(ሙሄ ሐዘን ጨርቆስ)
በድምፅ የተሰናዳውን ጦማር እዚህ ያድምጡ
እንዴት ሰነበታችሁ! እኔ ያው ደህና ነኝ፡፡ የመሐል አገር ሰው ምን ይሆናል ብላችሁ?! ምን ቢከፋ ጦሙን አያድር!ከሰላምታዬ ቀጥዬ የማሳስባችሁ ነገር ቢኖር ስለዚህ ‹‹ቀላል›› እየተባለ ስለሚጠራው ‹‹ከባድ›› ባቡራችን ይሆናል፡፡
ከተማችን አዲሳባ ሰሞኑን ፍንክንክ ብላለች- እንደ አዲስ ሙሽራ፡፡ ሰበር ሰካ ትላለች- አንደ ዘበናይ ሴት፡፡ ወጣ ገባ አብዝታለች- ወጧ እንዳማረላት ባልቴት፡፡ ባቡሩ መዳህ ጀመረ፡፡ ብታምኑም ባታምኑም ባቡሩ ነፍስ ያላቸውን ብዙ ሰዎች በዉስጡ አሳፍሮ መሄድ ጀመረ፡፡ አሁን ይሄን ማን ያምናል? እንኳንም በዚህ ዘመን ተወለድኩ!
Thumbs up for the government! ይላል ፎርቹን ጋዜጣ ደስታ ተናንቆት በጻፈው ርዕሰ አንቀፁ፡፡ ‹‹ባቡሩ ለአደጋ እንዳይጋለጥ(አደራ)›› ይላል ሪፖርተር በተቆርቋሪነት በጻፈው ርዕሰ አንቀጹ፡፡ ‹‹ይህ ባቡር ከሚርመሰመስበት የአፍሪካ መዲና የሚተላለፍላችሁ የዛሚ ኤፍ ኤም ስርጭት ነው፤ ዛሚ ተደማጭ ተመራጭ ኤፍ ኤም…›› ትላለች ሚሚ ድምፅዋን የባቡር እንዲመስል ጎርነን አድርጋ፡፡
ሌላ ኤፍ ኤም ቀየርኩ፡፡ ስለ ባቡሩ ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡ አድማጮች ይጠይቃሉ፡፡ ባለሙያው ከጋዜጠኛው ጋር በመተጋገዝ መልስ ይሰጣል፡፡
“እሺ አድማጫችን ማን እንበል?”
“ሰሚራ ነኝ፤ ከቄራ”
“እሺ ሰሚራ ጥያቄሽ ምንድነው?”
“እ…የኔ ጥያቄ..እ.. ባቡሩ እስካሁን አደባባይ አልተሠራለትም፡፡ የቱ ጋ ነው የሚጠመዘዘው?”
“ጥሩ ጥያቄ ነው ሰሚራ…እናመሰግናለን፡፡ ለጥያቄሽ የባቡርና ፉርጎ ባለሙያው ወደ በኋላ ማብራሪያ ይሰጡበታል፡፡ ወደ ቀጣዩ አድማጫችን እንለፍ…ሀሎ…ከየት ነው ማን እንበል?”
“ዘሌ ነኝ ከግንፍሌ!”
“እሺ ግንፍሌ ቀጥል…ጥያቄህ ምንድነው?”
