SONY DSCበአዲስ አበባ ሲካሄድ የሰነበተው የመጨረሻ የደቡብ ሱዳን ሰላም ድርድር እነሆ ሰኞ ዕለት ያለ ውጤት ተበትኗል፡፡ “ኢጋድ ፕላስ” በተሰኙት አደራዳሪዎች በተቀመጠላቸው ቀነ-ገደብ ዕለት ተቃዋሚው ሬክ ማቻርና ሶስተኛ ወገን ተደራዳሪዎች የሚባሉት ከእስር የተፈቱ የቀድሞ ባለስልጣናት የሰላም ሰነዱን ሲፈርሙ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ግን ተጨማሪ ሁለት ሳምንት ያስፈልገኛል በማለት ሳይፈርሙ ቀርተዋል፡፡

የሰላም ስምምነት መደረሱ ወይም የግጭቱ መቀጠል በደቡብ ሱዳን ላይ የሚኖረውን አንድምታ ባለፈው ሳምንት ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ አሁን ደግሞ የሰላም ሰነዱ ላለመፈረሙ ዋነኛው ምክንያቱ ምን ይሆን? ግጭቱ ከቀጠለስ በጎረቤት ሀገሮች በተለይም በኢትዮጵያ ላይ ምን ዓይነት የፀጥታና ብሄራዊ ደህንነት አንድምታዎች ይኖሩት ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች መፈተሽ አግባብ ይመስለናል፡፡ እነሆ የቻላቸው ታደሰን ዘገባ አድምጡ

ባሳለፍነው ሳምንት የሱዳኑን ኦማር አልበሽርን ጨምሮ ሁሉም የኢጋድ ሀገራት መሪዎች በደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነት ጉዳይ ላይ በካምፓላና አዲስ አበባ ሁለት ዙር ምክክሮችን ቢያደርጉም ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ግን በአስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ኩም አደርገዋቸዋል፡፡ ባለ ግማሽ ፊርማ ሰነድ አስታቅፈዋቸው ዞር አሉ፡፡
መቼም ማንኛውም የሰላም ድርድርና ስምምነት የሚሳካው የተደራዳሪዎች ቅን መንፈስ (good will) ሲኖር እንደሆነ አይካድም፡፡ ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሸ በስጦታ እንደተበረከተላቸው የሚነገርላትን ጥቁር የቴክሳስ ባርኔጣና እንደ ባላንጣቸው ጄኔራል ኡመር አልበሸር በትረ-መኮንን የማይለያቸው ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና የፖለቲካ ሴራ አዋቂ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ባለ ዶክትሬቱ ሬክ ማቻር ግን በብልጣብልጥነትና አለመተማመን ተክነዋል፡፡ ለምሳሌ ኪር ተቀናቃኛቸው ሰነዱን እስኪፈርሙ ጠብቀው በመጨረሻው ሰዓት አልፈርምም ማለታቸው የተቀናቃኛቸውን ስስ ጎን ለማጋለጥ፣ በአንጣሩ ደግሞ የራሳቸውን የበላይነት ለማስረገጥ እንደፈለጉ ያሳብቅባቸዋል፡፡

ሰውዬው በሰላም ሰነዱ መሰረተ ሃሳብ የተስማሙ ቢመስሉም የፌደራሊዝም አወቃቀር በሚኖረው የሽግግር ጊዜ በነዳጅ ዘይት የበለፀጉትን ሶስት ግዛቶች ተቀዋሚዎች በበላይነት እንዲያስተዳድሩ የሚለው ሃሳብ የእግር እሳት ሆኖባቸዋል፡፡

