ዋዜማ- የኢትዮጵያ መንግስት የብርና የውጪ ምንዛሪ ምጣኔን ገበያ መር እንዲሆን የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉን በይፋ አስታውቋል። የመንግስት የማክሮፋይናንስ ፖሊሲ ማሻሻያ ሆኖ ይፋ የተደረገው መግለጫ እንዳመለከተው “በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጪ ምንዛሪ ተመንን ማረጋገጥ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጪ ምንዛሪ መዛባት ለማስተካከል ይረዳል..” ይላል። መግለጫው ይፋ የተደረገው የአለም የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ በታቀደ ብድር ላይ ስብሰባ ለመቀመጥ በተዘጋጀበት ዋዜማ ነው። የውጪ ምንዛሪ ተመንን ለገበያ መተው አልያም ማዳከም ለታማሚው ኢኮኖሚያችን ምን በጎ አስተዋፃኦ አልያም ፈተና ይዞ ይመጣል? ስንል የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ምሁራንን አነጋግረናል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር አረጋ ሹመቴ፣ መንግሥት በውጭ ምንዛሬ እጦት እና በዕዳ ጫና ችግር ውስጥ የገባበት ጊዜ በመሆኑ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ብድር ለማግኘት ሲል የዶላርን ምንዛሬ ተመን ሊያሻሽል ይችላል ሲሉ ለዋዜማ ገልጸዋል።
በምንዛሬ ተመን መሻሻል ምክንያት የብር ዋጋ ሲወርድም፣ በኢትዮጵያ ዐብይ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጫና ይዞ መምጣቱ አይቀሬ መሆኑንም ተናግረዋል። አንድ አገር የመገበያያ ገንዘቧን ዋጋ ዝቅ የምታደርግበት ምክንያት እና ወቅት አለ የሚሉት ባለሙያው፣ ዋነኛው የዚህ ምክንያት ግን አገሪቱ የተትረፈረፈ የአገር ውስጥ ምርት እና ሸቀጥ በሚኖራት ጊዜ መሆኑን ጠበቅ አድርገው አንስተዋል።
ብዙ የአገር ውስጥ ምርት እና ሸቀጥ ክምችት በሚኖርበት ጊዜ፣ የገንዘብን ዋጋ ዝቅ ማድረግ፣ ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ብዙ ደንበኛ ለማግኘት ይረዳል ባይ ናቸው። ሆኖም ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው በዋናነት የግብርና ምርቶችን እና ማዕድናትን መሆኑን የጠቀሱት የኢኮኖሚክስ መምህሩ፣ እነዚህ ምርቶችም ወቅት ጠብቀው የሚደርሱ እና የሚሰበሰቡ እንደመሆናቸው፣ ምርቶቹ በሚደርሱበት ወቅት ጭምር ከፍተኛ ክምችት ኖሯቸው የብርን ዋጋ ለመቀነስ የሚያበቁ ምክንያቶች አለመሆናቸውን አስረድተዋል።
አንዳንድ ጊዜም ብዙ የምርት ክምችት ኖሮ እንኳን የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም አዋጭ ላይሆን እንደሚችል የገለጹት ባለሙያው፣ ወደ ውጭ የሚላከው ምርት በሌሎች አገራት በብዛት የማይመረት ከሆነ እና ብዙ ተወዳዳሪ ከሌለ ብቻ የራስን ገንዘብ የመግዛት አቅም ማዳከም አዋጭ ሊሆን እንደሚችል ለዋዜማ ነግረዋታል።
ስለሆነም የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን፣ ምግብ ነክ ሸቀጣ ሸቀጦችን፣ ማዳበሪያ እና ነዳጅን የመሳሰሉ ወሳኝ ሸቀጦችን በማስገባት በውጭ ገበያ ላይ ከፍተኛ ጥገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ የብርን ዋጋ ከዚህም በላይ እያዳከመች መሄዷ ከውጭ የሚገቡትን ሸቀጦች በውድ ዋጋ እየገዙ ለመቀጠል መስማማት እንደሆነ ባለሙያው ጠቅሰዋል።
መንግሥት ከዚህ ቀደም የብር የመግዛት አቅምን ካዳከመበት መጠን አንጻር፣ አሁንም በ20 በመቶ ወይም ከዚህ ከፍ ባለ መጠን እንዲቀንስ ቢያደርግ አይደንቀንም ያሉት ዶክተር አረጋ፣ አሁን ላይ የብዙ ሸቀጦችን ዋጋ እየወሰነ ያለው ከሕጋዊ ምንዛሬው በጣም የራቀው የትይዩ ገበያው ስለሆነ፣ የብር ዋጋ እንዲቀንስ ቢደረግ እጅግ የተጋነነ የኢኮኖሚ ጫና ላይፈጠር ይችላል ሲሉም ጠቁመዋል።
ሆኖም መንግሥት ጊዜያዊ ብድር ለማግኘት በሚል ቀላል የማይባል ቀውስ የሚያስከትል ውሳኔ መወሰን ባይኖርበት ጥሩ ነው የሚል ምክራቸውን ለግሰዋል።
