ዋዜማ- የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ መሪዎች ኢትዮጵያን ለ50 ዓመታት የባህር ጠረፍ ተጠቃሚ የሚያደርግ የመግባቢያ ሰነድ ከፈረሙ በኋላ በቀጠናው አዲስ የጆኦ ፖለቲካ ድንግርግር ተፈጥሯል። 

አሜሪካና ቻይና በሶማሊላንድ ጉዳይ የተለያየ አቋም አላቸው። ይህ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጥረት አጋዥም ፈታኝም እውነታ ነው። የአፍሪቃ ህብረት በተደጋጋሚ የቀረበለትን የሶማሊላንድ የዕውቅና ጥያቄ አልተቀበለም። የኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ  ዕውቅና መስጠት በአፍሪቃ አህጉር አዲስ መስመር ሆኖ ይመዘገባል። 

ስምምነቱ በታቀደው መሰረት ከተጠናቀቀ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪቃ ቀንድ አዲስ የታሪክ እጥፋት እንደሚሆን በርከት ያሉ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ። 

በሀገር ውስጥ በእርስ በርስ ግጭትና በበረታ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ከፊቷ የሚጠብቃት ተግዳሮትን ለመወጣት ያለችበትን ቁመና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ። 

የመግባቢያ ስምምነቱ 20ኪሜ በ90 ኪሜ  የሚሆን የባህር ሀይል ሰፈርና የበርበራ ወደብን ለመጠቀም የ50 ዓመታት የሊዝ ኪራይ ስምምነት ነው። 

ሶማሊያ ስምምነቱን “ተቀባይነት የሌለውና ሉዐላዊነቴን የሚዳፈር ነው፣ ለዚህም አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ወደ ኋላ አልልም”  ብላለች። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ አዲሱ ስምምነት አልሸባብ እንዲያንሰራራ በር ይከፍታል ሲሉም ለፓርላማቸው ተናግረዋል። አስከትለውም ለግብፅና ለኳታር መሪዎች ስልክ በመደወል የአጋርነት ድጋፍ ጠይቀዋል።  የሶማሊያ መንግስት የአፍሪቃ ህብረት፣  የፀጥታው ምክር ቤትና የአረብ ሊግ እንዲሁም ኢጋድ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርጉ የሚጠይቅ መግለጫ አውጥቷል።

ሶማሊያ በአዲስ አበባ የነበሯትን አምባሳደርም ለምክክር ወደ ሀገር ቤት ጠርታለች።

በሶማሊላንድ ሀርጌሳ የመግባቢያ ሰነዱ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድና ሙሴ ባሂ አብዲ መፈረሙ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍና የአደባባይ የደስታ መግለጫ እየተደረገ ነው። በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና ለመስጠት መስማማቷን የሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ይፋ ያደረገ ሲሆን ይህም ለሰላሳ አመታት ከሶማሊያ ተነጥላ ለቆየችው ሶማሊላንድ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ተደርጎ ተወስዷል። 

በዝርዝር ጉዳዮች ላይ በአንድ ወር ውስጥ ስምምነት ይደረሳል ተብሎ ይጠበቃል። 

በዚህ በሶማሊላንድና ኢትዮጵያ ስምምነት ዙሪያ አስቀድሞ መረጃው የተነገራቸው ጥቂት ሀገራት መኖራቸውን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ስምታለች። ምናልባትም የተባበሩት አረብ ዔምሬትስ ለሶማሊላንድ ዕውቅና በመስጠት ኢትዮጵያን ልትቀላቀል እንደምትችል ይጠበቃል። 

ለኢትዮጵያ የባህር ሀይል በማሰልጠንና የጦር መሳሪያ በመሸጥ አጋር የሆነችው ፈረንሳይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም። የአውሮፓ ህብረት ግን የሶማሊያን ሉዐላዊነት የሚዳፈር ማናቸውንም ድርጊት እንደሚያወግዝ በቃል አቀባዩ በኩል አስታውቋል። 

ዩናይትድስቴትስ ከወራት በፊት ከሶማሊላንድ ጋር የተናጠል ወታደራዊና የፀጥታ ትብብር ማድረግ የሚያስችላትን ህግ በኮንግረስ በኩል አስፀድቃለች። ይህ የአሜሪካ እርምጃ አሁን ኢትዮጵያ ላደረገችው ስምምነት አጋዥ መከራከሪያ ሊሆን የሚችል ነው። 

ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ ብርቱ ዲፕሎማሲያዊ ፈተና ከፊቷ የሚጠብቃት ኢትዮጵያ ጠንካራ የልዑካን አባላትን የያዘ የዲፕሎማሲ ቡድን ወደተለያዩ ሀገራት ለማሰማራትና  በውጪ ያሉ ዲፕሎማቶችን ስለጉዳዩ እንዲያስረዱ ለማድረግ ማቀዷን ሰምተናል። 

ዋነኛ የኢኮኖሚ አጋር የሆነችው ቻይና ፣ ከታይዋን ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያን እርምጃ እንደማትደግፈው ከወዲሁ እየተነገረ ነው። እስካሁን ከቻይና በኩል የወጣ መግለጫ የለም። 

የአረብ ሊግና አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከሶማሊያ ጎን እንደሆኑ ከወዲሁ እየተናገሩ ነው። ግብፅ ከሶማሊያ ጋር ሁለገብ ትብብር ለማድረግና የሶማሊያን የግዛት አንድነት ለማስከበር ድጋፍ እንደምታደርግ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ለሶማሊያ አቻቸው ለሀሰን ሼክ መሀሙድ ቃል ገብተዋል። 

ባለፉት ሶስት አመታት የሶማሊያ ወታደሮችን በማሰልጠን ስራ ተጠምዳ የሰነበተችው ኤርትራ እስካሁን ይፋዊ አስተያየት አልሰጠችም። ባለፉት ወራት ኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎቷን መግለጿን ተከትሎ ኤርትራን ልትወር ትችላለች በሚል ሰፊ መላ ምት በውጥረት የሰነበቱ ኤርትራውያን እፎይታ እንደተሰማቸው በማህበራዊ ሚዲያ ሲገልፁ አንብበናል። [ዋዜማ]