ዋዜማ ራዲዮ- አቶ ማቴዎስ ላለፉት ሦስት ዓመታት አዲስ አበባን ቀደው ሲሰፉ ነው የከረሙት፣ ከንቲባው እንኳ እንደ እርሳቸው አልደከሙም፡፡
ደግሞም ባለሐብት ናቸው፡፡ በስማቸው በአርክቴክቸር፣ በከተማ ልማት፣ በከተማ ዕድገትና በከተማ አስተዳደር ዙርያ የሚያማክር ዕዉቅ ድርጅት አላቸው፡፡ ማቴዎስ ኮንሰልት የሚባል፡፡ በሚሊዮኖች ገቢ ያስገባል፡፡ በዚህ ሐብት ላይ ስልጣን ተጨመረላቸው፡፡ በአዲሱ ካቢኔ የከተማዋ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ኾነው ተሹመዋል፡፡
መቼ ለታ ታዲያ ካፒታል ሆቴል ሰብስበውን ስለ መሪ ፕላኑ እያወያዩን ሳለ ከንቲባ ድሪባ ድንገት ከተፍ አይሉም!!? ሁላችንም ክው ብለን በድንጋጤ ቆመን ተቀበልናቸው፡፡ ክቡርነታቸው በተዘጋጀላቸው ወንበር ቁጭ እንዳሉ እኛም ቁጭ አልን፡፡ አቶ ማቴዎስ ቀልጠፍ ብለው የሚከተለውን ተናገሩ፡፡
እንግዲህ እዚህ ከመጡ አይቀር…በናንተው በተሰብሳቢዎች ስም ክቡር ከንቲባውን የምማጸነው ሥልጣንዎን በቅርብ ጊዜ ዉስጥ እንዳይለቁ ነው፡፡ አቶ ኩማን እንዲሁ እባክዎ ሥልጣን አይልቀቁ ስላቸው ድንገት ለቀው አምባሳደር ኾኑ፡፡ እንደ አዲስ አበባ ዉስብስብ ችግር ባለባት ከተማ አንድ ከንቲባ ዘለግ ላለ ጊዜ በወንበሩ ካልተቀመጠ ፈተና ነው፤ አለመታደል ነው፡፡ እኔ እንደሚገባኝ ክቡር ከንቲባው ገና አሁን የከተማችንን ዉስብስቡን ችግሮች እየተረዱት መጥተዋል፡፡ አይበለውና እርሳቸው ወርደው አዲስ ከንቲባ ቢመጣ አዲስ መፍትሄ ለማምጣት ይቅርና ገና ችግሩን ለመረዳት ሌላ 5 ዓመታት ይወስድበታል፡፡ እኔ የከተማ ፕላነር ነኝ፡፡ በማስረጃ መናገር እወዳለሁ፡፡
እስካሁን ከተማዋን የመሯት ከንቲባዎች በቁጥር 30 ናቸው፡፡ የከንቲባዎቹን ቁጥር ለአዲስ አበባ እድሜ ብናካፍለው በአማካይ አንድ ከንቲባ ቢበዛ ለ3 እና ለ4 ዓመታት ነው የቆየው ማለት ነው፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ አሁንም በናንተው ፊት ክቡር ከንቲባ ድሪባን የማሳስበው፣ እባክዎን ሥልጣን አይልቀቁ፡፡ (አድርባይነት የተጫነው ሞቅ ያለ የድጋፍና ጭብጨባ አጨበጨብን)
“የማቴዎስ ማስተርፕላን”
የአቶ ማቴዎስ ማስተር ፕላን ያለፉትን ዘጠኝ ማስተር ፕላኖች በስፋትና በጥልቀት ይተቻል፡፡ ሲጀመር እኛ ለምንኖርባት ከተማ ነጮች ፕላን ሊሠሩልን አይገባም ነበር የሚል ጽኑ አቋም አላቸው፣ አቶ ማቴዎስ፡፡
የአዲስ አበባ የመጀመርያው ማስተር ፕላን ከእቴጌ ጣይቱ የአሰፋፈር እቅድ ይጀምራል፡፡ ይህ በ1878 የሆነ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ 9 መሪ ፕላኖች መጥተው ሄደዋል፡፡ በ1928 የሊኮርቡዚየ የአሰፋፈር እቅድ፣ በ1938 የጉይዲና ቫለ ማስተር ፕላን፣ በ1948 የአምበርክሮምቢ ማስተር ፕላን፣ በ1958 የቦልተንና ሄነሲ ማስተር ፕላን፣ ከዚያም በየ አስር ዓመት ልዩነት የዲ ማርየን፣ የፖሎኒ፣ የኢትዮ ጣሊያን፣ እያለ በፈረንጅ ስሞች ከቀጠለ በኋላ በ1994 የአዲስ አበባ መሪ ፕላን ተከተለ፡፡ የመሪ ፕላን እቅድ ጉድለት ኖሮ አያውቅም፣ የአተገባበር እንጂ የሚሉት ታዲያ ብዙ ናቸው፡፡