በተለይ ደግሞ በዋናነት በዲንቃዎች ግዛት ውስጥ የምትገኘው ዋና ከተማዋ ጁባ ከወታደራዊ ቀጠና ነፃ እንድትሆን የሚለው ሃሳብ የጉረሮ አጥንት እንደሆነባቸው አልሽሽጉም፡፡ “ጁባ ከእጄ የምትወጣው በመቃብሬ ላይ ነው” የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ፊታቸው በቀላሉ የማይፈታው ኪር “የመንግስቴንና የሀገሬን ሉዓላዊነት አሳልፌ እንድሰጥ በውጭ ጫና እጄን እየተቆለመምኩ ነው” ሲሉ ሰንብተዋል፡፡ ባሁኑ ጊዜ የክብርና ሉዓላዊነት ጉዳይ የህዝቡን ቀልብ የሚገዛ ይመስል፡፡ ተቃዋሚዎች ግን ምላሽ አላጡም፡፡ “የእርስዎና የሀገሪቱ ሉዓላዊነት የከሰመው እኮ የኡጋንዳን ወታደሮች ወደ ሀገራችን ጋብዘው እኛን ሲያስወጉን ነው” ብለዋቸዋል፡፡
የሽምግልና ብቃታቸውና ትዕግስታቸው ክፉኛ የተፈተነው ኢትዮጵያዊው የኢጋድ ዋና አደራዳሪ አምባሳደር ስዩም መስፍን “ኪር ከሁለት ሳምንት በኃላ ተመልሰው ሰነዱን ይፈርማሉ” የሚል ተስፋ ቢሰጡም በጊዜው ግን ሰውዬው ሌላ አዲስ የመደራደሪያ ሃሳብ ይዘው ስላለመምጣታቸው ምንም ማረጋጋጫ አልነበረም፡፡ ሆኖም የማዕቀቡ ዛቻ እየተሟሟቀ ሲሄድ ኪር ሰነዱን ለመፈረም መዘጋጀታቸውን ለአሜሪካ ባለስልጣናት ትናንት ማረጋገጣቸው መልካም ዜና ነው፡፡
በእርግጥ የሰላም ሰነዱ ዋና ዓላማ ተኩስ ማስቆም ስለሆነ ከፍትህና ተጠያቂነት ይልቅ በስልጣን ክፍፍል ላይ ብቻ ማተኮሩ አይካድም፡፡ የሚፈለገው ነገር ደቡብ ሱዳን የዚምባብዌንና የኬንያን የስልጣን መጋራት ሞዴል እንድትከተል ይመስላል፡፡

 

ሁለቱ የቀድሞ ነፃ አውጭ ጓዶች (comrades-in-arms) ግን እንኳን አብሮ ለመስራት ፊት ለፊት ለመተያየት የማይፈለጉ መሆናቸውን በተደጋጋሚ በተግባር አሳይተዋል፡፡ ከዝነኛው ነፃ አውጭ መሪያቸው ጆን ጋራንግ ህልም በተቃራኒው በነዳጅ ሃብት የተንበሸበሸችውን ደቡብ ሱዳንን ያስገነጠሉት ሁለቱ ሰዎች ወደፊትም በስምምነት የሚኖሩ አይመስሉም፡፡