“ይቅርታ ግንፍሌ አይደለም ስሜ…ስሜ ዘላለም ነው…”
“እሺ…እሺ… ስምህ ማንም ቢሆን ችግር የለውም፤ ሌሎች አድማጮች መስመር ላይ ስላሉ ወደ ጥያቄህ እለፍ…”
“እሺ…በቅድሚያ እድሉ ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ፡፡ የኔ ጥያቄ ምንድነው…ሀዲዱ ላይ ስንሄድ ብዙዉን ጊዜ…” 
(ይሄኔ ባለሙያው ጣልቃ ገቡ) “እ…እዚህ ጋር ለሁላችንም ማስተካከያ ለመስጠት ነው…ይኸውም ምንድነው…”ሀዲዱ ላይ የሚጓዘው ባቡሩ ነው። እኛ እምንጓዘው በባቡሩ ውስጥ ነው…” እሺ አሁን መቀጠል ትችላለህ…ማነህ ግንፍሌ፡፡
======================
እኔ ተፀፀትኩ፡፡ ለባቡራችን ተገቢውን ክብር ባለመስጠቴ ተፀፀጽኩ፡፡ ለካንስ ይሄ ባቡር ከባቡርነት ወደ አድባርነት ተሸጋግሯል ጎበዝ!ላለፉት ጥቂት ወራት ባቡሩ በፖሊስ ሲጠበቅ አይቼ ‹‹እንደ ነብዩ ኤልያስ እንዳያርግ ፈርተው ነው?›› ብዬ ቀልጃለሁ፡፡ ይቅር ይበለኝ፡፡
ባቡሩን ቻይናዊ ሲነዳው አይቼ ‹‹ጥልያን ቁመቷን ቀንሳ አይኗን አጥብቦ ሾፌር ሆና መጣች ደግሞ›› ብዬ አላግጫለሁ፣ ይቅር ይበለኝ፡፡ ለነገሩ እኔ ብቻ አይደለሁም ባቡሩን በጥርጣሬ ሳየው የቆየሁት፡፡ ብዙ የሰፈሬ ልጆች ‹‹የቻይና ነው፣ ፎርጅድ ነው›› ሲሉ ነበር፡፡ እነርሱንም ይቀር ይበላቸው፡፡
ጭፍን ደጋፊዎች እንደመንኮራኮር፣ አክራሪ ካድሬዎች መንግስት ሰማያት እንደሚያደርስ የእሳት ሰረገላ፣ ጭፍን ተቃዋሚዎች በሆዱ እየተሳበ እንደሚሄድ ብረት ለበስ እባብ ቆጥረውት ነበር፣ ባቡሩን፡፡ በመጨረሻ መዳህ መጀመሩ ግን ታቃዋሚን ደጋፊንም እኩል አስፈንጥዟል፡፡ እንዴት ደስ አያሰኝም? በሦስት ዓመታት ምጥ የተወለደ የስዕለት ልጅ እኮ ነው፡፡ ከባላገሩ አይዶል እኩል ተጀምሮ ያለቀ የብረት ሸማ እኮ ነው፡፡ ‹‹ባቡሩ ሲመጣ›› የሚል መጽሐፍ በስሙ የታተመለት ተአምር እኮ ነው፡፡ እንዴት ደስ አያሰኝም? ቀላል ይሉታል ደግሞ፣ የሚያቀል ያቅልላቸውና፡፡
እውነት እውነት እላችኋለሁ የባቡሩ ነፍስ ዘርቶ መዳህ ሕዝቡንም መንግስትንም በእኩል ነው ያስደነገጠው ስላችሁ እመኑኝ፡፡ ለምሳሌ ‹‹የባቡር ሚኒስትራችን›› ዶክተር ጌታቸው በትሩ መቼለታ ለሪፖርት ጋዜጠኞች ምን አሏቸው፡፡ የሆድ የሆዳቸውን ነገሯቸው፡፡ ምን ብለው?
‹‹…ባቡሩን (እስካሁንም)…በጣም በጭንቀት ነው የምንከታተለው፡፡ በመጀመሪያዎቹ ቀናት በተለይ በጣም ፈርተን ነበር፡፡ ከአሁን አሁን የሆነ ነገር እንሰማለን ብለን፡፡…›› (ሪፖርተር፣መስከረም 18፣2008)
አሁን ይሄ የሰውየው ስሜት በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በኢንዱስትሪ አብዮት ጊዜ ስለተፈጠረ መጓጓዣ ባቡር የተባለ ነው የሚመስለው ወይስ አንድን መንኮራኮር ጨረቃ ላይ ለማሳረፍ ስለሚደረግ ሳይንሳዊ ሙከራ? ጉድ እኮ ነው ጎበዝ! ወደፊት ታሪክ ፀሐፊዎች የሚዘግቡት ንግግር ይመስለኛል፡፡ መጪው ትውልድ ከት ብሎ የሚስቅብንም ይመስለኛል፡፡ የሳቸው ሲገርመኝ ደግሞ ሌላ ምን ሰማሁ… ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሰሞኑን በነበረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ዉስጥ ለተሰበሰቡ የዓለም መሪዎች በሚያደርጉት ንግግር ዉስጥ የሚከተለው ዐረፍተ ነገር ይገኝበት ነበር ተባለ፤ ‹‹If there is one thing that makes the 70th session of the United Nations General Assembly unique is that it coincides with the inauguration of our first ever Light railway of Addis Abeba, the African capital!››
ባለቀ ሰዓት ነው አሉ የቅርብ አማካሪዎቻቸው እነ ዶክተር ተቀዳ ዓለሙ ተረባርበው ኒውዮርክ፣ 18ኛው ጎዳና በር ላይ ከሚገኝ ትንሽዬ ኪዮስክ ቀይ እስክሪብቶ ገዝተው ይህን አረፍተ ነገር የሰረዙባቸው፡፡
ይሄንን ተአምር ነው እንግዲህ ‹‹ቀላል›› እያሉ የሚጠሩት፣ የሚያቀል ያቅልላቸውና! ይሄ በሰፊው ሕዝብ ላይ እየተዘባበተ የሚተዳደረው ቲቪ ጣቢያማ ተውት፡፡ ባቡሩ ባርቆበታል አይገልጸውም፡፡ ከዜና አንባቢው ጀርባ ባቡሩ አለ፡፡ ሁልጊዜም ትልቅ የባቡር ፎቶ ገጭ ብሎ ነው ዜና የሚነበበው፡፡ የዛሬውን አያድርገውና ከዜናው አንባቢ ጀርባ የነበረው ትልቅ ፎቶ የታላቁን መሪ ምስል የያዘ ነበር፡፡ ታላቁን መሪ የተገዳደረ ብቸኛው ቁስ ባቡራችን ሆነ፡፡
ይሄንን ድፍን አንድ አገር ያርበደበደ ባቡርን ነው እንግዲህ ‹‹ቀላል›› እያሉ የሚጠሩት፡፡ የሚያቀል ያቅልላቸውና! እንግዲህ ባልኳችሁ ቲቪ አርእስተ ዜና ላይ ባቡሩ አለ፡፡ የአገር ዉስጥ ዜና አልቆ ከዉጭ ወደ ደረሱ ዜናዎች ለመሻገር ስለባቡሩ ቀጠን ያለ መረጃ ይሰጣል፡፡ ዜናው ሲያልቅ የቢዝነስ መረጃ አለ፡፡ እዛ ላይም እንዲሁ ስለባቡሩ የሆነች አጭር ዜና አትጠፋም፡፡ ከቢዝነስ መረጃ በኋላ ደግሞ የአየር ዘገባ አለ፡፡ እዚያ ላይም እንዲሁ የሰሞኑ አየር ለባቡር ትራንስፖርት ምቹ የሚባል እንደሆነ የሚጠቁሙ ነገሮች ይነገራሉ፡፡ ከዚያ የስፖርት ዘገባ ይቀጥላል፡፡
‹‹ጤና ይስጥልኝ አሁን የስፖርት ዘገባ የምናቀርብበት ሰዓት ላይ ደርሰናል፡፡ በቅድሚያ እግርኳስ፡፡
‹‹ባቡሩ ለስፖርት የሚሰጠው ፋይዳ የሚናቅ አለመሆኑን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች ገለጹ፡፡ ዝርዝሩን ሪፖርተራችን ሰባራው ባቡሬ ያቀርበዋል፡፡ (የሪፖርተሩ ስም ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ተቀይሯል)
‹‹የአዲስ አበባ የፕሪምየርሊግ ተሳታፊ ክለቦች ከልልምድ ሜዳዎች በሰዓቱ ወደ ስቴዲየም ለመድረስ ባቡሩ የማይናቅ ድርሻ እንደሚኖረው የክለብ መሪዎች ገለፁ፡፡ ይህ የተገለፀው ‹‹ስፖርትና የባቡር ፉርጎዎች ሚና›› በሚል ርዕስ በወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን አዳራሽ በተደረገ የግማሽ ቀን ሲምፖዚየም ነው፡፡ በሲምፖዚየሙ ላይ እንደተገለፀው የከተማ ባቡሩ በተለይ ከባምቢስ መስቀል አደባባይን አቋርጦ በቀኝ በኩል ወደ አምባሳደር መውጣት ሲችል በቀጥታ በስቴዲየም በኩል እንዲያልፍ መደረጉ መንግስት ምን ያህል ለስፖርቱ ትኩረት እንደሰጠ የሚያሳይ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ታራራራራም!
