ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ዜጎችን ክፉኛ እየፈተነ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመፍታት መንግስትን ሊያግዝ የሚችል የአቅርቦትና የዋጋ ማረጋጊያ ቦርድ በጊዜያዊነት ሊቋቋም እንደሚገባ አሳሰበ።
ማህበሩ ላለፉት ስድስት ወራት የዋጋ ግሽበት መዋቅራዊ ተግዳሮቶችና የፖሊሲ አማራጮች በሚል ርዕስ ያካሄደውን ጥናት ትናንት ይፋ ባደረገበት ጊዜ የዋጋ ግሽበት የህብረተሰቡን ህልውና እየተፈታተነ እንደሚገኝ በመግለፅ በጥናቱ ግሽበቱን አባብሰዋል ያላቸውን ምክንያቶች አስቀምጧል ። ከእነዚህ መካከል የነፍስ ወከፍ የምግብ እህሎች ምርት መቀነስ ለዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል ብሏል።
የግብርና የኢንዱስትሪ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፎች ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት አንጻር ሲታዩ ግብርና በ1990ዎቹ ከነበረበት 60 ከመቶ አሁን በግማሽ ሲቀንስ ኢንዱስትሪ ከ10 በመቶ ወደ 30 በመቶ አገልግሎት ከ30 ወደ 40 በመቶ ጨምሯል።
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የኢንደስትሪና የአገልግሎት ዘርፍ ማደግ የዋጋ ግሽበትን ማባባሱን በጥናቱ ማረጋገጡን ማህበሩ አመልክቷል ።
ኢትዮጵያ ለቁጠባ ዝቅተኛ ወለድ ከሚሰጡ 10 የአፍሪካ አገራት 8ኛ መሆኗን የሚገልጸው ጥናቱ ለተቀማጭ ገንዘብ የሚሰጠው ወለድ አነስተኛ መሆን በኢኮኖሚው ውስጥ የገንዘብ ፍሰትን በመጨመር የዋጋ ግሽበቱን አባብሷል ብሏል።
ማህበሩ በጥናቱ ከጠቆማቸው የመፍትሔ እርምጃዎች መካከል ነጻ የአቅርቦትና የዋጋ ማረጋጊያ ቦርድ በጊዜያዊነት ማቋቋም አንዱ ነው ።
ቦርዱ የአገር ምርትና የገቢ ንግድ አቅርቦት አስተዳደር ሚዛን የማስጠበቅ ፣ የዋጋ ግሽበትን የሚቀንስበት ግብ ማስቀመጥና የመከታተል ፣ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል ቅንጅት መፍጠር እንዲሁም ግሽበቱ ይበልጥ ለሚጎዳቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደረጉ ድጋፎችን የመለየት ሚናዎች ይኖረዋል ሲል ጥናቱ ለይቷል።
ለተቀማጭ የሚሰጠው ወለድና ለብድር የሚጠየቀው ገንዘብ የዋጋ ግሽበቱን ያገናዘበ እንዲሆን ማድረግ እንዲሁም በምግብ ፍጆታ ምርቶች ላይ ብቻ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘውን ፍራንኮ ቫሉታ ወይም የውጭ ምንዛሪ ያላቸው ዜጎች ከውጭ ምርቶች የሚያስገቡበትን አሰራር በግብርናና በግንባታ ግብአቶች በመድኃኒት በመሳሰሉት ላይም ተግባራዊ ማድረግ ጥናቱ ካስቀመጣቸው የመፍትሔ እርምጃዎች የሚጠቀሱ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ የአቅርቦት ሰንሰለቱን በማስተጓጐል የዋጋ ግሽበቱን አባብሰዋል ያላቸውን የአገር ውስጥ ግጭቶች ማረጋጋት ቢያንስ የዋጋ መረጋጋት ስለሚፈጥር ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ብሏል። [ዋዜማ ራዲዮ]