ መሆኑ በሀገሪቱ የዋጋ ንረት በማስከተሉ በገበያ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ዋጋ ንረት ፈጣሪ ባልሆነ መልኩ መጠቀም ያስችላል ተብሎ የታመነበት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ በአዲስ መልክ ባለፈው አመት ተጀምሯል።
ባንኮች 55 ቢሊየን ብር ብድርን ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ያቀረቡ ሲሆን አብዛኛው ብድርም ለግሉ ዘርፍ የቀረበ መሆኑም በብሄራዊ ባንኩ ገዥ ይናገር ደሴ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ አንድን ተበዳሪ ስንት ባንክ ላይ ብድር እንደወሰደ እና ሌሎች የተበዳሪ መረጃዎችን ለማግኘት እና ለማወቅ አስቸጋሪ ነው ; ብዙ መረጃ ክፍተቶችም የነበሩበት ነው፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የክሬዲት ሪፈረንስ ቢሮ ተቋቁሞ የብድር መረጃ አገልግሎት በመስጠት ባንኮች ሰለደንበኞቻቸው የብድር ታሪክ እና ተጋላጭነት የተሻለ መረጃ እንዲኖራቸውና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የብድር ትንተና እንዲሰሩ አሰራር ተዘርግቷል። እስካሁን ከ3 ሚሊዮን በላይ የተበዳሪዎች መረጃ በክሬዲት ሪፈረንስ ቢሮ የመረጃ ቋት ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል።
በኢትዮጵያ እያደገ በመጣው የባንክ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት ስላለ ይህንን እጥረት ለመቅረፍ እንዲያስችል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል አቃቂ የሚገኘውን የፋይናንስ ስልጠና አካዳሚ በአዲስ መልክ እንዲቋቋም ደንብ ተዘጋጅቶለታል ተብሏል። በቅርቡ በሚንስትሮች ምክርቤት ከፀደቀ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። የስልጠና ማዕከሉ ለመንግስት እና ለግል ባንኮች ለፋይናንስ ተቋማት፣ ለኢንሹራንስ ሰራተኞች ስልጠና ይሰጣል። በተለይም አሁን ላይ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ላይ ከፍተኛ የባለሙያዎች እጥረት ስላለ ይህንን ለመቅረፍ ባንኮች ከሚሰጡት አጫጭር ስልጠና በተጨማሪ ስልጠና ማእከሉ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ተስፋ ተደርጓል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]