ሌላኛው ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የዘርፉ ባለሙያ ክቡር ገና በበኩላቸው፣ የብርን የመገዛት አቅም ማዳከም የተሻለ ነገር ይዞ ይመጣል የሚል ዕምነት የላቸውም። በዚህ ርዐሰ-ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ በአደባባይ ሲሟገቱ የሚታወቁት ክቡር ገና፣ የብርን አቅም ማዳከም በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲኖራቸው ያደርጋል፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችም ዋጋቸው ከፍ ስለሚል የሚገቡበትን መጠን ይቀንሳል፤ በዚህም የተነሳ የመንግሥት ገቢ ከመጨመሩ ባለፈ፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችቱም ጠርቀምቀም ይላል የሚል እንደሆነ ሃቲቱን አሳጥረው ያብራራሉ።
ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች ገበያ እያገኙ ሲመጡ፣ ወደ አገር የሚገቡ የባህር ማዶ ባለሃብቶች ቁጥር ይጨምራል የሚል ዕሳቤ እንደመኖሩ፣ ከዚህ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬም አገሪቱ የዕዳ ጫናዋን ለማቃለል ያስችላታል ተብሎ እንደሚታመን አመልክተዋል። ሆኖም ይህ አካሄድ ብዙ ችግር እንዳለው ይናገራሉ። አቅሙ እንዲቀንስ በተደረገው ብር የውጭ ዕዳን ለመክፈል የበለጠ ገንዘብ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ወደ ውጪ ለሚላኩ ምርቶች ቅድሚያ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችም ዋጋቸው እንዲንር እንደሚያደርገው አንስተዋል።
አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎቻችን ከውጪ በሚገቡ ጥሬ ዕቃዎች ላይ ጥገኛ በመሆናቸው፣ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን ዋጋ መናር አቅማቸውን የበለጠ እንደሚያዳክምም ይጠቅሳሉ። የብርን ዋጋ ማዳከም ኢንቨስተሮችን ለመጠራት ያግዛል የሚባለውን ያህል፣ እንዳይመጡ ሊያርቃቸው እንደሚችልም የሚያብራሩት ክቡር፣ በየጊዜው የብር ዋጋ የሚቀንስ ከሆነ፣ የእነሱም ትርፍ እየቀነሰ ስለሚሄድ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ፍላጎታቸውን ይቀንሳል ሲሉ ገልጸዋል። ባለሙያው እንደሚሉት፣ የብርን አቅም የማዳከም ተደጋጋሚ ፍላጎት ከዚህ ቀደም የተወሰዱ ተመሳሳይ ዕርምጃዎች ውጤት አልባ ለመሆናቸው ማሳያ ነው።
የአገሪቱ ዐብይ ኢኮኖሚ የሚያድገውም ሆነ የሚረጋጋው እንዲህ ባለ ጥቂቶችን ብቻ ጠቅሞ አብዛኛውን የአገሪቱን ሕዝብ ሊያደኸይ በሚችል አማራጭ ሳይሆን፤ በትምህርት፣ በፈጠራ፣ በግብርና እና በሌሎች መሠረታዊ ዘርፎች ላይ ፖሊሲዎችን በማመቻቸት ነው በማለት ይመክራሉ።
ቻይና እ.አ.አ. በ1970ዎቹ ከፍተኛ የማምረት አቅም ስለነበራት፣ በውጭ ገበያ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የገንዘቧን አቅም በማዳከም ተጠቅማበታለች የሚሉት ክቡር ገና፣ ይሄ ግን ለኢትዮጵያ እንዴት ሊሰራ እንደሚችል አላውቅም ባይ ናቸው። ዝቅተኛ የኢንዱስትሪ ዕድገት እና የአገሪቱን ሕዝብ መመገብ የማይችል ግብርና ተይዞ፣ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም ሕዝብን የማደኽየት አካሄድ ነው ብለዋል። መጀመሪያ ለዚያ የሚያበቃንን ከፍተኛ የምርት ክምችት ለመፍጠር እንሥራ የሚሉት ባለሙያው፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቁ ችግር የጸጥታ ችግር ስለሆነ ቅድሚያ ይህን መፍታት ያስፈልጋልም ይላሉ።
ገንዘብን ማዳከም ብቻውን ችግር አይደለም የሚሉት ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዋሲሁን በላይ ደግሞ፣ በኢኮኖሚክስ አስተምህሮ ጉዳዩ ዕድልም ጭምር ነው ይላሉ። ወደ ውጭ የምንልከው ሸቀጥ መጠኑ እንዲጨምር ከማደረጉ ባለፈም፣ በዓለም ገበያም በርካሽ ዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያግዛል ሲሉም፣ ዕድል ያሉትን ሁነት ይጠቅሳሉ።