10ኛው ማስተር ፕላን ልዩ የሚያደርገው ታዲያ በኢትዮጵያዊያን መጠንሰሱ ብቻ ሳይሆን በዉዝግብ መታጀቡና ከተማዋ ወደጎን ለመስፋት አንዲት ኢንች ቦታ እንኳ በታጣበት ማግስት ለትግበራ ጫፍ መድረሱ ነው፡፡ ይህ ሀቅ ከተማዋ በቁመናዋ ብቻ እንድታድግ አስገደደ፡፡ አጎራባች የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በአዲስ አበባ ላይ ማደማቸውን ከቀጠሉ ግን ወደላይ ማደግ ሁሉን አቀፍ መፍትሄን አይሰጥም፡፡ ልዩ ዞኖቹ መልካም ጎረቤት መኾንን ካልፈቀዱ አዲስ አበባ በአንድ ኩላሊት ለመኖር ተገደደች ማለት ነው፡፡
ከ1.1 ሚሊዮን ሄክታር የተቀናጃ ማስተር ፕላን ወደ 54ሺህ ሄክታር የተናጥል ማስተር ፕላን ከዚያም ወደ 52ሺ ሄክታር መሪ ፕላን የሄደው 10ኛው መሪ እቅድ መጽደቅ ከነበረበት ሦስት ዓመት ዘግይቶ ሊጸድቅ የይስሙላ ዉይይት ብቻ ቀርቶታል፡፡ 300 መቶ ሺ ነዋሪዎችን በአንድ ሳምንት ዉስጥ ለግማሽ ቀን ብቻ በፍጥነት አወያዩ የተባሉ የወረዳ ሥራ አስፈጻሚዎች ለነርሱም እንግዳ የኾነውን ማስተር ፕላን ይዘው በጨበጣ ነዋሪዉን ማወያየት ላይ ተጠምደዋል፡፡ ሥራ አስፈጻሚዎቹ ቴክኒካል ጥያቄዎች ከነዋሪው ከተነሱባችሁ በሂደት ለሚመለከተው እናቀርባለን በሏቸው ተብለው ነው ወደ ዉይይት ግቡ የተባሉት፡፡ በአብዛኛው መድረኮች የታደሙት ታዲያ የድጋፍ ሰልፍ በመውጣት አበል የሚቀበሉት በእድሜ የገፉ ባልቴቶች ናቸው፡፡ ደግነቱ ከባልቴቶቹ ዉይይት በፊት ማስተር ፕላኑ በሊዮን፣ በጣሊያን፣ በዳካር እና በኮሪያ ሶል ከባለሞያዎች ዘንድ ለዉይይት ቀርቧል፡፡
መሪ ዕቅዱ መልከ ብዙ ገጽታዎች አሉት፡፡
የማያወላዳ የአፍሪካ ዋና ከተማ መሆን መሪ ሕልሙ አድርጓል፡፡ የቤት እጦትን መቅረፍ ትልቁ አጀንዳው ነው፡፡
የአፍሪካ መዲና የመኾን ፈተና
የመሪ ፕላኑ መግቢያ አዲስ አበባን The undisputed capital city of Africa ማድረግ ግቡ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ እርግጥ ነው ሸገር የአፍሪካ መዲናነቷ ጥያቄ ዉስጥ ሲገባ ኖሯል፡፡ ግብጽና ትሪፖሊ የተገቢነት ጥያቄ አንስተው ያውቃሉ፡፡ ናይሮቢ ለብዙ ዓለማቀፍ ተቋማት መመቸቷን በተግባር አስመስክራለች፡፡ አዲስ አበባ የማያወላዳ የአፍሪካ መዲና ለመሆን ከማንም የተሻለ እድል አላት ብንል ግን አልተሳሳትንም፡፡ ምናልባት ፈተና የሚኾንባት ገዢዎቿ የነዋሪዎቿን ነጻነት ለማፈን የሚወስዳዱት መሪር እርምጃ ደፋዉ ለእንደግዶቿም መትረፉ ነው፡፡ ኢንተርኔትን ነጋ ጠባ የምትቆልፍ፣ መብራት በየደቂቃው የምታጠፋ ከተማ የጨለማውን አህጉር ብትወክል ምጸት አይሆንም፡፡ ኾኖም ይህ ባህሪዋ ካልተስተካከለ ለመጪዋ አፍሪካ መዲናነት የምትመጥን አትሆንም፡፡
ምንድነው ተስፋዋ ያልን እንደሆነ…
ወደ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እየቀረበች መኾኗ፣ የተሻለ መሠረተ ልማት ግንባታ ሂደት እዚያም እዚህም መታየቱ፣ አንጻራዊ ሰላም መኖሩ፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነት በታሪክ አጋጣሚ ይዞ መቆየት መቻሏ፣ ባለኮከብ ሆቴሎች በገፍ ወደ ግንባታ መግባታቸውና የመሳሰሉት አዲስ አበባን የማያወላዳ (undisputed) ዋና ከተማ የመኾን ተስፋዋን ያለመለሙ ከፊል ሀቆች ናቸው፡፡ ነገሩን