ዋዜማ ራዲዮ- የ97 ታሪካዊ ምርጫ ሊካሄድ ዋዜማ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ (አዲሱ የኮምንኬሽን ጉዳዮች ሚንስትር አልያም የመንግስት ቃል አቀባይ) ሕንድ ሐይድራባድ ማስተርሳቸውን ለመጨረስ ትግል ላይ ነበሩ፡፡ ወዲያው ኦሮሚያ ኢንፎርሜሽን ቢሮ ትንሽዬ ልማታዊ ጋዜጠኛ ሆኑ፡፡ በምርጫው ማግስት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሌክቸረር ተባሉ፡፡ ነገሪ የጋዜጠኝነት ትምህት ቤት ብቅ ማለት የጀመሩት ግን በጣም ዘግይተው 3ኛ ዲግሪያቸውን መያዝ ከጀመሩ ወዲህ ነው፡፡
የያኔው ገናናው የጋዜጠኝነት ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት አቶ ነገሪ ጭራሽ አያውቁትም፡፡ በኖርዌይ መንግሥት ልዩ ድጋፍ ይደረግለት የነበረውን ይህን ጠንካራ ተቋም አንድም ጊዜም አልመሩትም፡፡ ከሰሀራ በታች ስመጥር “ስኩል ኦፍ ጆርናሊዝም” ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን፣ በላቁ ዓለም አቀፍ ፕሮፌሰሮችና በዘመናዊ መሳሪያዎች ተደራጅቶ የነበረውን ትምህርት ቤት ዝር አላሉበትም፡፡ መጀመርያ ዶክተር አሰፋ፣ ቀጥሎ ዶክተር አብይ ፎርድ በኋላም ዶክተር ገብረመድህን ስምኦን ናቸው ይህን የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ለመምራት የሞከሩት፡፡
የዶክተር ገብረመድኅንን ወደ ትምህርት ቤቱ በኃላፊነት መምጣት ፖለቲካዊ ትርጓሜ ነበረው፡፡ ያኔ አማጺዎችን ትረዳለች ተብላ መለስ ዜናዊ ጥርስ ዉስጥ የገባችው ኖርዌይ የተጋነነ ድጋፍ ለጋዜጠኝነት ትምርት ቤቱ ማድረጓ በነ አቶ በረከት ስምኦን እምብዛምም አልተወደደላትም፡፡ ኖርዌይም ቢሆን ነገሩ አላማራትም፡፡ በሂደት ድጋፉ እየተቀዛቀዘ፣ ክሮነሩ እያጠረ፣ ፖለቲካውም እየተበላሸ መጣ፡፡ ኖርዌይጂያንስ ጓዛቸውን ጠቅልለው በገቡበት ፍጥነት ሾልከው ወጡ፡፡
የትህርት ቤቱ ዝናም የዶክተር ገብረመድህንን መምጣት ተከትሎ አከተመ፡፡ ዶክተሩ በነበራቸው ቆይታ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍሉን ከማገልገል የበለጠ ኢህአዴግን አገልግለዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም ይላሉ በቅርብ የሚያውቋቸው፡፡ ለፖርቲው የነበራቸው ታማኝነት የበዛ ነበር ይባላል፡፡ እንዲያውም በአካዳሚያዊ አቅማቸው ደከም ያሉ፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ይሠሩ የነበሩ ተማሪዎችን የማይገባቸውን ዉጤት ሸጎጥ እያደረጉ ይታደጓቸው እንደነበር ዛሬም ድረስ ይታማሉ፣ ዶክተር ገብረመድኅን፡፡
ዶክተር ገብሬ የኢህአዴግ ባለዉለታም ናቸው፡፡ ምሁር በተራበበት በ97ቱ ምርጫ ፓርቲውን ወክለው በቦሌ ክፍለ ከተማ ከቅንጅት ጋር ትንቅንቅ የገጠሙት ሰው ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ሳይሆኑ ዶክተር ገብረመድህን ስምኦን ናቸው፡፡ እርግጥ ነው ዶክተር ገብረመድህን እንደ ዶክተር ነገሪ ሁሉ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን በቦርድ አባልነት አገልግለዋል፡፡ አሳሪ የሚዲያ ህጎችን በማርቀቅም ተሳትፈዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ማኅበር ሊቀመንበርም ነበሩ፡፡ ጥሩ የቋንቋ ችሎታና ቦታው የሚፈልገውን ቅልጥፍና ያሟሉ ለፓርቲው የታመኑ፣ ከፍ ያለ የማግባባት ችሎታ ያላቸው እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡
ታዲያ ዶክተር ገብረመድህን እያሉ እንዴት ዶክተር ነገሪ ሌንጮ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ኾነው ሊሾሙ ቻሉ?