በእርግጥ ኪር ውለው አድረው ሰነዱን ካልፈረሙ ማዕቀብ ሊጣልባቸው ይችላል፡፡ ችግሩ ግን በእንደዚህ ዓይነት ጦርነት ውስጥ በአንድ ወገን ላይ ብቻ ማዕቀብ መጣል እምብዛም የማይደገፍ መሆኑ ነው፡፡ በአናቱ ደግሞ ጎረቤት ሀገሮች ተቃራኒ ፍላጎቶች ያሏቸው መሆኑ፡፡ ምዕራባዊያን ደግሞ የክፍለ-አህጉሩን ሀገሮች በአብዛኛው የማያስማማ ሃሳብ የመጫን ፍላጎት ያላቸው አይመስሉም፡፡ ስለሆነም ለሁሉም አካላት ተመራጩ ነገር የሰነዱ መፈረም ብቻ ይሆናል፡፡
መቼም ደቡብ ሱዳን የኡጋንዳና የሱዳን የውክልና ጦርነት የፍልሚያ መድረክ (theatre of proxy war) መሆኗ ግልፅ ነው፡፡ ግጭቱ ቢቀጥል ደግሞ ኢትዮጵያንና ሌሎችንም ሀገሮች በእጅ አዙር ግጭት ውስጥ ላለማስገባቱ ማረጋገጫ የለም፡፡ ለአሁኑ ግን ግጭቱ ቢያንስ በኢትዮጵያ ላይ ምን አንድምታዎች እንደሚኖሩት በመጠኑ እንፈትሽ፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ግን ወደኃላ መለስ ብለን ብናይ የአሁኑ የአዲስ አበባው ድርድር ታሪካዊነት እንዳለው እንረዳልን፡፡ እኤአ በ1972 ዓ.ም በሱዳን መንግስትና “የአናንያ ንቅናቄ” (Ananya Movement) ተብለው በሚታወቁት ጥቁሮቹ የደቡብ አማፂያን መካከል የሰላም ስምምነት የተደረሰው አዲስ አበባ ላይ ነበር፡፡ በአፄ ሃይለ ሥላሴ ዋና ሸምጋይነት ማለት ነው፡፡ ከ43 ዓመታት በኃዋላ ደግሞ አሁን ሌላ ሽምግልና አዲስ አበባ ላይ ሲካሄድ መክረሙ ግጥምጥሞሽ ነው፡፡
ከንጉሱ ጋር የሚስተካከል አርቆ አሳቢነትና የሸምጋይነት ብቃት እንደሌላቸው የሚነገርላቸው የአሁኖቹ የኢትዮጵያ መሪዎች በሌሎች መሪዎች እየታገዙም እንኳ ታሪክን የመድገም ዕድል ስለማግኘታቸው በቀናት ውስጥ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ግን ኢጋድ ለደቡብ ሱዳን ያቀረበላት ሀገራዊ አወቃቀር አደጋ ካዘለው የሀገራችን ብሄር-ተኮር ፌደራሊዝም ጋር መመሳሰሉ የመሪዎቻችን አሻራ ተደርጎ ከተመዘገበላቸው ምፀታዊ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመጣ ባለፉት ወራት ህፃናትና ሴቶች የሚበዙባቸው ሁለት መቶ ሃያ ሺህ ያህል የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ክልሎች ተሰደው በግዙፎቹ አምስት የስደተኛ ጣቢያዎችም እንደተጠለሉ የተባበሩት መንግስታት ስደተኞች ድርጅት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በእርግጥ መንግስት በስደተኞች ላይ የሚከተለው ፖሊሲ “ለቀቅ ያለ” (open door policy) ስለሆነ ይመስላል ከግጭቱ በፊትም በዓለም ዓቀፉ ስደተኞች ድርጅት የተመዘገቡ 46 ሺህ ደቡብ ሱዳናዊያን ከሀገሬው ሰው ጋር ተቀላቅለው ይኖራሉ፡፡ በተለይ የኑዌር ጎሳ ተወላጅ ደቡብ ሱዳናዊያን ከድሮም ጀምሮ በሂደት ኢትዮጵያዊ ዜግነትም እንደያዙ አይካድም፡፡ ለዚህም ነው በጋምቤላ አነስተኛ ቁጥር የነበራቸው ኑዌሮች በአዲሱ ህዝብ ቆጠራ ቁጥራቸው በከፍተኛ ፍጥነት ጨምሮ የተገኘው፡፡

ከዚህ በመነሳት ስናየው የኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ውልውል ግልፅ ይሆናል፡፡ በአንድ በኩል ከጁባው መንግስት ጋር ቢጋጭ የአኙዋክ ሸምቅ ተዋጊ ሃይሎችን አደራጅቶ ሰላሜን ይነሳዋል ብሎ ይሰጋል፡፡ በተለይ እኤአ ከ1995ቱ የጎሳ ግጭት ወዲህ መንግስት ስር ሰደደ ኢትዮጵያዊ ስሜት ያላቸውን ነባሮቹን አኝዋኮች እያገለለ ኑዌሮችን ማቅረቡ የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ክልሉም በዘመነ-ኢህአዴግ ለመጀመሪያ ጊዜ በኑዌር ተወላጅ ፕሬዝዳንት መመራት የጀመረው ገና በቅርቡ ነው፡፡ ስለሆነም አኝዋኮች ስር የሰደደ ቅሬታ አለባቸው፡፡ ከአሁን በፊትም በሁለቱ ጎሳዎች መካከል በርካታ ግጭቶች መከሰታቸው አይዘነጋም፡፡