ለማስረገጥ አዲሱ መሪ ፕላን በገርጂና በለቡ ሁለት ዓለም አቀፍ ስቴዲየሞችን ይዟል፤ አምስት እያንዳንዳቸው 25ሺህ ሰው የሚይዙ የዞን ስታዲየሞች እቅድ ላይ ናቸው፡፡ 60ሺ ተመልካች የሚይዘው አደይ አበባ ስታዲየም ግንባታው 30 ከመቶ ደርሷል፡፡ ደበጦርኃይሎች፣ በሳርቤት፣ በሜክሲኮና በካዛንቺስ ባለ 5 ኮከብና ከዚያም በላይ የኾኑ አምስት ሆቴሎችን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት እንደሚገነቡ መሪ እቅዱ ተልሟል፡፡
ቦሌ አራብሳና መሪ ሎቄ ሁለት ዓለም አቀፍ ሆስፒታሎች እንዲገነቡባቸው የተመረጡ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በ2ኛው የመሪ ዕቅዱ ዓምስት ዓመት ደግሞ በእንጦጦ ተራራ ላይ አንድ ባለ አምስት ኮከብ የአፍሪካ ቁንጮ የሚሆን ሆቴል እንዲገነባ እቅድ ተይዟል፡፡
የጭቁኖች ሰፈር የነበረውና በአንድ ሌሊት የፈረሰው ወረገኑ፣ ከአየር መንገድ ጀርባ አዲስ የሞጃ ሰፈር ኾኖ ብቅ ያለው ቦሌ ቡልቡላ ለጎልፍ ሜዳ የተተዉ ሰፋፊ ተዳፋት መሬቶች ናቸው፡፡ የአየር መንገድ ክልል ዙርያውን ለጎልፍና ለፈረስ ግልቢያ የተተወ ስፍራ ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር 10ኛው ማስተር ፕላን ሰፋፊ ፕላዛዎችን በአፍሪካ ከተሞች ስም በመወከል ለመገንባት ያልማል፡፡ አንድነት አደባባይ ከለገሀር ጀርባ ለመፍጠር ያስባል፡፡ ትልቁ የብሔር ብሔረሰቦች አደባባይና ትልቁ የአፍሪካ ኅብረት አደባባይ የሚገነቡትም በዚሁ ስፍራ ይሆናል፡፡ ትልቁን የአፍሪካ ሙዝየም በጨርቆስ ለመገንባት ዉጥን ይዟል፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶች 54 የአፍሪካ ከተሞችን ስም መያዛቸው ሌላው እሴት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ አዲስ አበባን በአስር ዓመት ዉስጥ The undisputed capital city of Africa ለመሆን ያስችላታል ተብሏል፡፡
አንድ ሚሊዮን ቤት
በመሪ ዕቅዱ ሰነድ በ10 ዓመት 1.3 ሚሊዮን ቤት ለመገንባት መታሰቡ ተወስቷል፡፡ ይህ ታዲያ የከተማዋ የሕዝብ ቁጥር አሁን ካለበት 3.5 ተነስቶ የዛሬ 10 ዓመት 6 ሚሊዮን ይደርሳል በሚል ስሌት ነው፡፡ በ25 ዓመት ደግሞ የቤቶቹን ቁጥር 1.8 ሚሊዮን ማድረስ ይፈለጋል፡፡ ለብዙዎቸ ይህ አሀዝ የሚዋጥ አልሆነም፡፡ የቤቱም የሕዝቡም፡፡ አሁንስ 6 ሚሊዮን አልሞላንም ወይ የሚለው ብዙ ነው፡፡ የአሀዝ መፋለስ የእቅድ መፋለስን ያስከትላል፡፡
አንድ መንግሥት የሚያልመው ሕልም ቅዠት እንዳልሆነ ለመረዳት ያለፈ ታሪኩን መገምገም ብቻ በቂ ነው፡፡ በ1996 በተጀመረ የጋራ መኖርያ ቤት ፕሮጀክት ግማሽ ሚሊዮን ቤት በአጭር ጊዜ ሠርቶ ለማስረከብ ይኸው መንግሥት አልሞ ነበር፡፡ በድፍን 10 ዓመት መገንባት የቻለው ግን 150ሺ እንኳ አልሞላም፡፡ በ40/60 መርሐግብር 160ሺ ቤቶችን በሁለት ዓመት ገንብቼ አስረክባለሁ ብሎ ነበር መንግሥት፡፡ አሁን በ6 ዓመት ይህን ህልሙን ማሳካት እንደማይችል ከራሱ ሹሞች መስማት ተጀምሯል፡፡ ይህ በመሪ ፕላኑ ላይ የተቀመጠውን የ1.3 ሚሊዮን ቤት ፕሮጀክትን ታዲያ እንዴት ብሎ ማመን ይቻለናል?