እንዲህ የተባለለትን ባቡር ነው እንግዲህ ‹‹ቀላል›› እያሉ የሚጠሩት፤ የሚያቀል ያቅልላቸውና!
የምር ግን! ያለማጋነን! ከ66ቱ አብዮትና ከ97ቱ ምርጫ በኋላ መንግሥትም ሕዝብም ለጉድ ያወራለት ግኡዝ ነገር ቢኖር ይሄ ‹‹ቀላል›› የሚባለው ባቡራችን አይመስላችሁም? እኔ ይመስለኛል፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም ብዙ ሰው ባቡሩ በክፉ ሲነሳ አይወድም፡፡ አሁን ይህ ደብዳቤ ራሱ ስንት ሰው እንደሚያናድድ አስቤ ተጸጽትኩ፡፡ ባቡሩ ሲተች እናታቸው በብልግና የተሰደበችባቸው ያህል ተሰምቷቸው ለመደባደብ የሚቃጣቸው ካድሬዎችም አጋጥመውኛል፡፡ ባቡሩን በተመለከተ በጋዜጣም ሆነ በመጽሔት ላይ አስቂኝ ካርቱን ይዞ መውጣት የሚያስከስስ ይመስለኛል፡፡ ደግነቱ ጋዜጣም መጽሔትም ተዘግቷል፡፡ ለማንኛውም ይሄንን ጉድ ነው እንግዲህ ‹‹ቀላል ባቡር›› እያሉ የሚጠሩት፤ የሚያቀል ያቅልላቸውና!!
ራሴን ጠየቅኩ፡፡ ይሄ ነገር በኛ የተፈለሰፈ፣ እኛ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ያስተዋወቅነው፣ በምድራችን ላይ ያልነበረ አዲስ ክስተት፣ አዲስ ግኝት ነው እንዴ? አይደለም፡፡ ታዲያ ምንድነው እንዲህ መደመም? ትንሽ አልበዛም? በዝቷል እንጂ! እውነት እንነጋገር ከተባለማ….ግማሽ ቢሊየን ዶላር በአራጣ ከቻይና ተበድረን፣ የቻይና ገንቢዎች እግር ስር ወድቀን፣ ሾፌርና ረዳት እንኳን ቻይናዊያንን አስመጥተን ያሳካነው ነገር አይደለም እንዴ? እውነት እንነጋገር ከተባለማ… በዚህ የባቡር ፕሮጀክት ዉስጥ እኮ ‹‹የኛ›› የምንለው ተሳፋሪውን ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ምንድነው ይሄን ያህል በየራዲዮው የባቡር ጡሩንባ እያሰሙ፣ ‹‹ትልቅ ነበርን! ትልቅም እንሆናለን!›› እያሉ ማንቋረር? ጉድ እኮ ነው!
ይሄ ባቡር እኮ መዲናችን አዲሳባን ለአውዳመት አዲስ ልብስ እንደተገዛለት የደሀ ልጅ አጃጃላት፡፡ የምሬን ነው፡፡ አልበዛም ግን!?! አንድ በሆዱ ብረት እየታከከ፣ በግንባሩ የኤሌክትሪክ ገመድ እየላሰ ለሚሄድ የሕዝብ ቁምሳጥን ይህን ያህል አምልኮ አልበዛም? በሏ ደግሞ ‹‹ስንቶች የተዋደቁለትን ልማት ቁምሳጥን ብለህ ተሳልቀሀል››ብላችሁ በሽብር ክሰሱኝ፡፡ ለነገሩ ሳናስበው ብዙ ርቀት ወደ ኋላ ተንሸራተን ነው እንጂ ነገሩ እንኳን ለዓለምም ለአገርም ባዳ አልነበረም፡፡ ‹‹መክሸፍ›› ይሉታል ፕሮፌሰሩ ይህን አይነቱን አጋጣሚ፡፡
