ከግጭቱ ማግስት ጀምሮ በአፍሪካ ቀንዱ በይነ-መንግስታት ድርጅት ኢጋድ አማካኝነት ከ15 በላይ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ቢደረሱም አንዳቸውም ፍሪያማ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ደግሞ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ድርድር ሁለቱ ወገኖች እኤአ እስከ ነሃሴ 17 ድረስ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የመጨረሻ ቀነ-ገደብ ተቆርጦላቸዋል፡፡ የወቅቱ ኢጋድ ሊቀመንበር የሆኑት የኢትየጵያው ጠቅላይ ሚንስትርና የኬንያው ፕሬዝዳንትም ኡጋንዳ ካምፓላ ለውይይት ከተው ሰንብተዋል፡፡ ቻላቸው ታደሰ ጉዳዩን በዝርዝር ተመልክቶ ያሰናዳውን አድምጡለት
ነፃነቷን በህዝበ ውሳኔ እኤአ በ2011 ያገኘችው አፍሪካዊቷ እሞቦቅቅላ ሀገር ደቡብ ሱዳን ከውልደቷ ማግስት ጀምሮ ሰላም እንደራቃት ነው፡፡ ዜጎቿም አዲሱን የነፃነት አየር ሳያጣጥሙት በድጋሚ በባሩድ ሽታ መታጠን የጀመሩት እኤአ በታህሳስ 2013 የዲንቃ ጎሳ ተወላጁ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በኑዌር ተወላጁ የቀድሞው ምክትላቸው ሬክ ማቻር መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጎብኛል ካሉ በኃላ ነበር፡፡ አስካሁንም በግጭቱ ከ50 ሺህ በላይ ንፁሃን ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል፡፡ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ደግሞ ለመፈናቀልና ስደት ተዳርገዋል፡፡ ሴቶችን አስገድዶ መድፍር፣ ህፃናትን በውትድርና መመልመል፣ ጎሳን ማዕከል ያደረገ ጅምላ ጭፍጨፋን ጨምሮ በርካታ ዓለም ዓቀፍ የጦር ወንጀሎች በሁለቱም ወገኖች እንደተፈፀሙ ዓለም ዓቀፍ አጣሪ ቡድኖች ካረጋገጡ ቆይተዋል፡፡
ከግጭቱ ማግስት ጀምሮ በአፍሪካ ቀንዱ በይነ-መንግስታት ድርጅት ኢጋድ አማካኝነት ከ15 በላይ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ቢደረሱም አንዳቸውም ፍሪያማ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ደግሞ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ድርድር ሁለቱ ወገኖች እኤአ እስከ ነሃሴ 17 ድረስ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የመጨረሻ ቀነ-ገደብ ተቆርጦላቸዋል፡፡ በእርግጥም አደራዳሪዎቹ “ኢጋድ ፕላስ” (IGAD- Plus) ተብለው የሚታወቁትን የአፍሪካ ህብረት፣ አሜሪካ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣፣ ቻይና፣ አውሮፓ ህብረትና የተመድ ፀጥታው ምክር ቤትን ማቀፉ የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡ የወቅቱ ኢጋድ ሊቀመንበር የሆኑት የኢትየጵያው ጠቅላይ ሚንስትርና የኬንያው ፕሬዝዳንትም ኡጋንዳ ካምፓላ ለውይይት ከተው ሰንብተዋል፡፡
