ዋዜማ- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት እና የግል ድርጅት ሠራተኞች ውዝፍ ደሞዝ ላይ የስድስት ወራት ዕገዳ መጣሉን ዋዜማ ከምንጮቿ ተረድታለች።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 2015 ዓ.ም. ድረስ ላሉት ሃያ አምስት ወራት ሠራተኞቹ ያልተከፈላቸው ውዝፍ ደሞዝ፣ የመጨረሻ መፍትሄ እስከሚሰጠው ድረስ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለቀጣዩ ስድስት ወራት አልቀበልም ብሏል።
ዋዜማ የተመለከተችው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ፊርማ ያረፈበት እና ለተለያዩ የክልሉ ቢሮዎች የተላከው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ በጉዳዩ ላይ መፍትሄ እስከሚሰጥ ድረስ ለባለፉት ስድስት ወራት ተጥሎ የነበረው ዕግድ ለተጨማሪ ስድስት ወራት ተራዝሟል።
ደብዳቤው በጉዳዩ ላይ ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርብ ጥያቄ እና በፍርድ ሂደት ላይ ያለ ጉዳይ፣ ጥናት ተደርጎ መፍትሄ እስከሚያገኝ ድረስ ተጥሎ የነበረው ዕግድ፣ የኢንዱስትሪ እና የፋይናንስ ቢሮዎች ባቀረቡት ጥያቄ ምክንያት ለተጨማሪ ስድስት ወራት ማራዘሙን ይገልጻል።
በደብዳቤው ላይ እንደተመለከተው፣ ኢንዱስትሪ ቢሮው እስካሁን ስላደረገው ጥናት እንዲሁም ፋይናንስ ቢሮው በበጀት ጉዳይ ላይ እስከዛሬ ስለተደረጉ ጥረቶች ሪፖርት በማቅረብ የጥናት ጊዜው እንዲራዘምላቸው ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ጥያቄ አቅርበዋል።
በዚህ መሰረትም፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ባደረገው ስብሰባ፣ የጥናት ጊዜውን ለተጨማሪ ስድስት ወራት እንዲራዘመ መወሰኑ ታውቋል።
ውዝፍ ደሞዝ ይከፈለን የሚለውን ጥያቄያቸውን ወደ ፍርድ ቤት እንዳይወስዱ ዕገዳ ከተጣለባቸው ድርጅት ሠራተኞች መካከል፣ አድዋ ከተማ የሚገኘው የአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሠራተኞች ይገኙበታል። እነዚሁ የአልመዳ ፋብሪካ ሠራተኞች ለዋዜማ ባቀረቡት ቅሬታ ፣ ለስድስት ወራት ተጥሎ የነበረው ዕገዳ በተያዘው ወር ይነሳል በሚል ሲጠባበቁ ለተጨማሪ ስድስት ወር መራዘሙ አግባብ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
‘ፋብሪካው ደሞዝ መክፈል ካቆመ ሦስት ዓመታት አልፎታል’ ያሉን የፋብሪካው ሠራተኞች፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ከተከፈላቸው የጥቂት ወራት ደሞዝ በስተቀር እስካሁን ደሞዛቸው እንደተቋረጠ መሆኑን ለዋዜማ ነግረዋታል።
ከዚህ ባለፈም፣ ከወራት በፊት ጥያቄያቸውን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱት የፋብሪካው ሠራተኞች፣ ፋብሪካው ካለው ንብረት ላይ የተወሰነውን በጨረታ ሸጦ ደሞዛቸውን እንዲከፈላቸው ፍርድ ቤቱ ቢወስንላቸውም፣ ጨረታውን ያሸነፈው ግለሰብ እስከአሁን ጨረታውን ያሸነፈበትን ብር ሊከፍል ባለመቻሉ ውሳኔው ተግባራዊ አለመደረጉን ይናገራሉ።
“ደሞዛችንን ማግኘት ባለመቻላችን ለረሃብ፣ በሽታ፣ ስደት እና ልመና ተጋልጠናል” ሲሉም ምሬታቸውን ለዋዜማ ገልፀዋል።