እኔ እስከሚገባኝ ባቡር በጦቢያ ምድር አዲስ ሆኖ አያውቅም፡፡ ጎረምሶች በጋሽ አበራ ሞላ ሙዚቃ፣ የኔ ትውልድ መሿለኪያ ጋር ሳር በቅሎበትም በሚያብረቀርቅ ሀዲድ፣ የኔ ታናናሾች በአቡጀዲ ግርግር (ሲኒማ)፣ የኔ የታላቅ ታላቆች ድሬዳዋ ጣቃ ኮንትሮባንድ ሲነግዱ፣ ብቻ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ባቡርን ያውቁታል፡፡ “እንኳን እኛ የአጼ ምኒሊክ ባቾችም ያርፉታል” ነው ያለኝ አንድ ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በታሪክ ተመርቆ ሥራ ያጣ የጨርቆስ ልጅ በነገሩ ተናዶ፡፡ ለምን አይናደድ! ባቡር በዚች አገር ብርቅ ነው እንዴ? ታዲያ ምንድነው አስሬ በየኤፍ ኤሙ ‹‹ባቡሬ›› የሚለውን ሙዚቃ እየደጋገሙ ማስደለቅ፡፡
ደግሞ ከመንግስት የሕዝቡ ይባስ!? ባለፈው ሳምንት ሕዝቡን ከምር ስታዘበው ነበር፡፡ ታክሲ ጋቢና እያለለት በባቡር ለመሳፈር ሲያሽቋልጥ፤ ለስንት ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በአንቀልባ አዝሎ ያኖረውን አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ዶሮ ሦስቴ ሳይጮህ ክዶ ወደ ባቡር አሻግሮ ሲያማትር፤ አዳሜ የባቡር ሰረገላ ተደግፎ ፎቶ ሲነሳ፣ ‹‹ባቡር ዉስጥ ሆኜ ነው የማዋራህ›› እያለ ሲደዋወል- የአዲሳባ ሕዝብ ምን ነካው አልኩኝ፡፡ ብዙ ዜጎች ስማርትፎን አለመግዛታቸው ያስቆጫቸው ይህን “ታሪካዊ” አጋጣሚ ቀርጸው ለትውልድ ማቆየት ባለመቻላቸው መሆኑን ስረዳ ሸገር ምን ነካት አልኩኝ፡፡ ከአየርጤና፣ ከኮተቤ፣ ከጀሞ፣ ከለቡ፣ከካራ፣ ከዘነበወርቅ፣ ከሰሜን ማዘጋጃ፣ ከሩፋኤል ባቡሩን ለማየት የሚጎርፉ ብዙ ዜጎች ነበሩ ነው የተባለው፡፡
ይህ ነገር በንጉሡ ጊዜ አውሮፕላን ሲገባ ከተፈጠረው ሁኔታ በምን ይለያል? እስኪ አስረዱኝ…በምን ይለያል?
“….ነሐሴ 12፣1922 ዓ.ም የከተማው ሰው አውሮፕላኑ ለማየት ወደ ገፈርሳ ሜዳ ተጓዘ፡፡ ለመሄድ ያልቻለው በየደጁ ቆሞ ሽቅብ እያየ ይጠባበቅ ጀመር፡፡ በገፈርሳ ለአቀባበል ሰፋፊ ድንኳን ተተክሎ ተዘጋጀ፡፡ ድንኳኑም በአበባና በሰንደቃላማ ተሸላልሞ አጌጠ፡፡ የተጠሩት ብጹአን ጳጳሳት፣ ታላላቅ ሰዎች አንጋጠው ይጠባበቁ ጀመር፡፡ ሦስት ሰዓት ሲሆን ግርማዊ ንጉሥ ተፈሪ ሚኒስትሮቻቸውንና መኳንንቱን አስከትለው ገፈርሳ ደረሱ፡፡
