ዋዜማ ራዲዮ- ለኦህዴድ ካድሬዎች እንኳ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የአቶ አባዱላ የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ እያነጋገረ ነው፡፡ ለፓርቲው ቅርብ ነን የሚሉ ሰዎች የአባዱላን ‹‹ድንገተኛ›› እርምጃ በጥልቅ ታስቦበት የተደረገና አዲሱ የኦህዴድ አመራር እየተዳከመ ለመጣው ማዕከላዊው መንግሥት የላከው አደገኛ መልዕክት አድርገው ይወስዱታል፡፡
ከማስተር ፕላኑ ጥያቄ አንስቶ በኦሮሚያ ክልል እስከሚከሰቱ ጥቃቅን ግጭቶች ድረስ በየአካባቢው እየዞሩ ሕዝብን ሲያረጋጉ የኖሩት አቶ አባዱላ ከኦሮሞ ሕዝብ የሚቀርብላቸው ‹‹የተጨቁነናል፤ በቃን›› አቤቱታ ተስፋ የተሞላበት ምላሽ ሲሰጡ ቢከርሙም በሶማሊያ የልዩ ኃይልና በመከላከያ ሠራዊቱ ተፈጸመ የተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ከተመለከቱ በኋላ ልባቸው እየሻከረ እንደመጣ ይነገራል፡፡
መሹዋለኪያ አካባቢ ከሚገኘው የኦህዴድ ጽሕፈት ቤትና የዶክተር ዐብይ አሕመድ ቢሮ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት አቶ አባዱላ ከአፈጉባኤነታቸው ተነስተው በድርጅታቸው የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ በአዲሱ የኦህዴድ አመራር ግፊት ሲደረግባቸው ቆይተዋል፡፡ ምናልባትም የኦሮሚያን አዲሱን የኢኮኖሚ አብዮት የሚመራ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው የመቀጠል እቅድ እንዳላቸው ይሰማል፡፡
ከአፈ ጉባዔነት ለመልቀቅ በጠየቁ በሶስተኛው ቀን ማክስኞ ዕለት ከአንድ የውጪ ኩባንያ ጋር የተደረገ የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት የኦሮሚያ ክልል መንግስትን ወክለው ተፈራርመዋል። ይህ ክስተት የአባዱላን ቀጣይ የሰራ ድርሻ አመላካች አድርገው የወሰዱት ብዙ ናቸው።
ራሱን በአዲስ መልክ እያዋቀረ የሚገኘው የዶክተር ዐብይ አህመድ የድርጅት ጽሕፈት ቤት ‹‹እስከዛሬ እርምጃ ላይ ነበርን፣ ከአሁን በኋላ ግን እንሮጣለን›› የሚል መርህ በማንገብ ራሱን ለከፍተኛ ለውጥ እያዘጋጀ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በቅርቡም 25 የሚሆኑ ከፍተኛ ካድሬዎችን ወደ ርዋንዳ፣ ቻይናና ሌሎች የሩቅ ምስራቅ አገሮች ለልምድና ልዩ ስልጠና በሚል የላካቸው ሲሆን የኦሮሞ ምሁራንን ያካተተ ሌላ ቡድን ደግሞ ፓርቲውን በተሻለ ቁመና ለማቆም የሚያስችል ሰፊ ጥናት በማድረግ አዲስ ሰነድ በማዘጋጀት ተጠምዷል፡፡
‹‹አውቀንም ሆነ ሳናውቀው ወንበሩን ይዘናል፤ ላረጋግጥላችሁ የምችለው ሕዝባችን እውነተኛ ሥልጣንን አጎናጽፈን ለመጪው ትውልድ ከማስረከብ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለን ነው›› የሚሉት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ከፍ ያለ ተቀባይነት እያገኙ መጥተዋል፡፡