ፋብሪካው አሁን ላይ፣ ከጦርነቱ በፊት ከነበሩት አምስት ሺህ ገደማ ቋሚ ሠራተኞች መካከል፣ ወደ ሁለት ሺህ የሚደርሱትን ብቻ ወደ ሥራ እንዲመለሱ በማድረግ በከፊል ሥራ መጀመሩ ታውቋል። ከአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሠራተኞች በተጨማሪም፣ በኤፈርት ስር በሚተዳደሩት ሌሎች ድርጅቶች ዘንድም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች መኖራቸውን ዋዜማ ተገንዝባለች።
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ በክልሉ የሚኖሩ አንድ ጠበቃ በበኩላቸው፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሠራተኞቹ በጦርነቱ ወቅት ያላገኙትን የውዝፍ ደሞዝ ጥያቄ ላለመመለስ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ደንብ ማውጣቱን ለዋዜማ ገልጸዋል። እኒሁ ጠበቃ፣ ለዚሁ ተብሎ በጊዜያዊ አስተዳደሩ በቅርቡ ወጥቷል ባሉት ‘ደንብ 4/2016’ መሰረት፣ ሠራተኞቹ በጦርነቱ ወቅት ያልተከፈላቸውን ውዝፍ ደሞዝ በተመለከተ ክስ ከማቅረብም ሆነ ከመጠየቅ ይታገዳሉ።
እንደ ዋዜማ ምንጮች ገለጻ፣ ከመንግሥት ሠራተኞች ይልቅ በኤፈርት ስር ያሉ የተለያዩ ድርጅት ሠራተኞች፣ በጦርነት ወቅት ያልተከፈላቸውን ውዝፍ ደመወዝ ለማግኘት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ክስ መስርተው ነበር። በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች በተለይ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ደሞዛቸው በቋሚነት እየተከፈላቸው ሲሆን፣ የድርጅቶች እና ፋብሪካዎች ሠራተኞች ግን አብዛኞቹ ደሞዛቸው እስከአሁን ተቋርጦ እንደሚገኝ ተሰምቷል።
ከክልሉ መንግሥት በኩል የኢንዱስትሪ ሠራተኞች ደሞዝ እስከአሁን የተቋረጠበት ምክንያት፣ ተቋማቱ በጦርነቱ ወቅት በደረሰባቸው ጉዳት የተነሳ በቀላሉ ማገገም እና ወደ ሥራ መመለስ ባለመቻላቸው ነው ።
ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የክልሉን ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊዎች ለማናገር ጥረት ያደረገች ሲሆን፣ አንድ የቢሮው ኃላፊም፣ ስለጉዳዩ ሲወራ ከመስማታቸው በስተቀር መቼ እና እንዴት እንደተወሰነ እንደማያውቁ ነግረውናል። የመንግሥት ሠራተኞች እና የግል ድርጅት ተቀጣሪዎች በጦርነቱ ወቅት ስላልተከፈላቸው ደመወዝ የሚያነሱት ጥያቄ ላይ ለስድስት ወራት ዕግድ የተጣለ መሆኑን ግን፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ካሰራጨው ደብዳቤ ‘እንደተገነዘቡ’ ገልጸዋል። ኃላፊው አክለውም፣ ዋዜማ የተመለከተችው የጌታቸው ረዳ አስተዳደር ደብዳቤ ላይ እንደተጠቀሰው፣ ኢንዱስትሪ ቢሮው ተጥሎ የነበረው ዕገዳ ለተጨማሪ ስድስት ወራት ይራዘምልኝ ብሎ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ጥያቄ ማቅረቡን ጭምርም እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ሆኖም ጉዳዩን ሊያውቁ የሚችሉት የቢሮው አመራሮች ስለሚሆኑ እነሱ ሃሳብ ቢሰጡ የተሻለ እንደሚሆን የገለጹልን ቢሆንም፣ የኢንዱስትሪ ቢሮው ኃላፊ፣ በተደጋጋሚ የተደወለላቸውን ስልክ ባለማንሳታቸው ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም። ጊዜያዊ አስተዳደሩ በተቋቋመበት ወቅት፣ በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ለሁለት ዓመት ደሞዝ ያልተከፈላቸው የመንግሥት እና የግል ሠራተኞች ደሞዛቸውን እንዲያገኙ ጥረት እንደሚያደርግ መግለፁ ይታወሳል። [ዋዜማ]