ይልቅ በዚህ መሪ ዕቅድ ስሜት የሰጠኝ የትኛውም ቅይጥ ሕንጻ በአናቱ መኖርያ ቤት እሽኮኮ እንዲል የሚያስገድድ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ተፈጻሚነቱ በባለሐብቶች የእጅ መንሻ ካልተቀለበሰ መልካም ነገር ነው፡፡ በብዙ መልኩ፡፡ አንደኛ መሠረተ ልማት በማዕከላዊ የከተማዋ ስፍራዎች በአጭር ጊዜ ዉስጥ እንዲዘረጋ ያስችላል፡፡ ሁለተኛ ከጥግጊት ኑሮ ርቃ አለቅጥ ለተለጠጠችው ከተማ መልክ ያበጅላታል፡፡ ፈተናው በዚያው መጠን ነው፡፡ ስንቱ ሕንጻ በሕንጻ ደንብ ይመራል የሚለው አንዱ ጥያቄ ነው፡፡ የኑሮ ዘያችን፣ የጋርዮሽ ኑሯችን ለአፓርትመንትኛ የሚኾን አይደለም፡፡ በስንቱ ሕንጻ ቡናና ጌሾ እንደሚወቀጥ፣ በስንቱ ኮሪደር ገብስና በርበሬ እንደሚሰጣ ሳስብ….፡፡ የስንቱ ሕንጻ ሊፍቱ እንደሚበላሽ፣ በስንቱ ቆጥ የፍሳሽ ጦርነት እንደሚፈነዳ ሳስብ፡፡ ደግሞም የአዲስ አበባ ዉሀ ከእንጦጦ ካልተንደረደረ ከ15 ፎቅ በላይ የመውጣት ጉልበት የለውም፡፡ በታንከር የ30 ፎቅ ነዋሪን የዉሀ ፍላጎት ለማስታገስ እንደሚሞከር ሳስብ ገና ይደክመኛል…፡፡
ጨርቆስ ቀን ወጣላት
ጨርቆስ፣ የሸገር ዉራ ሰፈር፣ የአዲስ አበባ የድህነት ታርጋ፣ የጌቶ ሕይወት መፈልፈያ፣ የጀማሪ ኮሚክ አፍ ማሟሻ፡፡ ጨርቆስ ለዘመናት በመሐል ሰፋሪ ከተሜዎች ተንጣለች፣ ተንጓጣለች፡፡ ነገሩ ሳይደግስ አይጣላም ይመስላል፡፡ 10ኛው የሸገር ዐብይ ፍኖተካርታ (ማስተር ፕላን) ቂርቆስን ከድህነት መንጭቆ አውጥቷታል፡፡ ይህ መሪ እቅድ እንደሚበይነው ጨርቆስ የመጪው ዘመን ኹነኛዋና ብቸኛው የከተማ ማዕከል ትኾናለች፡፡ ከእንግዲህ ጨርቆስን (ቂርቀስን) የሚያህል ዉብ ቦታ አይደለም በአዲስ አበባ በሰሜን አፍሪካም አይገኝም ተብሏል፡፡
እርግጥ ነው አዲስ አበባ ላለፉት አንድ መቶ ሠላሳ አንድ ዓመታት አንድ ራሱን የቻለ፣ ሁሉን ያግባባ ዕዉቅ የከተማ ማዕከል ኖሯት አያውቅም፡፡ ፈረንጆቹ City Centre የሙሉትን ማለቴ ነው፡፡ በምኒሊክ ዘመን እንጦጦ፣ በጣይቱ ዘመን ፍልዉሀ፣ በንጉሡ ዘመን ገለሀር፣ በጣሊያን ዘመን ፒያሳ፣ በደርግ ዘመን አውቶቡስ ተራ፣ በኢህአዴግ ዘመን ቦሌ የከተማችን ማዕከላት መስለው ወይም ኾነው አገልግለዋል ብንል ጨርቆስ የሚጪዎቹ 25 ዓመታት የመዲናችን እምብርት ትኾናለች፡፡
ከለገሀር ባቡር ጣቢያ ጀምሮ ገነት ሆቴልን ይዞ፣ የለገሐርን ጀርባ ሰፈሮችን ይዞ እስከ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ድረስ የሕንጻ ከፍታቸው ከ30 በላይ የኾኑ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ይገነባሉ፡፡ የባህር ዳር በዘንባባ የተከለሉ እግረኛ መንገዶችን የመሰሉ ለዚያውም ስፋታቸው እጥፍ ሆኖ ጨርቆስ ላይ ይሠራሉ፡፡ ከብሔራዊ ቴአትር የሚጀምርና እስከ ጨርቆስ የሚዘልቅ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድ ይገነባል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ጨርቆስ የክፍለ አገር አውቶብሶች ዋና ጣቢያ፣ የአዲስ አበባ አውቶብሶች ዋና ጣቢያ፣ የከተማ ቀላል ባቡር ዋና ጣቢያ፣ የምድር ለምድር ሜትሮ ባቡር ዋና ጣቢያ፣ አገር አቀፉ ፉርጎ ዋና ጣቢያ፣ ለገሀርና ጨርቆስ እንዲሆኑ ተወስኗል፡፡
