ዋዜማ ራዲዮ- የኦሮሚያ ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት ማስፋፊያ ተነሽ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ካሳ ወይም ምትክ ቦታ ሳይሰጣቸው ቤታቸውን በሦስት ቀን ውስጥ እንዲያፈርሱ የመጨረሻ ማስጠንቀቂ እንደተሰጣቸው ዋዜማ ከተነሽዎች ሰምታለች፡፡
አዲስ አበባ ፍላሚንጎ አካባቢ እስከ ግሪክ ትምህርት ቤት ድረስ ባለው አካባቢ ለሚገነባው የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ማስፋፊያ ቦታውን እንዲለቁ ትዕዛዝ የተሰጣቸው መካከል 15 የግለሰብ ቤቶች የሚገኙ ሲሆን፣ የቀበሌ ቤቶችም ተነሽ ናቸው ተብሏል፡፡
ዋዜማ የተመለከተችው በየካቲት 30/2014 ዓ.ም ለተነሽዎች የተሰጠ የቤት ማፍረሻ የመጨረሻ ማስጠንቀቂ ትዕዛዝ “ይህ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በደረሰዎት በተከታታይ ሦስት ቀናት ውስጥ ቦታውን ነጻ እንድታደርጉ እያሳሰብን፣ ይህ ሳይሆን ቢገኝ ግን ለሚወሰደው እርምጃ ጽሕፈት ቤታችን ኃላፊነቱን እንደማይወስድ እናሳውቃለን” ይላል፡፡
የመጨረሻ ማስጠንቀቂ ደብዳቤውን ለተነሽዎች የጻፈው የቂርቆስ ከፍል ከተማ ወረዳ 01 የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ነው፡፡
ይህ ደብዳቤ የደረሳቸው ተነሽዎች፣ በቃል ደረጃ ካሳ በዝግ አካውንት ገብቶላችኋል ብንባልም እጃችን ላይ የደረሰ የሰነድ ማስረጃ ፣ገንዘብም ይሁን ቦታ የለም ብለዋል፡፡
“ከስምንት ወራት በፊት የምትክ ቦታ ምረጡ ተብለን ብንመርጥም አስካሁን በእጃችን የገባ የምትክ ቦታ ካርታ የለም” ሲሉ ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡
“የካሳ ገንዘብ በዝግ ሂሳብ (አካውንት) ገብቷል የሚሉትን አምነን እንዳንቀበል፣ እኛ ያላወቅነውና ያልፈረምንበት አካውንት ምን አይነት አካውንት እንደሆነ ግራ ገብቶናል” ይላሉ ተነሽዎቹ፡፡
የማስፋፊያ ተነሽዎቹ ለቤታቸው የሚከፈላቸውን ካሳ መጠንና እና የሚሰጣቸውን ምትክ ቦታ ወይም ቤት ሁኔታ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ በእጃች ላይ የገባ ነገር ሳይኖር ቤታችንን በሦስተ ቀን አፍርሳችሁ ውጡ መባላቸው ግራ አጋብቶናል ብለዋል፡፡
ዋዜማ ከተነሽዎቹ እንደሰማችሁ አስካሁን አንድ ተነሽ በአካውንቱ ገንዘብ እንደገባለትና ቀሪዎችቹ ሰዎች ቦታም ይሁን ገንዘብ አለመቀበላቸውን ነው፡፡
ተነሽዎቹ እንደሚሉት በመነሳታቸው ቅሬታ እንደሌላቸው ነገር ግን ምንም ነገር እጃቸው ሳይገባ ቤታቸውን አፍርሰው አንዲወጡ መታዘዛቸው ግራ አጋብቶናል ሲሉ ነግረውናል፡፡
ጉዳዩን አስመልክተን ጥያቄ ያቀረብንለት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ስለጉዳዩ መልስ መስጠት የሚችለው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ፅሕፈት ቤት ነው በሚል ያልተብራራ ምላሽ ስጥቶናል። የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ፅሕፈት ቤት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ላቀረብንለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም። [ዋዜማ ራዲዮ]