ይሄ የማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ድሮ ድሮ ከመድረክ ትዕይንት ነጻ ሲሆን ነበር ለስብሰባ የሚያገለግለው፡፡ አሁን አሁን ከስብሰባ ነጻ ሲሆን ነው ቴአተር የሚያሳየው፡፡ ባለፉት አምስት ቀናት (አርብ፣ ቅዳሜ፣ሰኞና ማክሰኞ) የመሬት ሊዝ ድራማ ሲተወንበት ዉሎ አምሽቷል፡፡ ያውም ባለ ብዙ ገቢር ድራማ፡፡
የታሸጉ የሊዝ ካኪ ፖስታዎች በሕዝብ ፊት የሚቀደዱት ከዚህ አዳራሽ ነው፡፡ እነዚህ መሬት የጠማቸው ባለሀብቶች ደግሞ ሲያናድዱ፡፡ ቢያንስ የሚከሰክሱት ብር አጓጉቷቸው እንኳ በአዳራሹ አይታደሙም እንዴ? ጥቂት የነርሱ ደላሎችና ወኪሎች ካልሆኑ በስተቀር አዳራሹ ወና ነበር፡፡ እንዲያውም የመድረኩ አስተባባሪዎች ተደራሲ ሲጠፋ ትዕይንቱን ወደ ማዘጋጃ ቤት ‹‹ሎቢ›› አወረዱት አሉ፡፡
ሊዝ የወጣው ከአስሩ ክፍለ ከተሞች በአምስቱ ላይ ብቻ ነበር፡፡ ወትሮ በሊዝ ቦታ አቅራቢነቱ በይበልጥ የሚታወቀው ቦሌ ክፍለ ከተማ ለዚህ ዙር አንድም መሬት አላዋጣም፡፡ ቸብችቦ ሳይጨርሰው አይቀርም መሰለኝ፡፡ አቃቂ ቃሊቲ 47 ቦታዎችን፣ ኮልፌ ቀራንዮ 24 ቦታዎችን፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ 55 ቦታዎችን፣ የካ 15 ቦታዎችን፣ አራዳ 2 ቦታዎችን ለጨረታው የመስዋእት በግ አድርገው አቅርበዋል፡፡ ከነዚህ ዉስጥ የዲታዎችን ቀልብ የሳቡት 4ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት ጋር የቀረቡ ሁለት ቦታዎችና ሳርቤት ገብርኤል የቀረቡት 6 ቦታዎች ናቸው፡፡ በተለይ የሳርቤት ገብርኤሎቹ ቦታዎች በሊዝ ታሪክ ክብረወሰን ሰብረዋል፡፡
ከምስራቅ በር እንጀምር፡፡ አርብ የካቲት 18 የተከፈቱት ፖስታዎች የአቃቂ ቃሊቲ ስለነበሩ መካከለኛና ዝቅተኛ ሀብታሞች ተሳትፎ የሚያደርጉበት ጨረታ ነው ተብሎ ዝቅ ያለ ግምት ተሰጥቶት ነበር፡፡ የአዳራሹ ድባብም ይህንኑ የሚያሳይ ይመስላል፡፡ 50 የሚሆኑ ታዳሚዎች እንኳን አልነበሩም፡፡ ለነዚህ 47 ቦታዎች የቀረቡት የተጫራቾች ብዛት ግን ከ900 ይልቃል፡፡ በዚህ ክፍለከተማ የቀረበው አማካይ የጨረታ ዋጋ 15ሺ ብር ሲሆን በላይ አብ ሞተርስ አካባቢ ወደ ቱሉ ዲምቱ በሚሰነጠቀው መንገድ ኮሮኮንች ገባ ብሎ ለሚገኝ አንድ 244 ካሬ ቦታ የመኖርያ ስፍራ አቶ አሸናፊ የተባሉ ግለሰብ 25 ሺ ብር ሰጥተዋል፡፡ እውነትም አሸናፊ፡፡ በሌላ ቋንቋ እኚህ ሰው (አቶ አሸናፊ) አቃቂ ቃሊቲ ሄደው 244 ካሬ ባዶ ቦታ ያውም ሰፈር ዉስጥ 6.1 ሚሊዮን ብር ከፍለው ገዙ እንደማለት ነው፡፡
ቅዳሜ የካቲት 19 የየካ ጨረታ የተከፈተ ሲሆን በዚህ ክፍለከተማ ልዩ ስሙ አያት ተብሎ በሚጠራውና ወደ ጣፎ በሚወስድ አስፋልት ገባ ብሎ ባለ ሰፈር ለቀረቡ 6 ቅይጥ ቦታዎች፣ ለእያንዳንዳቸው በካሬ ከ21ሺ እስከ 23ሺ ብር ቀርቦባቸዋል፡፡ የሚገርመው ከነዚህ ዉስጥ የተወሰኑት ቦታዎች በ17ኛውና በ18ኛው ዙር ወጥተው ከ15ሺ ብር በታች ቀርቦባቸው አሸናፊዎቹ ባልታወቀ ምክንያት ሳይወስዷቸው የቀሩ መሆናቸው ነው፡፡ የቦታዎቹ ስፋት ከ400-500 ካሬ የሚገመቱ ናቸው፡፡
