ዕድሜ ለፈረንሳዊው ፍራንሲስ ፋልሴቶ ይሁንና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን በሚባሉት 50ዎቹ እና 60ዎቹ የተደረሱ ዘፈኖች የውጭ ሀገር ሙዚቀኞችን ቀልብ መቆጣጠር ከጀመሩ ቆዩ። የኢትዮጵያን ሙዚቃ በመጫወት ዝናን ያተረፉ የውጭ ባንዶችም ቁጥራቸው ከቀን ወደ ቀን ይጨምር ይዟል።
ሁሉም ባንዶች ወይ ሙሉ በሙሉ በውጭ ዜጎች የተዋቀሩ ናቸው አሊያም ኢትዮጵያውያንን ለዓመል ያህል በመሀላቸው ጣል ያደርጋሉ። መቀመጫቸውም ሆነ ዋነኛ የሙዚቃ መድረካቸው በውጭ ሀገር ነው። ጃዝማሪስ ግን ይለያል።
በኢትዮጵያውያን እና ጀርመናውያን ጥምረት በሚሊኒየሙ መባቻ የተመሰረተው ጃዝማሪስ በውስጡ እንዳሉት ሙዚቀኞች ስያሜውንም ያገኘው ፈረንጅኛውንና ሀገርኛውን በመቀላቀል ነው። ጃዝን እና አዝማሪን። የእነ መሐሙድ አህመድ፣ ግርማ በየነ፣ ሙለቀን መለስን እና የሌሎች ተወዳጅ ድምጻውያንን ዘፈኖች በጃዝ እና ሮክ ስልት በተለየ የአጨዋወት ዘዬ የሚያቀርብ ነው።
የባንዱ አባላት ከ”ጉራማይሌ” እስከ “ጋይስ ባር” ባሉ የአዲስ አበባ የምሽት መዝናኛዎች ለዓመታት የሙዚቃ አፍቃሪዎችን ያዝናኑ ናቸው። መልካቸውና ስማቸውም ለብዙ ሙዚቃ ወዳድ እንግዳ አይደለም።
በዘመናዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃ እንደ ፈርጥ የሚታየው ቤዚስቱ ሄኖክ ተመስገን አንዱ የቡድኑ አባል ነው። በአዲስ አኩስቲክ ፕሮጀክትና በሌሎችም ባንዶች ብቃቱን እያሳየ ያለው ወጣቱ የድራም አናጋሪ ናትናኤል ተሰማ ሌላኛው ነው። ሁለቱ ጀርመናውያን ኦላፍ ቦኤልሰን እና ዮርግ ፋዬ አልቶ ሳክስ እና ኤሌክትሪክ ጊታር ይጫወታሉ። ዮርግ ከኢትዮጵያዊቷ ሙኒት መስፍን ጋር ባወጣቸው ሁለት አልበሞች በይበልጥ ይታወቃል።
እኒህ ድንቅ የሙዚቃ ተጫዋቾች የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ካዛንቺስ እንደራሴ አካባቢ በሚገኘው “ጋይስ ባር” የተጫወቷቸው ሙዚቃዎች እንደሌላው ጊዜ ከምሽት ታዳሚ ጆሮ ደርሰው ብቻ አልቀሩም። ይልቅስ በድምፅ ባለሙያዎች ልቅም ተደርገው ተቀድተው ነበር። የመድረክ ቅጂው ውጤት በእኛ ሀገር እምብዛም ባልተለመደ መልኩ በዲጂታል አልበም መልክ ለሙዚቃ አፍቃሪያን ቀርቧል።
ባለፈው ወር የተለቀቀው ይኸው አልበም 10 ሙዚቃዎችን ይዟል። የመሐሙድ “በምን ሰበብ ልጥላሽ”፣ “መቼ ነው” እና “አይኖቼ ተራቡ” እንደዚሁም የግርማ በየነ “እኔ ነኝ ባይ ማነሽ” እና “ፍቅር እንደ ክራር” በአልበሙ ውስጥ ተካትተዋል። “ሙዚቃዊ ስልት”፣ “ማዶ”፣ “የፈረንሳይ ጀልባ”፣ “የካቲት” እና “አልማዝ የሀረሯ” የሌሎቹ ሙዚቃዎች ስያሜዎች ናቸው።
አልበሙን በ10 ዮሮ አሊያም በ11.17 ዶላር በኦንላይን መግዛት የሚቻል ሲሆን በቀጥታ ማዳመጥም ይቻላል። እነሆ ማስፈንጠሪያው https://jazzmaris.bandcamp.com/releases