ፈረንሳዊው ሙሴ ማዮም ከጧቱ በ1 ሰዓት አውሮፕላኑን ከጅቡቲ አስነሳና የሐዲዱን መስመር ተከትሎ በአየር ላይ ወደ አዲስ አበባ መብረር ጀመረ፡፡ 2 ሰዓት ሲሆን ድሬዳዋን አለፈ ተባለ፤ 3 ተኩል ላይ ሞጆን አለፈ ተባለ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ወሬው ስለጠፋ ምናልባት ወድቆ ተሰባብሮ ይሆናል የሚል ስጋትና ጥርጣሬ በሁሉም ልብ ተፈጠረ፡፡ የአብራሪው የሙሴ ማዮ ሚስት ማዳም ማዮ ገፈርሳ ላይ ሆና ትጠባበቅ ነበርና የአውሮፕላኑ ወሬ በመጥፋቱ ስለተጨነቀች ከግርማዊ ንጉሥ ፊት ቀርባ ስታለቅስ ያያት ሁሉ በሐዘን ተነሳ፡፡ ድንጋጤ ሆነ፡፡
… በሰባት ሰዓት ግድም ሙሴ ማዮ አዲሳባ ደርሶ በታላቁ ቤተመንግስት አንዣበበ፡፡ ይህም ለግርማዊት ዘውዲቱ ሰላምታ የማቅረብ ምልከት መስጠቱ ነበር፡፡ ቀጥሎም በግርማዊ ንጉሥ ተፈሪ መኖርያ ቤት ላይ አንዣቦ ድምጡን እያሰማ አለፈና ገፈርሳ ከሜዳው ላይ አረፈ፡፡ በዚህን ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ደስታውን በጭብጨባ ገለጠ፡፡ ንጉሡ ለሙሴ ማዮ የኮማደር ማዕረግ የሆነውን የኢትየጰጵ ክብር ኮከብ ኒሻን ሸለሙት፡፡ ከዚህ በኋላ ግብዣ ተደረገ፡፡ ከዚያም የአውሮፕላኑ የክርስትና ስም ንስረ ተፈሪ ተብሎ ተሰየመ፡፡ የክርስትናው አባትም የግርማዊ ንጉሥ ተፈሪ ታናሹ ልጅ ልዑል መኮንን ሆነው በአውሮፕላኑ ላይ ሻምፓኝ አፍስሰው አጠመቁት፡፡ (የሐያኛው ክፍለዘመን መባቻ፣ 371-372)
ይህ አስቂኝም አስደናቂ ታሪክ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሆነን ደገምነው፡፡ ባቡር የሚያስደንቀን ጉዶች ሆንን፡፡
ለባቡራችን የክርስትና ስም አወጣንለት፤ በንጉሥ ባይሆንም በኛ ሰፈር ተረበኛ ልጅ፡፡ባቡራችንን ‹‹ሞላ ዘገየ›› ብሎ ጠራው፡፡ ትርጉሙም ‹‹ይሞላልም ይዘገያልም›› የሚል ሆነ፡፡
በአዲሳባ ሕዝብ ከልክ ያለፈ አሽቋላጭነት ከመናደዴ የተነሳ በዚህ ባቡር መቼም ላልሄድ ቃል ገብቼ ነበር፡፡በመጨረሻ ተሸነፍኩ፡፡ “ወደፊት ለልጆቼ ምን አወራለሁ?” የሚል ሐሳብ መጣብኝ፡፡ ከትናንት በስቲያ ተሳፈርኩበት፡፡ አንድ ቢጫ ብጫቂ ሰጥተው 4 ብር ቀረጡኝ፡፡ ተፀፀጽኩ፡፡ የተፀፀትኩት በዋጋው አይደለም፡፡ ይህን ብጫቂ ትኬት ለማግኘት ሳሪስ ጋ 35 ደቂቃ መቆሜ ነው፡፡ ወረፋው ለጉድ ነው፡፡ ሰዉ ደግሞ ተናጋሪ ሆኗል፡፡ ‹‹እንኳን ከታክሲ ሰልፍ ወደ ባቡሩ ሰልፍ በሰላም አሸጋገረን›› ይባባላል፣ እንግልት ያደመነው ፈገግታ እየተለዋወጠ፡፡