ፒያሳና ጀሞ 2ኛ ደረጃ የከተማ ማዕከላት ሲሆኑ ሌሎች 13 ሰፈሮች ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ የከተማ ማዕከልነት ተይዘዋል፡፡
አረንጓዴው ጦርነት
ከአዲስ አበባ መሬት 30 እጁ ለመንገድና ተዛማጅ ልማት፣ 40 እጁ ለግንባታ፣ የተቀረው 30 እጁ ለአረንጓዴ ቦታ መሰጠቱን ስሰማ ፈገግ አልኩኝ፡፡ አንድም የደስታ አንድም የ”እስቲ እናያለን”፡፡ ታሪክን የኋሊት ማየት የፊቱን ለመተንበይ ይረዳል፡፡
በ9ኛው ማስተር ፕላን ለአረንጓዴ መሬት የተሰጡ ቦታዎች አንድም በወረራ ተይዘዋል፣ አንድም ጉልበተኞች ሕንጻ ሠርተውበታል፡፡ አንድም መንግሥት ራሱ ያወጣውን እቅድ ቀዶ በጉልበት ቦታዎቹን ከሕዝብ ቀምቷል፡፡ ወረቀት ላይ አረንጓዴ ስለተባለ ብቻ ሳር አይበቅልበት መቼም፡፡
ለሕዝብ የተከለሉ ቦታዎች ለሕዝብ የኾኑበት አጋጣሚ ከስሟል፡፡ ለምሳሌ ሼክ ሞሐመድ ከጊቢ ገብርኤል ተነስቶ ቁልቁል በሂልተን እስከ ኢሲኤ የሚወርደውን አረንጓዴ ቦታ ከገነቡ ዘመን የለውም፡፡ ኾኖም ይህ ጥብቅ ቦታ ለማን እንደተሰራ፣ ማን በባለቤትነት እንደሚያስተዳድረው እስከዛሬም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የሼኩ ርስት ሆኖ ተቀምጧል ማለት ይቀላል፡፡ እርግጥ ነው ሕጻናት ብር ከፍለው አልፎ አልፎ ዥዋዥዌ ይጫወቱበታል፡፡ እርግጥ ነው ሙሽሮች አጥሩን ተደግገው ፎቶ ተነስተዋል፡፡ ድሀ የከተማዋ ነዋሪዎች ግን በአካባቢው ድርሽ ማለት እንኳ ይፈራሉ፡፡ ለሕዝብ ፓርክ ብር ከተከፈለ፣ በሕዝብ ፓርክ ድሀና ሀብታም ከተለየ ምኑን የሕዝብ ፓርክ ሆነው? ሼኩ ለመሰሎቻቸው የገነቡት ነው የሚመስለው፡፡
ፒኮክ ፓርክ፣ አድዋ ፓርክ፣ እና ሌሎች ጥቂት የአዲስ አበባ ክፍት ቦታዎች በቤት አልባ ነዋሪዎች ተወረው ተይዘዋል፡፡ ለነዋሪዎቹ ሌላ መጠለያ መገንባትና ቦታውን ማስከበር፣ ለአጣዳፊ የመንግሥት ፕሮጀክትም ቢኾን አረንጓዴ ቦታዎችን አለመፍቀድ ከአቶ ማቴዎስ ቢሮ የሚጠበቅ አርበኝነት ነው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሰማሁትን ላካፍላችሁ፡፡ አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት ጀርባ ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዋና መሥሪያ ቤቱን ሊያስገነባ ሲል ግንባታ ፍቃድ ቢሮ ፕላንህን ከማስተር ፕላኑ ጋር አጣጥም ይለዋል፡፡ ይሄኔ ዘራፍ አለ፤ እኔ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ነኝ፤ ፕላን አሻሽል ልባል አይገባም ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ፡፡ ነገሩ እየተካረረ አቶ ማቴዎስ ቢሮ ደረሰ፡፡ በመጨረሻ አቶ ማቴዎስ መልስ ሰጡ፡፡ ከዚህ በኋላ ማስተር ፕላኑን ማክበር የሚጀምረው ከመንግሥት ፕሮጀክቶች ነው፡፡ አስተካክል ተባለ፡፡ ደግነቱ ሰሞኑን የተባለውን አስተካክሎ ግንባታ ጀምሯል፡፡ ኾኖም ስንቶቹ መሥሪያ ቤቶች ለማስተር ፕላኑ ይታዘዛሉ? የሚለው የሚሊዮን ብር ጥያቄ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ወንዞች ወደ ላይ ይፈሳሉ
