ዋዜማ- የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪን የተመለከተ ረቂቅ ለሚንስትሮች ምክርቤት ሊቀርብ እንደሆነ ዋዜማ ተረድታለች። 

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚም ሆነ የፋይናንስ ንዑስ ክፈለ ኢኮኖሚውን በመሠረታዊነት የሚቀይሩ አዳዲስ አዋጆችን በተከታታይ እያወጣ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ካቢኔ፣ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው በኩል ረዘም ላለ ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው አዋጅ ሊቀርብለት እንደሆነ ተስምቷል። 

እንደ ዋዜማ የመረጃ ምንጭ ከሆነም፣ በቀጣዮቹ ሳምንታት ለካቢኔ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው ረቂቅ፣ የአገሪቷ የኢንሹራንስ ድርጅቶችን አስመልክቶ የሚቆጣጠራቸውን አካል ከብሄራዊ ባንክ አስወጥቶ ሌላ እነርሱን ብቻ የሚመለከት ተቆጣጣሪ ተቋም ለማቋቋም ያለመ እንደሆነ ተሰምቷል። 

በዓለም ባንክ አማካኝነት ከስድስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የዚህ አዋጅ አስፈላጊነት ጥናት፣ የውጪ ኩባንያዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ምክረ-ሃሳብ እንደማያቀርብ ግን ምንጩ ጠቅሰዋል።

በዓለም ባንክ እና በብሄራዊ ባንክ ባለሙያዎች አማካኝነት ተረቆ አልቋል የተባለው ረቂቅ አዋጅ ላይ፣ የግል ኢንሹራንስ ድርጅት የቦርድ አባላትም ይሁኑ ከፍተኛ የአስተዳደር ኀላፊዎች ሃሳብ እንዳልተጠየቁ ያወሱት አንድ የዋዜማ ምንጭ፣ ‘የሚንስትሮች ምክር ቤት ከተመለከተው በኋላ እናወያያችኋለን’ መባላቸውን ለዋዜማ ነግረዋታል። 

ከወራት በፊት የተሾሙት የባንኩ ገዢ ማሞ ምህረቱም፣ ይህ ተቋም እንዲቋቋም ጠንከር ያለ ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ዋዜማ ተረድታለች። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ በያዝነው ወር መገባደጂያ ይህንኑ ተቋም ለማቋቋም እና ከቀጣዩ በጀት ዓመት ጀምሮም የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ በዚህ ተቋም ስር እንዲሆኑ መወሰኑም ተሰምቷል። በዚህ አዋጅም፣ ግማሽ ክፈለ-ዘመን ለሚሆን ጊዜ የኢንሹራንስ ሴክተሩን ሲመራ የነበረው ብሄራዊ ባንክ፣ የመቆጣጠር ኀላፊነቱ የሚያበቃ ይሆናል። 

የአገሪቷ የኢንሹራንስ ድርጅቶች፣ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ፣ የኢንሹራንስ ንዑስ ፋይናንሺያል ኢኮኖሚው በብሄራዊ ባንክ ቁጥጥር ስር መሆኑ ሊኖራቸው ይችል የነበረውን ዕድገት እንደገደበባቸው በተለያዩ መድረኮች ሲወተውቱ ሰንብተዋል። እንደ ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ አመራሮች እና ክፈለ-ኢኮኖሚውን በቅርበት እንደሚያውቁት ባለሙያዎች ገለፃ፣ ከሦስት ዐሥርታት በላይ የቆየው ይህ የቁጥጥር መስመር፣ አዳዲስ የኢንሹራንስ ድርጅቶች ወደ ክፈለ-ኢኮኖሚው እንዳይገቡ ከማገዱ ባለፈ፣ ተጨማሪ የኢንሹራንስ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እጅጉን እንደገደባቸው ይናገራሉ። የባንኮች ቁጥር ሲጨምር፣ የኢንሹራንሶች ዕድገት ለማዝገሙም፣ ክፈለ-ኢኮኖሚው በብሄራዊ ባንክ ስር መሆኑ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱም ይነሳል።    

ልክ የዛሬ ዓመት፣ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደ አንድ አሕጉር አቀፍ ስብሰባ ላይ በተናጋሪነት የተገኙት የብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ዶ/ር ሰለሞን ደስታ፣ የአገሪቷ የኢንሹራንስ ክፍለ-ኢኮኖሚ ለውጪ የኢንሹራንስ ድርጅቶች ክፍት እንደሚደረግ ተናግረው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም፣ ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ ዜግነት ብቻ በነበራቸው ባለሃብቶች ተይዞ የቆየው ኢንዱስትሪው፣ ከሦስት ዓመታት በፊት የባህር ማዶ ዜግነት የያዙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም እንዲሳተፉበት የሚያስችል አዋጅ በሕዝብ እንደራሴዎች እንዲፀድቅ መደረጉ ይታወሳል።  [ዋዜማ]