እንደታሰበው ተፋላሚ ወገኖች በቀነ-ገደቡ አስተማማኝ ሰላም ስምምነት ላይ ይደርሱ ይሆን? ድርድሩ ካልተሳካስ ግጭቱና ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ የሚወስደው እርምጃ ምን መልክ ይኖረው ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች መመርመር ተገቢ ነው፡፡
እኤአ በታህሳስ 2013 በደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰው ግጭት ጎሳዊ መልክ የያዘው ወደያውኑ ነበር፡፡ የግጭቱ ዋነኛ ማጠንጠኛ ከነፃነት ትግሉ ዘመን ጀምሮ በጎሰኝነትና መንደርተኝነት መስፈርት የተመሰረተ የሃብትና ስልጣን ክፍፍል ብሎም የግልሰባዊ ክብርና ዝና ፉክክር ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ፖለቲከኞችም የዘመናዊ የሀገር ግንባታና አመራር ዘይቤዎችን በመከተል ፋንታ በሽምቅ ውጊያ አስተሳሰብና አሰራር ላይ ተቸክለው ስለመቅረታቸው ጥርጥር የለውም፡፡
በናይጀሪያዊው ኦሌሴጎን ኦባሳንጆ የተመራው የአፍሪካ ህብረት አጣሪ ቡድንም የተፈፀሙ የጦር ወንጀሎችን ባለፈው ጥር ወር አጥንቶ ካጠናቀቀ በኃላ ሪፖርቱ ይፋ እንዳይሆን ቢደረግም አፈትልከው የወጡ መረጃዎች ግን ሳልቫ ኪርንና ሬክ ማቻርን ተጠያቂ በማድረግ ከፖለቲካ ተዋናይነታው ሙሉ በሙሉ እንዲታዱ የውሳኔ ሃሳብ እንዳቀረበ አልጄዚራ ቴሌቪዥን ዘግቦ ነበር፡፡ ይህን ግን አሁንም ሆነ ወደፊት ተግባራዊ ማድረግ የማይታሰብ ነው፡፡
በእርግጥ የሰላም ሂደቱ እንዳይሳካ እንቅፋት ከሆኑት ጉዳዮች አንደኛው የክፍለ አህጉሩ ሀገሮች ጥቅም ግጭት መሆኑ አያከራክርም፡፡ በርካታ ተንታኞችም ሀገሪቱን “የአፍሪካ ቀንዷ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ” በማለት የሚጠሯት የግጭቱን ክልላዊ ውስብስብነት በመገንዘብ ነው፡፡ ተቀማጭነቱ አሜሪካ የሆነው “ይብቃ ፕሮጄክት” (Enough Project) እስካሁንም በተፋላሚ ወገኖች ላይ ማዕቀብ ላለመጣሉ ሱዳንንና ኡጋንዳን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ሱዳን ብታስተባብልም አማፂያንን እንደምትደግፍ ይነገራል፡፡ የኡጋንዳ ወታደሮች ደግሞ ደቡብ ሱዳን ግዛት ውስጥ ሰፍረው በግልፅ ከሳልቫ ኪር መንግስት ጎን ሆነው መዋጋት የጀመሩት ገና ከማለዳው ነበር፡፡ በእርግጥ ከአማፂያንና መንግስት በተጨማሪም ሌሎች ተደራዳሪ ግልሰቦችና ጎሳዊ ቡድኖች መበራከታቸው የሰላም ሂደቱን እያወሳሰበው ይገኛል፡፡
እስካሁን ኢጋድን ክፉኛ በፈተኑት ድርድሮች የተፈረሙት የተኩስ ማቆም ስምምነቶቹ በሙሉ የተፈረሙበት ቀለም ሳይደርቅ በአንዱ ወይም በሌላኛው ወገን ሲጣሱ አንዳንዶቹ ደግሞ ያለ ምንም ስምምነት ተበትነው ቀርተዋል፡፡ ኢጋድም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም እርምጃ ለመውሰድ የማይችል መሆኑ በተግባር ታይቷል፡፡ በድርድሮችም ተፋላሚ ወገኖች ወደ ዋነኛዎቹ ጉዳዮች ከመግባት ይልቅ በስነ-ስርዓት ጉዳዮች ላይ ብቻ በጣም ረዥም ጊዜ ማጥፋታቸው የስልጣን ጥማታቸውን ልክ አልባነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በያዝነው ዓመትም ተደራዳሪዎቹን ለረዥም ጊዜ በዘመናዊና ውድ ሆቴሎች ሲቀማጠሉ ለምግባቸው፣ ለመኝታቸውና ለመጠጥ የሚወጣው ወጭ ከፍተኛነት አውሮፓ ህበረትን ክፉኛ እንዳማረረውና ከአቅም በላይም እንደሆነበት አዲስ አበባ የሚገኙ ዲፕሎማቶች መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