በወንዞች ዳርቻ ልማት ሊጀመር ገንዘብ ተለቋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የማሳያ ፕሮጀክቶች ትግበራ ላይ ናቸው፡፡ አቶ ማቴዎስ በአንድ ስብሰባ ላይ እንዳሉት ከዚህ በኋላ መኖርያ ቤቶች ለወንዝ ጀርባቸውን አይሰጡም፡፡ ወንዞች ፈሳሽ የቆሻሻ ገንዳዎች መኾናቸው ያበቃል፣ ከዚህ ቀደም ወንዝ ዳርቻ የሚገኙ ቤቶች ፈላጊ አልነበራቸውም፡፡ ከዚህ በኋላ እጅግ ዉድ ዋጋ የሚወጡ ቤቶች ወንዝ ዳር የሚገኙት ይሆናሉ ተብሏል፡፡ የአገሪቱ ሀብታሞች ዉድድራቸው የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ላይ ቤት በመሥራት ይሆናል ብለዋል አቶ ማቴዎስ፡፡ በዚህን ጊዜ እኔና ወዳጆቼ ‹‹የአዲስ አበባ ወንዞች ወደላይ መፍሰስ ሊጀምሩ ይሆን እንዴ?” አልን፡፡ ነገሩ ደስ የሚል ባዶ ሕልም ቢኾንብን ነው እንዲያ ያልነው፡፡
የዉሀ ቀለም ምን አይነት ነው? ብለን እስክንጠይቅ ድረስ አዲስ አበባ በጥቁር ወንዞች ተሞልተታለች፡፡ እጅግ አስፈሪ መልክና ይዘት ያላቸው የአዲስ አበባ ወንዞች በምን ተአምር ነው ሊነጹ የሚችሉት? በሺዎች የሚገመቱ የወንዝ ዳር ሕገወጥ ሰፈራዎች በምን ተአምር ነው ምትክ ቦታ የሚያገኙት፣ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ በምን ተአምር ነው ወደ ወንዝ የማይለቀቁት? ወንዙ ሁሉ ቆሻሻ ሞልቶት ደረቅ ቆሻሻን አስፋልት አውጥቶ መድፋት ግዳጅ በሆነባት አዲስ አበባ እውን ወንዞች ቀን ይወጣላቸዋልን? አስፋልት ዳር የተደፋ ቆሻሻን በመኪና ማንሳት የተሳነው ማዘጋጃ ቤት እውን ወንዝን ማጽዳት ይሳካለታልን? ጨለምተኛ ልትሉኝ ትችሉ ይሆናል፡፡ ለኔ ግን ይህ እቅድ በኢህአዴግ ከተሳካ ወንዞች ወደላይ መፍሰስ ጀመሩ ማለት ነው፡፡
የክፍለ ከተሞች ብዛት
በ10 ክፍለ ከተሞች ተዋቅራ የኖረችው አዲስ አበባ የክፍለ ከተሞቿ የሕዝብ ብዛትም ኾነ የቆዳ ስፋት አለመመጣጠን አሰቃይቷታል፡፡ በተለይም በአስተዳደር ደረጃ 700 ሄክታር የሚኾነው ልደታም ሆነ 2ሺ ሄክታር የሚሰፋው ቦሌ ተመሳሳይ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ሲመድብለት ቆይቷል፡፡
ቦሌ ክፍለ ከተማ በማስፋፊያ ዞን ምክንያት ተለጥጦ አያት ጸበል ደርሶ፣ ቦሌ አራብሳን አልፎ የኦሮሚያ ድንበር አቁሞታል፡፡ ይህን ክፍለ ከተማ ለሁለት የመቁረስ ሐሰብ ከተጸነሰ ሰንብቷል፡፡ መሪ ፕላኑ ቦሌ ክፍለ ከተማን ለሁለት በመቁረስ ማስፋፊያው ላይ የሚገኙትን ቦሌ አራብሳ ክፍለ ከተማ ፣ ነባሮቹን ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚል ሰይሟቸዋል፡፡ ባልጠፋ ስም ለምን ሁለት ክፍለ ከተማ ቦሌ የሚል ቃል እንዲሸከም እንደሚደረግ ግን ግልጽ አይደለም፡፡ ሌላ አራብሳ የሚባል ክፍለ ከተማ ከሌለ ቦሌ የሚል ቅጥያን መጨመርስ ለምን አስፈለገ ስል ጠይቂያለሁ፡፡ አቃቂ ቃሊቲን ለሁለት የመከፈል እጣ ይገጥመዋል፣ ኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ ከአብራኩ ይወጣል፡፡
