በሀገሪቱ በገበያ ላይ እየቀረበ ካለው ሲጋራ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር የገባ ነው። ከአራት አመት በፊት 197 በመቶ ግብር የተጣለበት ብሄራዊ ትንባሆ ሰሞኑን ደግም 150 ፐርሰንት ተጨማሪ ታክስ ወድቆበታል። ፋብሪካው ህልውናዬ አደጋ ላይ ወድቋል እያለ ነው። መንግስት የማህበረሰብ ጤናን ለመጠበቅ በሚል ያደረገው ተደራራቢ ግብር ለህገወጥ ገበያው መስፋፋት አስተዋፅዖ አድርጓል። ዋዜማ የሚመለከታቸውን አነጋግራለች፣ አንብቡት
ዋዜማ- የኢትዮጵያ ብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት፣ በ2012 ዓ.ም በምርቶቹ ላይ የ197 በመቶ ኤክሳይስ ግብር ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ፣ በየዓመቱ ኪሳራ እያስመዘገበ መሆኑን ገልጿል። በቅርቡ ደግሞ መንግሥት በድጋሚ 150 በመቶ ግብር በትምባሆ ምርቶች ላይ መጣሉን ተከትሎ የገበያ ድርሻው የበለጠ ጫና ውስጥ መግባቱን ዋዜማ ተረድታለች። ጃፓን ቶባኮ ኢንተርናሽናል (ጄ ቲ አይ) የተሰኘው የንግድ ድርጅት፣ በ2011ዓ.ም የድርጅቱን 71 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ገዝቶ ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ፣ ዓመታዊ ምርቱ ከ5 ቢሊዮን ነጠላ የሲጋራ ምርት በልጦ ነበር። ሆኖም በ2012ዓ.ም መንግሥት በጣለው የ197 በመቶ የኤክሳይስ ግብር ምክንያት ምርቱ ወደ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዝቅ ማለቱን ሰምተናል። ይህን ተከትሎም ላለፉት አራት ዓመታት የድርጅቱ ዓመታዊ የምርት መጠን ቀድሞ ከነበረበት በእጥፍ ቀንሶ፣ ከ2 እስከ 3 ቢሊዮን ነጠላ ሲጋራ ዝቅ ብሏል። ድርጅቱ በበኩሉ፣ በቅርቡ የተጣለው ተጨማሪ የ150 በመቶ ግብር ደግሞ ዓመታዊ የምርት መጠኔን ከዚህም የባሰ ሊቀንሰው ይችላል ባይ ነው።
መንግሥት፣ የማኅበረሰቡን ጤና ከመጠበቅ አኳያ የአጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ በሚል በትምባሆ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የግብር ጭማሪ ቢያደርግም፣ በዚያው ልክ በኮንትሮባንድ የሚገቡ የሲጋራ ምርቶች በከፍተኛ መጠን መጨመራቸውን፣ የድርጅቱ የኮርፖሬት ጉዳዮች እና የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ያየህይራድ አባተ ለዋዜማ ተናግረዋል። በኮንትሮባንድ የሚገቡ ሲጋራዎች ዋና መነሻቸው የተባበሩት አረብ ኤሜሬት እና የመን ሲሆን፣ የሚገቡትም በሶማሌ ላንድ እና ጅቡቲ በኩል መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች።
በኮንትሮባንድ የሚገቡት የሲጋራ ምርቶች፣ በቅርቡ ከተደረገው የግብር ጫማሪ በፊት በአዲስ አበባ ከ16 እስከ 20 በመቶ የገበያ ድርሻ ሲኖራቸው፤ በምዕራብ ኢትዮጵያ እስከ 19 በመቶ፣ በምስራቁ ክፍል ደግሞ እስከ 98 በመቶ በመድረስ በአገር አቀፍ ደረጃ 51 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዳላቸው ዋዜማ ሰምታለች። በቅርቡ የተጣለውን ተጨማሪ የግብር መጠን ተከትሎ ደግሞ፣ የኮንትሮባንድ ሲጋራው የገበያ ድርሻ እስካሁን ከነበረበት 51 በመቶ ከፍ ብሎ ከ60 በመቶ መብለጡ እንደማይቀር ዳይሬክተሩ ለዋዜማ ተናግረዋል።
በ2011 የኮንትሮባንድ ሲጋራ ገበያው ድርሻ 35 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በዓመቱ (2012) የተጣለውን ግብር ተከትሎ በህገወጥ የሚገባው እና በርካሽ ዋጋ የሚሸጠው ሲጋራ የገበያ ድርሻው 65 በመቶ ሊደርስ ችሏል። በኮንትሮባንድ የሚገቡ የትምባሆ ዓይነቶች የጤና ማስጠንቀቂያ የሌላቸው በመሆናቸው፣ የጤና ማስጠንቀቂያ የሌለው እና ግብር ያልተከፈለበት ትምባሆ እንዳይሸጥ የወጣውን የአገሪቱን ሕግ የጣሱ መሆናቸውንም ተረድተናል።