መንግስት አማፂያኑን ቢያስቀይም ደግሞ በጋምቤላ ኑዌሮችና አኝዋኮች መካከል የጎሳ ግጭት ይቀሰቅሱብኛል የሚል ስጋት ይኖርበታል፡፡ በእርግጥም የአማፂያኑ ወቅታዊ የበላይነት የሚታይባቸውና በርካታ ኑዌሮች ያሉባቸው ጆንገሊና ላይኛው ናይል ክልሎች ከጋምቤላ ጋር የሚዋሰኑ መሆኑ ስጋቱን አሳማኝ ያደርገዋል፡፡ መንግስት ወገንተኛ ለመሆን ቢገደድ ግን በአንፃራዊነት በዲንቃዎች የበላይነት ከተያዘው መንግስት ከሚመጣው አደጋ ይልቅ የአማፂያኑ የበለጠ ስለሚያሰጋው ለእነሱ ለማድላት ይገደዳል፡፡
መቼም የደቡብ ሱዳን ግጭት በግልፅ ክልላዊ ገፅታ ቢይዝም ባይዝም ጋምቤላ ለመንግስት ስስ ብልት ነች፡፡ ተወደደም ተጠላ የጋምቤላ ፀጥታ በደቡብ ሱዳን ፀጥታ ይወሰናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዓለም ዓቀፍ ካምፓኒዎች በነዳጅ ዘይት ፍለጋ የሚርመሰመሱባት ናት፡፡ “የደቡብ ሱዳን አፍንጫ ሲመታ የጋምቤላ ዓይን ያለቅሳል” ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ እንዲያውም ደቡብ ሱዳን የተረጋጋች ሀገር አይደለችም እንጂ ጋምቤላ የዩክሬኗን ዶኔስክ ግዛት ዓይነት ቀውስ ለመቀስቀስ የምትችል እንደሆነች መታዘብ አያዳግትም፡፡
አንድ ሰሞን ኢትዮጵያ አማፂያንን ትረዳለች፤ የአማፂያን ወታደሮችም ጋምቤላ ውስጥ ህክምና እያገኙ ወደ ጦር ግምባር ይመለሳሉ የሚሉ ጭምጭምታዎች ከጁባ ማፈትለክ የጀመሩትም ይህንን የመንግስት አጣብቂኝ በመገንዘብ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለኢትዮጵያ ወገንተኝነት እስካሁን ውሃ የሚቋጥር ማስረጃ ሊቀርብ አልቻለም እንጂ፡፡
በጥቅሉ ሲታይ ምናልባት ከሱዳን በስተቀር የአዲሲቷን ሀገር ሰላም የማይፈልግ የኢጋድ አባል ሀገር ያለ አይመስልም፡፡

ስለዚህ አሁን ያለው ዋናው ጥያቄ ፕሬዝዳንት ኪር ሰነዱን ፈርመው ሀገሪቱ ብሄር-ተኮር ፊደራሊዝም ይኖራት ይሆን? ወይስ የለየለት የእርስ በርስ ጎሳዊ ጦርነትና እንደ ሱማሊያ መፈራረስ ይጠብቃት ይሆን? የሚለው ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ዘላቂ ሰላምና ፍትህ ስለመምጣቱ አጠራጣሪ ቢሆንም ሰዎቹ በረዥም ግጭት ውስጥ መቆየት ስለማይችሉና የመጫዎቻ ካርዶቻቸውንም ስለጨረሱ ለጊዜው ስምምነቱ ተፈርሞ ግጭቱ የሚቆም ይመስላል፡፡ ሆኖም ግን ውስብስቡን ስምምነት የመተግበር ከባድ ፈተና ፊት ለፊታቸው ተደቅኗል፡፡
መቼም በሰላም ስም ፍትህን ማዳፈን በተለመደባት አፍሪካ ውስጥ ደቡብ ሱዳናዊያን እንፃራዊ ሰላም ቢያገኙም እንኳ ለተፈፀመባቸው ግፍ ግን ተገቢውን ፍትህን ለማግኘት ስለመቻላቸው ያጠራጥራል ነው፡፡ ለፍትህ ጥብቅና መቆም ያለበት ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብም የተሸከመው የሞራልና የህግ ሃላፊነት የሚፈተነው ያኔ ይሆናል፡፡

የአዘጋጁ ማስታወሻ-የመጀመሪያ ክፍል ሪፖርታችንን በዚህ ማስፈንጠሪያ ማዳመጥ ይቻላል http://wazemaradio.com/?p=951