በኮልፌ ቤቴል አካባቢ ለመኖርያ ለቀረቡ ባዶ ቦታዎች አስገራሚ ዋጋ ቀርቦባቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ከ20 ሺ ብር በላይ መሆናቸው ሳያንስ ወይዘሮ አደሰች አብዱ ካልደፈረሰ አይጠራም በማለት ይመስላል ለ200 ካሬ ሜትር ቦታ 30 ሺ 100 ብር አቅርበው ተወዳዳሪዉን ኩም አድርገውታል፡፡
እስቲ የድሀ ወሬ ትተን ወደ ገብርኤል እንሂድ፡፡ ቦታው የዋዛ አይደለም፡፡ ድሮም ሳርቤት ገብርኤልን የሚደፍር መካከለኛ ሐብታም የለም፡፡ ያ ሰፈር የሞጃ ሰፈር ነው፡፡ ከድሮም፡፡ ገብርኤል ቤተክርስቲያንን አልፈን፣ የኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ‹‹ላፍቶ›› መዝናኛን አልፈን፣ የሼክ አላሙዲንን ሎሊ ነው ኖኒ ሕንጻን አልፈን፣ የአፍሪካ ሕብረት ዋና ፀሐፊ ዋና መኖርያ ቤት ሰፈር ስንደርስ ከጀርባ አንድ ቆሻሻ ገንዳ የሚቀመጥበት ሜዳ እናገኛለን፡፡ ይህ ስፍራ ከ10 ሚሊዮን በታች ዱዲ በማይቀንሱ ቤቶች የተከበበ ሲሆን እያንዳንዳቸው ከ 400 ካሬ ያላነሱ 6 ቦታዎች ወጥተውታል፡፡ ከጨረታው በፊት ወደዚህ ስፍራ ያመራችው የዚህ ሪፖርት አቅራቢ ቦታውን ለማየት ይመጡ በነበሩ ባለሀብቶችና በያዟቸው መኪናዎች መደመሟን በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ ትወዳለች፡፡ ብዙዎቹ የ2015 ሞዴል እጅግ ቅንጡ መኪኖችን ይዘው፣ በአጃቢ የመጡ ባለሀብቶች ነበሩ፡፡ ማጋነን ካልሆነ ሼክ አላሙዲ ሴት ልጃቸውን ለመዳር ሽማግሌ ወደዚህ ሰፈር ልከው ነው የሚመስለው እንጂ አንድ የቆሻሻ ገንዳ የሚያርፍበት መናኛ ቦታ ለማየት አይመስልም ነበር፡፡ የተፈራው ደርሷል፡፡
ማክሰኞ የካቲት 22 ቀትር ላይ ይፋ በተደረገው የጨረታ ዉጤት የቦታ ኮድ 11525 የሚል ስም የተሰጣት፣ 482 ካሬ ለሆነች ብጣሽ መሬት፣ 62ሺ ብር በካሬ አቀረቡ፡፡ እውነት ለመናገር የአሸናፊውን ስም በቃሌ ይዤው የነበረ ቢሆንም ለቦታው ያቀረቡትን ዋጋ ስሰማ ደንግጬ ስማቸውን እንድረሳ ሆኛለሁ፡፡ አንባቢ ድንጋጤዬ ምክንያታዊ ስለመሆኑ ለማስረዳት እኚህ ሰው 482 ካሬ ባዶ ቦታን የገዙት በ29 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ለመግለጽ እሻለሁ፡፡ እኚህ ሰው ቦታው ላይ ቤት ሰርተው ለሚቀጥሉት 40 ዓመታት በየወሩ 60ሺ ብር ለመክፈል እንደተስማሙ ለመግለጽ እሻለሁ፡፡ ይህ ታዲያ የወለድ ሂሳብ ሳይጨምር ማለት ነው፡፡ይህ ቦታ ከ99 ዓመት በኋላ የርሳቸው አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡
የኚህ ባለሐብት ዋጋ እብደት ነው ተብሎ ታዳሚው መንሾኳሾክ ከመጀመሩ የርሳቸው ጎረቤት ለመሆን የገቡ ዋጋዎች መሰማት ተጀመረ፡፡ የተቀሩት አምስቱም ቦታዎች ዋጋዎች ከ30 ሺህ በላይ ሲሆኑ እርሳቸው አጠገብ ለሚገኝ 309 ካሬ ኒዕማ ሽፋ የተባሉ ወይዘሮ 52ሺ ብር አቅርበዋል፡፡ ወይዘሮዋ 309 ካሬ ባዶ ቦታን በ16 ሚሊዮን ብር ለመግዛት ቃል ገቡ እንደማለት ነው ጎበዝ፡፡ መኪያ ሬድዋን የተባሉ ሴት 52,350 ብር በማቅረብ በወይዘሮ ኒዕማ በጥቂት መቶ ብሮች ተቀድመው ጥሩ 2ኛ ሆነው ጨረታውን ጨርሰዋል፡፡
19ኛው ዙር ጨረታ በጥቅሉ ሲዳሰስ የከተማዋ ባለሐብቶች ገንዘባቸውን መለስተኛ ኢንደስትሪ ላይ ከማዋል ይልቅ መሬት ላይ ማዋል አዋጪ ሆኖ እንደታያቸው የሚያመላክት ይመስላል፡፡ የአገሪቷ ሞጃዎች የገንዘብ አመጣጥ ጤና የራቀው እንደሆነ መመስከርም ይችላል፡፡