አሁን ግን የዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ ተፋላሚ ወገኖችን “በናንተ ላይ ትዕግሰቴ ተሟጧል” እያላቸው ይገኛል፡፡ ከእንግዲህ “በትር/ልምጭ” (stick) እንጂ “ካሮት” (carrot) የማቅረብ ፍላጎቱ ያለውም አይመስልም፡፡ እነሱም ጀንበራቸው ማዘቅዘቋን ሳይረዱት አልቀሩም፡፡ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የስልጣን ዘመንም ስለተጠናቀቀና ተቃዋሚዎችም የመከፋፈል አደጋ እንደተጋረጠባቸው ሰሞኑን ሱዳን ትሪቡን መዘገቡ የሰላም ስምምነት ለመፈረም ያበረታታቸው ይሆናል የሚል ተስፋ አሳድሯል፡፡
ሆኖም ግን የሁለቱ ወገኖች ጦር አዛዦችም ካሁኑ ሰነዱን እያጣጣሉት ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ ደግሞ ሁኔታው ሌላ አዲስ አቅጣጫ ይዟል፡፡ ሁለት ከፍተኛ ጄኔራሎች ከአማፂያኑ ተገንጥለው መውጣታቸውን በይፋ የገለፁ ሲሆን ሳልቫ ኪርም ሆኑ ማቻር ከሰላም ድርድሩ እንዲገለሉ በመጠየቅ የአፍሪካ ህብረት አጣሪ ቡድን ቀደም ሲል ካቀረበው ምክረ ሃሳብ ጋር የሚመሳሰል ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ እንዲያውም ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የሽግግር መንግስቱን እንዲመሩት በመጠየቅ ለስልጣን ፍላጎት እንዳላቸው ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ የጄኔራሎቹ ማፈንገጥ የማቻርን የመደራደር አቅም የሚያዳክም፤ በአንጣሩ ደግሞ ለጁባው መንግስት የልብ ልብ የሚሰጥ በመሆኑ ድርድሩን እንዳያኮላሸው ያሰጋል፡፡
አሜሪካ ከግጭቱ አፈታት ሂደት በአብዛኛው ገለል ብላ ብትቆይም ፕሬዝዳንት ኦባማ ባለፈው ወር አዲስ አበባ ላይ ከኬንያ፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳና አፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ጋር በጉዳዩ ላይ ሰፊ የጋራ ምክክር አድርገዋል፡፡ መቼም ስለ አፍሪካ ፖለቲካ ጥልቅ እውቀት ያላቸውን የፀጥታ አማካሪያቸውን ሱዛን ራይስን ያስከተሉት ኦባማ ለግጭቱ ፖለቲካዊ ቀውስ የመጨረሻ መፍትሄና ቀጣይ እርምጃዎች ሳያስቀምጡ ይመለሳሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ የመፍትሄ ሃሳብን በግድም በውድም ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ ደግሞ ከአንድ ልዕለ ሃያል ሀገር መሪ የሚጠበቅ ነው፡፡ በአፍሪካ ህብረቱ ንግግራቸውም አፅንዖት የሰጡት የማዕቀብን ጉዳይ ነበር፡፡ መቼም አሜሪካ በዋናነት የደቡብ ሱዳን የጡት አባት መሆኗ አይካድም፡፡