ይህ ነው የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤቱን ተማሪዎች ላለፉት ሳምንታት ሲያነጋገረ የቆየ ጉዳይ፡፡ የዋዜማ ዘጋቢ የአንዳንዶቹን ተማሪዎች ሂስና ስሜት በስልክ ጠይቃ በወፍ በረር እንደሚከተለው ቃኝታዋለች፡፡
በየመድረኩ በሚያቀርቧቸው የጥናት ወረቀቶች አዘውትረው የልማታዊ ጋዜጠኝነት ፍልስፍናን የሚሰብኩት ዶክተር ነገሪ፤ በ3ኛው ዓለም ጋዜጠኝነትን ለልማትና መልካም አስተዳደር ማሳለጫነት ማዋል ይቻላል የሚል ጽኑ እምነት አላቸው፡፡ የልማታዊ ጋዜጠኝነት ፍልስፍናን ያቀነቅናሉ፡፡ ምናልባት ይህ አስተሳሰባቸው ሳይሆን አይቀርም ለቦታው ያስመረጣቸው ይላሉ የዋዜማ ዘጋቢ ያነጋገረቻቸው የቀድሞ ተማሪዎቻቸው፡፡
ዶክተር ነገሪ በማስተማርም በማስተዳደርም፣ በቋንቋም ደከም ያለ አቅም እንዳላቸው የሚያምኑት በርከት ያሉ ተማሪዎቻቸው ሁለት ነገሮችን በመልካም ጎኑ ያነሱላቸዋል፡፡ ቀጠሮ አክባሪነታቸውና የተዋጣለት የምርምር ጽሑፍ አሰናጅነታቸውን፡፡
“ሌሎች መምህራን በቀጠሮ ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡ ዶክተር ነገሪ ግን ቀጠሮ ላይ ቆራጥ ናቸው፡፡” ይላል በመመረቂያ ወረቀት ላይ የሚያማክሩት የነበረ ተማሪያቸው፡፡ በቢሮ 410 መቼም አጥቻቸው አላውቅም ፡፡ “….ምናልባት የማይገኙት ማክሰኞና ሐሙስ በፓርላማ ስብሰባ ምክንያት ነው፡፡ እንጂ በሽ በሽ ናቸው” ሲል ዶክተሩን በቀጠሮ አክባሪነታቸው ያሞግሳቸዋል፡፡
የዚህ ተማሪያቸው ምስክርነት እውነትነት ሳይኖረው አይቀርም፡፡
ዶክተር ነገሪ በኔልሰን ማንዴላ ስም በተሰየመውና 6 ኪሎ ካምፓስ የ5ኛ በር መውጫ፣ 4ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው ቢሯቸው በተሾሙ ማግስት እንኳ ማልደው ተገኝተው ነበር፡፡ ረፋድ ላይ በርከት ያሉ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክቶችን ከተማሪዎቻቸውና ከባልደረቦቻቸው ይቀበሉም ነበር፣ በግማሽ ፈገግታ፡፡
‹‹እኔማ አልፈልግም ብያቸው ነበር…ማስተማሩ ነበር የሚሻለኝ›› ብለው ለጸሐፊያቸው ሲናገሩ በጆሮዬ ሰምቻቸዋለሁ የሚለው ጎልማሳ የሥራ ባልደረባቸው በምን መለኪያ እርሳቸው ለቦታው እንደታጩ እስካሁንም ሊገባኝ አልቻለም ይላል፡፡ ቦታው እንደነ ዶክተር አብዲሳ፣ እንደነ ዶክተር ዘነበ፣ እንደነ ዶክተር ገብረመድኅን አይነት ቀልጠፍጠፍ ያሉ ሰዎችን የሚፈልግ ነው፡፡ ዶክተር ነገሪ ግን እኔ እስከማውቃቸው ድረስ ቦታው ይከብዳቸዋል፣ ይላል ይኸው የሚዲያ መምህርና የሥራ ባልደረባቸው፡፡ ላለፉት 3 ዓመታት አብሯቸው በመልካም ሁኔታ እንደሰራም ይናገራል፡፡
“ከሁለት ዓመት በፊት የጥናት ወረቀት አማካሪዬ ነበሩ የምትል ሌላ ወጣት በበኩሏ ግርምቷን መደበቅ የተሳናት ይመስላል፡፡ ‹‹…እኔ በበኩሌ ዶክተር ነገሪ ሚኒስትር ሆኑ ሲባል ለምን እንደሆነ አላውቅም በጣም ደንግጫለሁ፡፡ እውነቱን ንገሪኝ ካልሽኝ ለቦታው የሚሆኑ ሰው አይደሉም፡፡ አማርኛንም ሆነ እንግሊዝኛን አቀላጥፎ መናገር ላይ ብዙም አይደሉም፡፡ ማርክ ስጫቸው ካልሽኝ ከ10 ስድስት ነው የምሰጣቸው፡፡” ትላለች እየተፍለቀለቀች፡፡
“በብዛት የአካዳሚክ ቋንቋን ነው የሚናገሩት፡፡ እንዴት አድርገው ነው በዓለም አቀፍ ሚዲያ ላይ ቀርበው የመንግሥትን አቋም በእንግሊዝኛ የሚያንጸባርቁት? የምትለው ሌላኛዋ ተማሪያቸው ናት፡፡ “ብቻ ይቅናቸው…” ብላ አጭር አስተያየቷን በአጭሩ ትደመድማለች፡፡
“ዶክተር ነገሪ ሁሉንም ሰው ላለማስቀየም የሚሞክሩ ሰው ናቸው፡፡ መወሰን የሚችሉ ሰው አይደሉም፡፡ ይህ ባሕሪያቸውም ሌላ ፈተና ይሆንባቸዋል” ይላል ከፍ ብሎ አስተያየቱን የሰጠኝ ባልደረባቸው፡፡
