ኢትዮያውያት ሴተኛ አዳሪዎችን ዕርቃን ምስል የሚያሳይ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን በኒዮርክ ለዕይታ ቀረበ።
“New Flower: Images of the Reclining Venus” በሚል ርዕስ የቀረበው የፎቶ ኤግዚቢሽን የተዘጋጀው አወል ሪዝኩ በሚባል ወጣት ትውልደ ኢትዮጵያዊ አርቲስት አማካኝነት ነው። ይህ የራቁት ፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን አርቲስቱ አወል የወላጆቹን የትውልድ አገር ኢትዮጵያን ለመጎብኘት በሔደበት ጊዜ ያነሳቸውን በአዲስ አበባ ያገኛቸውን ሴተኛ አዳሪዎች ፎቶግራፎች የያዘ ነው።
(መዝገቡ ሀይሉ ዝርዝር ዘገባውን አዘጋጅቶታል ከታች ያድምጡ)
የፎቶግራፎቹ ሞዴሎች ኾነው የቀረቡት ሴቶች በፎቶግራፉ ላይ የሚታዩት ፎቶግራፋቸው በተወሰደበት የአዲስ አበባ ሆቴሎች የማደሪያ ክፍሎች ውስጥ በአልጋ ላይ ርቃናቸውን ጋደም እንዳሉ ነው። አርቲስቱ እነኚህን ሴቶች ፎቶግራፍ ያነሳበት መንገድ በአውሮፓ “renaissance” ተብሎ በሚታወቀው ዘመን በተሰሩትና በግሪካውያኑ የፍቅር አምላክ ቬኑስ ስም በተሰየሙ ታዋቂ ሥዕሎችና ቅርጻ ቅርጾች የአሰራር ዘይቤ ነው።
የ27 ዓመት ወጣት የኾነው አርቲስቱ አወል ይህን የመሰለ የሥነጥበብ ዘይቤ በመከተል በሚያቀርባቸው የፎቶግራፍ፣ የቅርጻቅርጽ እና የፊልም ሥራዎቹ ተወዳጅነትን ያተረፈ ባለሞያ ነው። የሥነጥበብ ሥራዎቹ የሚለዩት ታዋቂ ከኾኑ ጥንታዊ ሥራዎች ጋር ባላቸው መመሳሰል ነው። ያም ኾኖ ግን በሥራዎቹ የሚታየው ከነዚህ ታዋቂ ጥንታዊ ስዕሎችና ቅርጾች ጋር ያላቸው መመሳሰል ብቻ ሳይኾን ኾን ተብሎ የተፈጠረውም ተቃርኗቸው ነው። በጥንታውያኑ ምስሎች ላይ ሞዴል ኾነው የተሳሉት ወይም የተቀረጹት ሴቶች ነጮች ብቻ ናቸው። እነኚህ ዘረኝነት እንደ ነውር ባልተቆጠረበት ዘመን የተሰሩ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ጥቁር ሞዴሎችን የጥበቡ አካል አድርገው አለማቅረባቸው ብዙም የማያስደንቅበት ዘመን ላይ ነው የተሰሩት። ከዚህም በከፋ መልኩ ጥቁሮች በወቅቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ የተሰጣቸውን ዝቅ ያለ ደረጃ የሚያሳዩ ብዙ የሥነጥበብ ሥራዎችም ተሰርተው ነበር። የአወል ሥራዎች ተቃርኖ የሚነሳውም ከዚሁ የጥንታውያኑን የሥነጥበብ ሥራዎች ባህርይ ነው።
“ከልጅነቴ ጀምሮ ሙዚየምና ጋለሪዎች ስጎበኝ ጥቁሮችን የሚያሳዩ ሥራዎች ብዙም እንደሌሉ ተረዳሁ” የሚለው አወል ገና በልጅነቱ ይህን ጉዳይ በመቃረን የሚቆም ሥራ ለመስራት ለራሱ ቃል መግባቱን ይናገራል። በመኾኑም ሥራዎቹ ላይ የሚታዩት ሞዴሎች ጥቁር እንዲኾኑ ከማድረጉም በላይ በታዋቂዎቹ የሥነጥበብ ሥራዎች ላይ የሚታዩትን ሞዴሎች የተለመደ አቋቋም ዘይቤ እንዲከተሉ ያደርጋል።
ሁሉም ሞዴሎች በጥንታውያኑ ስዕሎች መሰረት ራቁታቸውን የቆሙ ናቸው። ነገር ግን እንደታዋቂዎቹ ሰዓሊዎች ሙሉ በሙሉ ሐፍረታቸውን ለማሳየት እርሱም እንዳልፈለገ የእነሱም ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ ክብር እንዳልፈቀደላቸው ይናገራል።
ፍላግ አርት ፋውንዴሽን በተባለ ድርጅት ረዳትነት የቀረበው ይህ የስዕል ኤግዚቢሽን እስከ ዲሴምበር 12 ድረስ ለዕይታ እንደቀረብ ይቆያል።
ከስድስት አመት በፊት በኢትዮዽያ ተመሳሳይ ዕርቃን የፎቶ ኤግዚቢሽን ለማሳየት የሞከረው የፎቶ ባለሙያ ቢንያም መንገሻ በመጨረሻ ሰአት ዝግጅቱን እንዲሰርዝ በመንግስት ባለስልጣናት መገደዱን በዝግጅቱ ታዳሚ የነበሩ ምንጮቻችን ይናገራሉ። ቢንያም በአሁኑ ጊዜ በስደት በአውሮፓ ይኖራል። ዕርቃን የፎቶ ጥበብ ወትሮም ነገርን አክርሮ ለሚያየውና በባህላዊና ሀይማኖታዊ ጉዳዮች ረድፍ ለሚሰለፈው ማህበረሰባችን ለመቀበል የሚቸግር ዘርፍ ነው።