“ማንም ሸማች ርካሽ ነገርን መግዛት ይፈልጋል፤ ስለዚህም ብዙ ይገዙህና ብዙ የውጭ ምንዛሬ ታገኛለህ፤ ካልሆነማ፣ ዋንኛ የቡና አቅራቢዎች ከሆኑት ከብራዚል እና ከኮሎምቢያ ገበሬ ጋር እንዴት መወዳደር ይቻላል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
የታዳጊ አገራት የመገበያያ ገንዘብ ዋጋ ዝቅ እንዲል በማድረግ ላይ ትልቅ ሚና ያላቸው ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ)፣ በጉዳዩ ላይ የሚከተሉት ፖሊሲና የሚሰጡት ምክረ ሃሳብ ታዳጊ አገራቱ የኢኮኖሚ ቀውስና የዕዳ ጫና ውስጥ እንዲዘፈቁ ያደርጋል በሚል ከፍ ያለ ትችት ይቀርብባቸዋል።
ዶክተር አረጋ፣ እነዚህ ተቋማት ራሳቸውም አትራፊ መሆን ይፈልጋሉ፤ ስለዚህም የብር የመግዛት አቅም ቢቀንስ እነሱም ተጠቃሚ ናቸው ይላሉ። ከተቋማቱ የሚገኘው ብድር ምንጩ ከአሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ለራሳቸው የሚጠቅም ዕርምጃ እንዲወሰድ ቢፈልጉ የሚደንቅ አይደለም ባይ ናቸው።
ክቡር ገናም በበኩላቸው፣ የአበዳሪዎች ፍላጎት የውጭ ምንዛሬ መጠናችን ጨምሮ እዳቸውን እንድንከፍላቸው ነው ሲሉ ይገልጻሉ። ይህን ተከትሎም የገንዘብ ዋጋ እንዲዳከም ተደርጎ ከተቋማቱ ብድር ቢገኝ፣ የተገኘው ገንዘብ በአገሪቱ ልማት ላይ ያን ያህል ተጽዕኖ አይፈጠርም የሚሉት ክቡር፤ ለዚህም በምክንያትነት የሚያነሱት፣ ከሚገኘው ብድር አብዛኛው ባለፈው ዓመት ላልተከፈለ ዕዳ የመዋሉን አይቀሬነት ነው።
ዋሲሁን በላይ በበኩላቸው፣ አገራት እስከሆነ ልክ ድረስ ብድር እና ዕርዳታቸው ስለሚያስፈልገን የሚሉንን እየተለሳለስን መቀጠል ይኖርብናል ባይ ናቸው። ተቋማቱ ለአባሎቻቸው የሚመች የመዋዕለ-ንዋይ ሜዳ መፍጠር ይፈልጋሉ፤ ስለዚህም ካንተ የሚጠበቀው የሚመክሩህ ምክር የአገር ውስጥ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለውን እየለካህ መተግበር ነውም ሲሉ ያብራራሉ።
የብር የመግዛት ዋጋ መዳከሙ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ዋጋ ስለሚጨምር ሸማቾች የአገር ውስጥ ምርቶችን ተጠቃሚነት ይጨምራል የሚል መከራከሪያም ሲነሳ ይደመጣል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በብዛት የምታስገባቸው እንደ ማዳበሪያ፣ ነዳጅ፣ ዘይት እና ሌሎች የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ዋጋቸው ቢጨምር እንኳን ለእነዚህ ምርቶች የሚኖረው ፍላጎት ሊቀንስ እንደማይችልም ይጠቀሳል።
የገንዘብ ቅያሬን አስመልክቶ ሦስት ዓይነት ስሌቶች ያሉ ሲሆን፤ የመጀመሪያውና ደርግ ሲጠቀምበት የነበረው ገታራ የገንዘብ ቅያሬ ስሌት ነው። ከኢሕአዴግ ጀምሮ እስካሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ከፊል ተንሳፋፊ የቅያሬ ስሌት ደግሞ ሁለተኛው ሲሆን፤ ገበያ-መር የሆነው የቅያሬ ስልት ደግሞ ሦስተኛው መሆኑን የምጣኔ ሃብት መምህራኑ ያስረዳሉ።
ከዶላር ጋር አቻ የነበረው የኢትዮጵያ ብር፣ ቀስ በቀስ ዋጋው እየቀነሰ መጥቶ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1984 ዓ.ም. በመንግሥት በተወሰደ እርምጃ የብር ዋጋ በ142 በመቶ እንዲቀንስ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም በ2 ብር ከ7 ሳንቲም ይመነዘር የነበረውን አንድ ዶላር፣ በ5 ብር እንዲገዛ አድርጓል። ከዚህም በመቀጠል በ17 በመቶ ዋጋው እንዲቀንስ ካደረገው የ2002 ዓ.ም. ውሳኔ በኋላ፣ ከጥር 2012 እስከ ጥር 2015 ዓ.ም. ባሉት ሦስት ዓመታት ብቻ፣ በአዝጋሚ ሁኔታ በተደረገ የምንዛሬ ተመን ጭማሪ፣ የብር ዋጋ በ40 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉን ጥናቶች ያሳያሉ። [ዋዜማ]
የአዘጋጁ ማስታወሻ– ምሁራኑን ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ መንግስት የውጪ ምንዛሪ ተመንን ገበያ መር ለማድረግ ከመወሰኑ ጥቂት አስቀድሞ መሆኑን አንባብያን እንድትረዱልን እንጠይቃለን