አቶ በከር ሻሌን ከፖለቲካ መድረክ ገለል በማድረግ የሦስትዮሽ አመራርን የያዙት አቶ ለማ መገርሳ እንደ አባት የሚታዩትን አቶ አባዱላን ከጎን ለማሰለፍ ብርቱ ጥረት እንዳደረጉ ይነገርላቸዋል፡፡ አቶ አብይ አህመድም የዚሁ የሦስትዮሽ አመራር አንድ ማዕዘን ናቸው፡፡
አቶ አባዱላ ከአፈጉባኤነት ተነስተው በፌዴራል የማንኛውም እርከን ሥልጣን ላይ ይቀመጣሉ ብለው እንደማያምኑ የሚናገሩ ማካከለኛ ካድሬዎች ወደ እናት ፓርቲያቸው የማይመለሱ ከሆነ የአቶ አባዱላ የፖለቲካ ዘመን ፍጸሜ ይታወጃል ሲሉ ይተነብያሉ፡፡
አባዱላ ስልጣኔን “ልልቀቅ” ጥያቄ ያቀረቡት ከብዙ ድርድርና ክርክር በኋላ ሲሆን ጥያቄያቸው ከአንጋፋ የፓርቲ ሹማምንት ተቃውሞና ልምምጥ እንደገጠመው ለጉዳዩ ቅርብ ነን የሚሉ ይናገራሉ።
አባዱላን ከሙስና ጋር በተያያዘ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል የመከሩና ያስመከሩ የቅርብ ወዳጆቻቸው እንደነበሩና በአንድ የቢሮ ውስጥ ውይይት አባዱላ ክፉኛ ተበሳጭተው ወደመኖሪያ ቤታቸው ሲሄዱ ተመልክቻለሁ ይላል በበታች ስራተኝነት የሚያገግል አንድ የኦህዴድ አባል።
የቀድሞ የደህንነት መስሪያቤት ባልደረባ የነበሩት አባዱላ ገመዳ “ለትግሉ የከፈልኩትን ዋጋ ታሪክ ይፈርደዋል” በማለት ለቀረቡባቸው ውንጀላዎችና ተቃውሞዎች ምላሽ ሲሰጡ ከርመዋል።
በመጨረሻ አራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በታደሙበት ስብሰባ የአባዱላ ስልጣን መልቀቅና ሸግግሩ እንዴት መሆን እንደሚገባውና ለህዝብና ለፓርቲው አባላት እንዴት መገለፅ እንዳለበት ከስምምነት ተደርሶ መለያየታቸውን በከፍተኛ ሀላፊነት ላይ ያሉ የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ባልደረባ ተናግረዋል።
የአባዱላ መልቀቅ የፖለቲካ ቀውሱን መባባስ አመላካች ነው በሚለው የማይስማሙት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች መምህር በበኩላቸው “እኔ የማውቀውና አባል የነበርኩበት ፓርቲ ያለ አንዳች ምክንያት አንጋፋውን የኦሮሞ ፖለቲካኛ መልቀቂያ ሊቀበል የሚችል አይመስለኝም” ይላሉ።
“ይልቁንም ፓርቲው ከገባበት ቀውስ ለመውጣት የተወሰደ እርምጃ ይመስለኛል” አንድም ግለሰቡ ላይ ከፍተኛ ተጠያቂነት የሚያስከትል ማስገደጃ ስበብ ተገኝቶ አልያም ለአዲስ ሀላፊነት ለመመደብ ታስቦ ሊሆን እንደሚችል ግምት ያስቀምጣሉ መምህሩ።
“በኔ አስተያየት ገዥው ፓርቲ በኦሮሚያ የተባባሰውን ቀውስ ለመፍታት አዳዲስ እቅዶችን ከማዘጋጀቱ ጋር ተያይዞ አባዱላ ከፌደራሉ ይልቅ በክልሉ ጉዳይ እንዲሳተፉ ለማስቻል የተቀየሰ ዘዴ ይመስለኛል” ብለውናል።