ወረዳዎችም በቁጥር መጠራታቸው ያበቃና ስሜት በሚሰጥ የሰፈር ስም ይተካሉ ተብሏል፡፡ አራት ኪሎ ወረዳ፣ ካዛንቺስ ወረዳ፣ ሽሮ ሜዳ ወረዳ እያለ ይቀጥላል፡፡
መርካቶና የሕንጻ ከፍታዋ
መርካቶ ትልቋ የቱሪስት ማግኔት መሆን የምትችል የአዲስ አበባ ላሊበላ ነበረች፡፡ ፎቅ ካልሰራ ልማት የማይመስለው ኢህአዴግ አበላሻት፡፡ አሁን ድንክ ፎቆች አጥለቅልቋታል፡፡ በ9ኛው መሪ ፕላን የመርካቶ የፎቅ ከፍታ አራት ብቻ ስለነበር ከዚያ ከፍ ያለ ቁመት ያለው ሕንጻ ለማቆም ሚሊዮን ብር ጉቦ መስጠት ግድ ነበር፡፡ በዚህ አዲሱ የከተማዋ እቅድ ይህ እግድ ተነስቶ ረዣዥም ፎቆችን በመርካቶ መገንባት ፈቅዷል፡፡
በአዲስ መሪ ዕቅድ መርካቶ የእግረኛ ገነት ትሆናለችም ተብሏል፡፡ ከጠዋቱ 12 ሰዓት አስከ ምሽቱ 12 ሰዓት የትኛም መኪና ወደ መርካቶ አይገባም፡፡ ከሕዝብ አውቶቡሶች በስተቀር የቤት መኪና እንኳ ዝር ማለት አይችልም፡፡ በመርካቶ ዳርቻዎች በሚገነቡ ሰፋፊ የመኪና ማቆምያዎችና መጋዘኖች ሰዎች ግብይታቸውን ይፈጽማሉ፡፡
የሕንጻ ከፍታ እንደ ቀድሞው በወለል ብዛት መወሰን በዚህ መሪ እቅድ ተሸሽሏል፡፡ በአራት ዞኖች ከተማዋን የሚፍላት አዲሱ ማስተር ፕላን በዞን አንድ የመሐል ከተማ ዝቅተኛው የግንባታ ከፍታ 70 ሜትር ነው፡፡ ይህ በወለል ሲመነዘር ወደ 10 ፎቅ ይደርሳል፡፡ በዞን አንድ የወለል ከፍታ ከፍተኛው ገደብ ወሰን የለውም፡፡
ዞን አንድ የሚባለው መሐል ፒያሳን ይዞ ብሔራዊን ለገሐርን እስከ ጨርቆስ ያካልላል፡፡ መሐለኛው የከተማዋ ክፍል እንደማለት ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የሚሰሩ ሁሉም ፎቆች 30 በመቶ ግንባታቸውን ለመኖያ ቤት ማድረግ ይገደዳሉ፡፡ ይህ በቅይጥ ግንባታ የመኖርያ ቤት የመገንባት ግዴታ ከመሐል ከተማ በሚወጡት ሰፈሮች እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ የዞን 2 ተብሎ በተያዘው የመገናኛ አካባቢ 40 በመቶ፣ የዞን 3 ተብሎ በተያዘው የከተማዋ ወጣ ያለ ክልል 50 በመቶ፣ የዞን አራት የከተማዋ ጥጋ ጥጎችና ድንበሮች እስከ 60 በመቶ የማንኛውም የሕንጻ ግንባታ መኖርያ መሆን ይኖርበታል፡፡
የመኖርያ ግንባታ ግዴታ የማይጣልባቸው ሆስፒታሎች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡
ለመሬት ቁጠባ ሲባል ሕንጻዎችን አስፋልት ጥግ አምጥቶ መገንባትን የሚፈቅደው ይህ መሪ ፕላን የሕንጻ ከፍታ ግዴታን በወለል ከመቁጠር ይልቅ የጥቅል ወለል ምጣኔ ዘዴን ይከተላል፡፡ በእንግዝኛው FAR (Floor Area Ratio) ይባላል፡፡ ሕንጻው ከቁመናው ማጠርና መርዘሙ ይልቅ በግንባታው መፍጠር የሚችለው ድምር የወለል ስፋት አስገዳጅነት አለው፡፡
በዚህ መሪ እቅድ ለከተማዋ 300 ግዙፍ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ይገነቡላታል፡፡ አሁን ደረጃቸውን የጠበቁ የከተማዋ መጸዳጃ ቤቶች ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ 60 የመኪና ማቆምያዎች ቦታዎችም ለከተማዋ ተለይተው ተይዘዋል፡፡
አፈጻጸሙ ግልጽ አይደለም