አሁን በኢጋድ አመንጪነት በቀረበው የሰላም ስምምነት ሰነድ ላይ ድርድሩ አዲስ አበባ ላይ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሰነዱ በሚቋቋመው የአንድነት ሽግግር መንግስት ውስጥ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የፕሬዝዳንትነቱን መንበር ጨምሮ አብዛኛውን ስልጣን እንዲይዝና አማፂያን ደግሞ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትነቱንና 33 በመቶ የካቢኔ ስልጣኖችን እንዲሰጣቸው ሃሳብ አቅርቧል፡፡ በነዳጅ ዘይት በበለፀጉትና አማፂያኑ በሚቆጣጠሯቸው ጆነገሊ፣ ዩኒቲና የላይኛው ናይል ግዛቶች ግን በተለየ አማፂያን የስልጣን የበላይነት እንዲኖራቸው ሃሳብ የቀረበ ሲሆን ይህ ግን ለጁባው መንግስት እንዳልተዋጠለት የቻይናው ዥንዋ በቅርቡ ዘግቦ ነበር፡፡ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስም ለሁለት ዓመት ከግማሽ በሚቆየው ሽግግር መንግስትም ዋና ከተማዋ ጁባ ከወታደራዊ ቀጠና ነፃ ሆና በዓለም ዓቀፍ ወታደሮች ጥበቃ ስር እንድትሆን ይጠይቃል፡፡ ይህም ፕሬዝዳንቱ በራሳቸው ጎሳ ተወላጆች ያዋቀሩትን የግል ሰራዊታቸውን ስለሚያሳጣቸው ፍቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ ተብሎ ተሰግቷል፡፡ በሽግግሩ ጊዜም ሁለቱ ሰራዊቶች ተነጣጥለው ይቆያሉ፡፡
መቼም የሰላም ስምምነቱ ሰነድ ከተፈረመ ወይም ሳይሳካ ቀርቶ ግጭቱ የሚቀጥልና ማዕቀቦችም የሚጣሉ ከሆነ በኢትዮጵያና በጠቅላላው ክፍለ አህጉሩ አሰላለፍ ላይ የሚኖረው አንድምታ ራሱን የቻለ ሌላ አርዕስተ ጉዳይ ስለሆነ በይደር ማቆየቱ ይሻላል፡፡ ስለዚህ አሁን ማንሳት የሚሻለው ጥያቄ በመጭዎቹ የአጭርና ረዥም ጊዚያት ምን ሊከሰት ይችላል? የሚለውን ነው፡፡ እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አራት የቢሆን መላ ምቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
አንደኛው መላ ምት “ሁሉም አሸናፊ” (win-win) የሚሆኑበት ወይም “አንደኛው የበለጠ አሸናፊ ሌላኛው ተሸናፊ” (win-lose) የሚሆኑበት የሰላም ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚለው ነው፡፡ ካለው ግፊት አንፃር ይህ መላ ምት የመሳካት ዕድሉ ከፍተኛ ይመስላል፡፡
ሁለተኛው መላ ምት ድርድሩ በስምምነት ካልተቋጨ ሁለቱ ወገኖች ከዓለም ኣቀፉ ህብረተሰብ ጠንካራ ተፅዕኖ ከመምጣቱ በፊት አንዳቸው በሌላኛው ላይ ሙሉ ወታደራዊ የበላይነት ለመጎናፀፍ በፍጥነት የሞት ሽረት ውጊያ ውስጥ ለመግባት ይገደዳሉ፡፡ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ሙሉ በሙሉ በጦር ሜዳ ድል ለማሳካት ያስችለናል ብለው ስለሚያስቡ ማለት ነው፡፡ ሆኖም ለዚህ እንቅፋት የሚሆንባቸው እስካሁንም ድረስ ተዋግተው እንዳቸው ባንዳቸው ላይ አንፃራዊ ወታደራዊ የበላይነት ያልተጎናፀፉ መሆናቸው ነው፡፡ በተጨማሪም አንፃራዊ ወታደራዊ የበላይነት ለመጎናፀፍ የጦርነቱ አድማስ ክልላዊ መልክ እንዲኖረው ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይህም በዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ የሚጣሉ ማዕቀቦች ሁሉ ተፈፃሚነት እንዳይኖራቸው እንቅፋት ይሆናል፡፡