ያሰብኩበት እስክደርስ ሌላ 25 ደቂቃ አልወሰደም ብላችሁ ነው? እውነትም ‹‹ሞላ ዘገየ›› አልኩ በሆዴ፡፡ ባቡሩ ዉስጥ መቀመጫ ኩርሲ ማግኘት ሾፌሩን መሆን ይጠይቃል፡፡ ወይም ከቻይናዊ ቤተሰብ መወለድን ይጠይቃል፡፡ የመተሳሰብ ባሕላችን ባስ ዉስጥ እንጂ ባቡሩ ዉስጥ ብዙም የሚሰራ አይመስልም፡፡ አንዲት አሮጊት ሴትዮ በቀኝ እጃቸው ምርኩዝ፣ በግራ እጃቸው የባቡሩን የብረት ዘንግ ይዘው ቆመው ሳለ ማንም ዉሪ ጎረምሳ ይቀመጡ አላላቸውም፡፡ ወገባቸው እየተንቀጠቀጠ 35 ደቂቃ ሙሉ ቆመው መጨረሻ ፌርማታ ላይ ወረዱ፡፡ እርሳቸውም ሕዝቡ ባቡር እንደባረቀበት ተረድተው ነው መሰለኝ ቁልጭ ቁልጭ የማለት ነገር እንኳን አላሳዩም፡፡ የምኒሊክ ዘመን ሰው ይመስሉኛል፡፡ ለርሳቸው ባቡር ብርቅ አይደለም፡፡
ታዲያ ባቡሩ ዉስጥ ሆኜ አንድ አስገራሚ ነገር አስተዋልኩ፡፡ ብታምኑም ባታምኑም ሰው ሁሉ አማትቦ ነው የሚሳፈረው፡፡ ወደ ባቡሩ የሚገባው ሰው በሙሉ ከተቀያሪ ወንበር ወደ ሜዳ እንደሚገባ ተስፈኛ የእግር ኳስ ተጫዋች ያማትባል፡፡ የሚያማትበው ዜጋ ቁጥር ሲበዛብኝ ጊዜ “ይሄ ባቡር ታቦት ጭኗል እንዴ?” አልኩት ከጎኔ ለቆመ ጎልማሳ፡፡ ገላምጦኝ ፊቱን አዞረ፡፡ ደግሞ የአጋጣሚ ነገር ይሁን አላውቅም ባቡሩ ሲጓዝ እንደታቦት ተሸካሚ ቄስ በዝግታ ነው፡፡ ፈጠነ ከተባለ በሰዓት 20 ኪሎ ሜትር እንጂ ከዚያ አይዘልም፡፡ ከሳሪስ ሰፈሬ ለመድረስ ሙሉ 35 ደቂቃ ፈጀብኝ፡፡
ባቡሩን ሳነሳ ስንት ነገር ትዝ አለኝ መሰላችሁ፡፡ ድሮም ባቡር “የትዝታ ፉርጎ” አይደል የሚባለው? ግን በዚህ ስልቹ ዜጋ በበዛበት ዘመን ትዝ ያለ ነገር ሁሉ አይጻፍም ብዬ ተውኩት፡፡ ለማንኛውም ባቡራችን ላይ ከሆነው ይልቅ ወደፊት የሚሆነውን ሳስብ ፈገግ እላለሁ፡፡
ከዚህ በኋላ ባቡር ተኮር ነጠላ ዜማዎች ይበዛሉ፡፡ ባቡር የሌለበት ፊልምና ድራማ ይናፍቀናል፡፡ ከባቡሩ ጋር የተገናኙ የዘፈን ግጥሞች ከመብዛታቸው የተነሳ ‹‹ር›› በሚል ፊደል ቤት የሚመቱ ስንኞች ይበዛሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ወይ እናት ኢትዮጵያ ወይ አንቺ አገር፣ ብረር ብረር አለኝ ልክ እንደ ባቡር፡፡ ከዚህ በኋላ ኢህአዴግ ማንኛውም ትችት ሲቀርብበት መልስ የሚሰጠው ከባቡር ጋር የተያያዘ ዘጋቢ ፊልም በመስራት ይሆናል፡፡ የቲቪ እሁድ መዝናኛና ህብረትርኢት ከእንግዲህ ባቡሩ አካባቢ ነው የሚቀረፀው፡፡ ከቢዝነስና ከአየር ዘገባ ቀጥሎ በየዜናዎች ‹‹የባቡር ዘገባ›› የሚባል አዲስ ፕሮግራም ይጀመራል፡፡
የአዲሳባ አዳማ ፈጣን መንገድን የጎበኘው ታጋዳላይ አንዳርጋቸው ጽጌ በድጋሚ ቱታ ለብሶ፣ ባቡሩን ተደግፎ፣ ‹‹ፈገግ በል›› ተብሎ ፎቶ እንዲነሳ ይደረጋል፡፡ ይህንን ነው እንግዲህ ‹‹ቀላል ባቡር‹‹ የሚሉን፤ የሚያቀል ያቅልላቸውና!