መንግሥት በቅርቡ የጣለውን የ150 በመቶ ተጨማሪ ግብር ተከትሎ፣ ድርጅቱ ማከፋፈያ ዋጋውን በአማካኝ በፓኮ እስከ 13 ብር ድረስ ጨምሯል። ይህን ተከትሎ በዋና ከተማዋ በቸርቻሪዎች ዘንድ የሚሸጡ የሲጋራ ምርቶች በአንድ ወር ውስጥ በፓኮ እስከ 50 ብር ጭማሪ ማድርጋቸውንም ዋዜማ ባደረገችው የገበያ ዳሰሳ ተረድታለች። ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ የተጣለው ግብር የኮንትሮባንዱን ንግድ እንዲባባስ ያደረገው፣ ጭማሪው የተጠና ባለመሆኑ ነው። በ2012 የተጣለው የ197 በመቶ ግብር የኮንትሮባንድ ንግዱ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ እንዲኖረው ከማድረግ በዘለለ፣ የአጫሾችን ቁጥር በመቀነስ መፍትሄ አለማስገኘቱን ገልጸዋል። ድርጅቱ፣ በምርቶቹ ላይ ሁለት ጊዜ የተጣለበት ከፍተኛ ግብር የገበያ ድርሻው እንዲያሽቆለቁል እንዳደረገው ይናገራል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻም፣ ድርጅቱ ሁሌ በኪሳራ ውስጥ ይቀጥላል ብሎ መተማመን አይቻልም።
ከዚህ የኮንትሮባንድ ንግድ በተጨማሪ ድርጅቱ፣ በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ የምርት ግብዓቱ መቃጠሉ ችግር ውስጥ እንደከተተው ይናገራል። ድርጅቱ የጥሬ ዕቃ የሚሆን የትምባሆ ቅጠል ምርት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንዲሁም በደቡብ ክልል ያለው ሲሆን፣ በአማራ ክልል ሸዋሮቢት፣ ጀውሃ እና አጣዬ አካባቢ ያለው በጸጥታ ችግር ምክንያት በታጣቂዎች ተቃጥሎበታል። በዚህም አሁን ላይ 50 በመቶ ገደማ ጥሬ ዕቃውን ከውጭ እያስመጣ እንደሆነ ገልጿል። የጃፓኑ ኩባንያ ድርጅቱ ከገዛው በኋላ ገበሬዎችን በመደገፍ 90 በመቶ በላይ ጥሬ ዕቃውን ከአገር ውስጥ ማግኘት ችሎ እንደነበር ዳይሬክተሩ ነግረውናል። ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ ገደማውን ጥሬ ዕቃ ከአማራ ክልል ነበር የሚያገኘው።
ድርጅቱ ከሚያመርታቸው የሲጋራ ዓይነቶች ኒያላ የተሰኘው ምርቱ በገበያ ድርሻው ቀዳሚው ሲሆን፣ የሽያጭ ድርሻውም እስከ 94 በመቶ ይደርሳል ተብሏል። ኒያላ ዊንስተን እና ኒያላ ፕሪሚየም ሌሎቹ ምርቶቹ ሲሆኑ፣ ኤል ዲ የተሰኘ የሲጋራ ዓይነትም በአራተኛነት ያመርታል። ተስከር የሚባለውን የሲጋራ ምርቱን ደግሞ ወደ ደቡብ ሱዳን እንደሚልክ ሰምተናል። ድርጅቱ፣ ‘ምቹ ሁኔታዎች ከተፈጠሩልኝ፣ ከአገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪ የጎረቤት አገራት እና የቀጠናው ገበያ ላይ ትልቅ ተስፋ አለኝ’ም ብሎናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት የተቋቋመው፣ ከ75 ዓመታት በፊት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ ነበር። ድርጅቱ ለረዥም ጊዜ በመንግሥት ባ ለቤትነት ሥር ከቆየ በኋላ፣ 29 በመቶ ድርሻው ለየመኑ ሼባ ኢንቨትመንት ግሩፕ ተሸጠ። በ2011 ደግሞ፣ ቀሪው 71 በመቶ ድርሻው፣ በዓለም ላይ በትምባሆ ምርቶቹ ታዋቂ ለሆነው ጃፓን ቶባኮ ኢንተርናሽናል ኩባንያ በ1 ቢሊዮን ዶላር በመሸጡ፣ አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ከድርጅቱ ባለቤትነት ሙሉ በሙሉ ሊወጣ ችሏል። የጃፓን መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ባለድርሻ በሆነው ጃፓን ቶባኮ ኢንተርናሽናል ውስጥ የ33 በመቶ ድርሻ አለው። [ዋዜማ]