“2ኛ ዲግሪዬን ስሠራ Communication Theory የሚባል ኮርስ ሰጥተውኛል” የምትል ሌላ የቀድሞ ተማሪያቸው ደግሞ የማስተማር ችሎታቸውን ጭምር ጥያቄ ዉስጥ ትከታለች፡፡ ” በወቅቱ ኮርሱን የምንወስደው ብዙዎቻችን ከተለያዩ የክልል ዩኒቨርስቲዎች የመጣን ነበርን፡፡ ይህንን ኮርስ ይነስም ይብዛ እናውቀዋለን፣ አንዳንዶቻችን እንዲያዉም አስተምረነዋል፡፡ እርሳቸው ሲያስተምሩን ግን ልንታዘባቸው እንጂ የእውነት ለመማር አልበረም ክፍል ዉስጥ የምንገኘው፡፡” ትላለች፡፡
ሌሎች ተማሪዎች ግን ከዚህ በተቃራኒው ይመሰክሩላቸዋል፡፡
“በርግጥ ብዙ አያወሩም፤ አሳይመንት አብዝተው ይሰጣሉ፡፡ ሁሉም መምህራን እንደሚያደርጉት አማርኛም እንግሊዝኛም እየቀላቀሉ ነው ያስተማሩን፤ እንደማንኛውም የተማረ ኢትዮጵያዊ በቂ እንግሊዝኛን ይናገራሉ፡፡ ከማንም አያንሱም ከማንም አይበልጡም› ልልሽ የምችለው ይህንን ብቻ ነው” ይላል ከአመት በፊት የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሙን የጨረሰ አስተያት ሰጪ፡፡
አሁን በጎንደር ዩኒቨርስቲ በመምህርነት የምታስተምር የቀድሞ ተማሪያቸውም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥታኛለች፡፡
“…ሲያስተምሩ ላይመስጡሽ ይችላሉ፤ ግን ያው እንደሁሉም አስተማሪዎች ናቸው…” ትላለች፡፡
በፈረንጆች አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ነገሪ ሌንጮ የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪያቸውን ያጠናቀቁት በሕንድ ሐይድራባድና አንድራ ዩኒቨርስተዎች ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ሁለተኛ መንፈቅ ላይ ኮርስ እንደሰጡት የሚናገር ሌላ ወጣት በበኩሉ ዶክተር ነገሪ ጠንካራ የኦሮሞ ብሔርተኛ እንደሆኑ አውቃለሁ ይላል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዳ “ከኛ ከተማሪዎቻቸው በተለየ የሚያቀርቧቸው አብረዋቸው ቸርች የሚጸልዩ ኦሮሞ ፕሮቴስታንቶችን ነበር፡፡ ይሄ የኔ ብቻ ሀሜት እንዳይመስልሽ፤ ብዙዎቻችን ያስተዋልነው ነገር ነው፡፡” ይላል፡፡
በተጨማሪም በሚዲያ ቀርበው ተቃራኒ ሐሳብ ለመሞገት እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ አይነት አቅም የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡ እንዳየኋቸው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ካልሆነ ንግግር ላይ ብዙ አይደሉም” ሲልም ተጨማሪ አስተያየቱን ያክላል፡፡
ዶክተር ነገሪ ስልጣናቸውን ከተረከቡ ቀናት ቢቆጠሩም እስካሁን አንድ ሁለት ጊዜ ለዉጭ ሚዲያ አጠር ያለ ቃል ከመስጠት ዉጭ ሙሉ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው አያውቁም፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ለአገር ዉስጥና ለዉጭ ሚዲያ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
“እኔ እንደምንም ብዬ ‹‹ሪኮመንዴሽን ሌተር›› ላጽፋቸው እየሞከርኩ ነው፡፡ ለስኮላርሺፕ ይጠቅመኛል” ትላለች ከትናንት በስቲያ በስልክ ያነጋገርኳት የቀደሞ ተማሪያቸው፤ ከርሳቸው ያልተጠበቀ ሥልጣን አንድ ያልተጠበቀ ትረፍ ማግኘት እንዳለባት በጽኑ ያመነች ይመስላል፡፡