አዲስ አበባ እስከ አፍንጫው ስታቅድ የኖረች ከተማ ናት፡፡ ከተማዋን ለማጠር ያለመው ቀለበት መንገድ አሁን ከተማውን ለሁለት ከፍሎ የኑሮ ፈተና ሆኗል፡፡ በዚህ የከተማ ግንብ 14 አዳዲስ መተላለፊያ ድልድዮች ይገነባሉ ተብሏል፡፡ ከዓመታት በፊት ገርጂ የከተማው ጠረፍ ተደርጎ በመታሰቡ የኢንደስትሪ ዞን ተደርጎ ቆይቶ ነበር፡፡ አሁን በነዋሪዎች ተጥለቅልቋል፡፡ ፋብሪካና ቤት ተጎራብተዋል፡፡ በጀሞና ፉሪም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በሀና ማርያምም ነገሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ መስተዳደሩ ኢንዱስትሪዎች ከከተማ መውጣት እንዳለባቸውና በአንድ ዞን እጅብ ብለው መገንባት እንደሚኖርባቸው የተረዳው እጅግ ዘግይቶ ነው፡፡
በኢንደስትሪ ሳይሆን በአገልግሎት ዘርፍ እንጀራዋን ትጋግራለች የሚል አዲስ እቅድ የተያዘላት አዲስ አበባ እነ አሚቼን እነ ሞይንኮን፣ እነ ቢጂአይን፣ እነ አረቄ ፋብሪካን፣ እነ አዋሽ ወይን ጠጅን፣ እነ መከላከያን አባብላ ከከተማ ለማስወጣት ታልማለች፡፡ 10ኛው መሪ ፕላን ይህን በስሱ ይጠቁማል፡፡ አፈጻጸሙ ግን ግልጽ አይደለም፡፡ ጋራዦችን ሁሉ ለቅሞ አቃቂ ቃሊቲ ለመውሰድ ተሞክሮ አልተሳካም፡፡ አሁንም ፋብሪካዎችን ከከተማ መሐል የማስወጣቱ ሂደት አፈጻጸሙ ግልጽ አይደለም፡፡ ሕልሙ እንደማይተገበር ለመናገር ነብይ መሆን የማያስፈልገውም ለዚሁ ነው፡፡
ምራቅ የሚያስውጥ መሪ እቅድ
መሪ እቅዱን የሚተነትነው ሰነድ ሲነበብ ከገጽ ገጽ ምራቅ ያስዉጣል፡፡ ለምሳሌ በ10 ዓመት ዉስጥ በአዲስ አበባ የመኖርያ ቤቶች እጥረት ሙሉ በሙሉ ይቀረፋል ይላል፡፡ “ይቃለላል” ብሎ ትሁት ለመሆን እንኳ አይሞክርም፡፡ ሙሉ በሙሉ ይቀረፋል ብሎ ነው የሚደመድመው፡፡
አረንጓዴ ቦታን በተመለከተ አለም አቀፍ የ9 ኪሎ ሜትር የነፍስ ወከፍ የአረንጓዴ ሽፋን መመሪያ ተግባራዊ ሆኖ ሁሉም ወጣቶች በየመንደራቸው ሰፋፊ የመጫወቻ ቦታ ይኖራቸዋል ይላል፡፡
የትኛውም ነዋሪ ካለበት ከየትኛውም ስፍራ በአምስት ደቂቃ ርቀት ምቹና ቀልጣፋ የብዙኃን ትራንስፖርት ያገኛል ይላል፡፡ ይህ እቅድ በሰልፍ ርዝመት የሪህ በሽተኛ ለሆነው አዲስ አበቤ እያነቡ እስክስታ ነው፡፡
የቀላል ባቡሩ ከጦርኃይሎች ወደ ጀሞ፣ ከአያት ደግሞ ወደ ጣፎ መርዘም ብቻ ሳይሆን የመሬት ለመሬት ተምዘግዛጊ ባቡሮች እንደሚገነቡ፣ ለሕዝብ አውቶቡስ ብቻ የሚተዉ የመሐል አስፋልቶች ግንባታ እንደሚጀመር፣ እግረኞችን ብቻ የሚያስተናግዱ ሰፋፊ መንገዶች እንደሚገነቡ፣ ከብሔራዊ ቴአትር እስከ ኩባ አደባባይ ለትራፊክ ዝግ ሆኖ የእግረኛ መንሸራሸሪያ ብቻ እንደሚሆን፣ በአካባቢው የሚገኘው የመከላከያ ሚኒስትር አጥሩ ፈርሶ ክፍት ሙዝየም እንደሚደረግ፣ ታላቁ ቤተመንግሥት፣ ግዮን ሆቴልና ፍልዉሀ አጥራቸው ፈርሶ አንድ ትልቅ የሕዝብ ፓርክ እንደሚወጣቸው ከዘረዘረ በኋላ በአዲስ አበባ አርቴፊሻል ሀይቅ ተሰርቶ የጀልባ ሽርሽር የሚካሄድባቸው ቦታዎችን እስከመለየት ይሄዳል፡፡
ይህን ጊዜ ታሳሪው መረራ ጉዲና ታወሱኝ፡፡ ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ ይሉ ነበር፡፡
ቢኾንም ቢኾንም
ካለማለም፣ ማለም ሳይሻል አይቀርም፡፡