ሦስተኛው በአሜሪካ ሃሳብ አመንጪነት የተባበሩት መንግስታት ፀጥታው ምክር ቤት በአማፂያኑና በጁባው መንግስት ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲሁም በከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸውና ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦቻቸው ላይ የባንክ ተቀማጭ ገንዘብን እገዳ፣ የገንዘብ ዝውውርና የውጭ ጉዞ እገዳ ሊጥልባቸው ይችላል፡፡ ዓላማውም ተቀናቃኞቹ ባስቸኳይ ተኩስ እንዲያቆሙና ለሰላም ድርድር እንዲቀመጡ ማስገደድ ነው፡፡ በፀጥታው ምክር ቤት የሚጣሉ የተመረጡ ማዕቀቦች (targeted sanctions) ደግሞ ሁሉም ሀገሮችና ድርጅቶች እንዲተገብሩት የሚያስገድድ በመሆኑ ጠንከር ያለ ጥርስ ያለውና በሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ላይ ከባድ ተፅዕኖ የሚያሳርፉ ይሆናሉ፡፡
በእርግጥ ቀደም ሲልም አሜሪካና አውሮፓ ህብረት በሁለቱ ወገኖች የተወሰኑ ወታደራዊ አዛዦች ላይ የጉዞና ገንዘብ እገዳ ቢጥሉም ከሰዎቹ የስራ ባህሪ አንፃር ማዕቀቦቹ የይስሙላ ከመሆን አላመለጡም፡፡ በእርግጥ በኃላ ላይ የፀጥታው ምክር ቤት በሀገሪቱ ላይ አጠቃላይ የሆነ ማዕቀብ ቢያዘጋጅም እስካሁን ማንንም ግለሰብ ወይም ወገን በስም ለይቶ ስላልጠቀሰ ተፈፃሚ አልሆነም፡፡ ሆኖም ደቡብ ሱዳን ሉዓላዊ ሀገር በመሆኗና ከሱዳን ጋር ባላት ጥል ሳቢያም የጁባው መንግስት የተቃዋሚዎችን ያህል የመሳሪያ ማዕቀብ ሰለባ ላይሆን ይችላል፡፡
አራተኛው የቢሆን መላ ምት የፀጥታው ምክር ቤት በሁለቱም ወገኖች በኩል በጦር ወንጀል የሚጠረጠሩ ፖለቲከኞችንና ወታደራዊ አዛዦችን ጉዳይ ወደ ዓለም ኣቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት በመምራት የእስር ማዘዣ እንዲወጣባቸው ያደርግ ይሆናል የሚለው ነው፡፡ ቀደም ብሎም የተመድ ሰብዓዊ መብት አጣሪ ቡድን የጦር ወንጀሎች መፈፀማቸውን እንዳረጋገጠ አይዘነጋም፡፡ ተጠያቂነቱ ግን አሁን ባለው ሁኔታ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርንና የአማፂያኑን መሪ ሬክ ማቻርን የማካተት እድሉ የመነመነ ይመስላል፡፡ በተለይ ዋነኞቹን ሰዎች በመጀመሪያ ተጠያቂ ማድረግ የሰላም በርን ሙሉ በሙሉ መዝጋት እንዳይሆን ስጋት ስለሚኖር፡፡
በጥቅሉ ሲታይ መቼም ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኃላ ሰላምን በባላንጣ ወገኖች ላይ ከመጫን ውጭ የተሳለ አማራጭ ባይኖርም በቀነ-ገደብ፣ በውጭ ግፊትና ተፅዕኖ የሚመጣው ስምምነት ግን ለቀውሱ ዘላቂ መድህን ስለመሆኑ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን አሁን ደቡብ ሱዳናዊያን ከምንም በላይ የሚፈልጉት የተኩሱን በአስቸኳይ መቆም እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ይህ ግን ሊሳካ የሚችለው ባላንጣዎቹ በቅን መንፈስ ስምምነት ላይ ሲደርሱ ወይም ስምምነት ላይ የማይደርሱ ከሆነ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የግጭቱ ዋነኛ ተዋናዮችን ከባድ ቁንጥጫ ሲያቀምሳቸው ብቻ ነው፡፡ እስካሁን በራሳቸው ሙሉ ተነሳሽነት፣ ባለቤትነትና ሙሉ ፍቃድ ሰላም ማውረድ የተሳናቸው ተፋላሚ ወገኖች አሁን የትኛውን መንገድ እንደሚመርጡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይታያል፡፡