ዋዜማ ራዲዮ-የቱርክ መንግስት በትግራይ ነጋሽ የሚገኘውን የንጉስ አርማህ ወይም ነጃሺ የመቃብር ስፍራ እድሳት እያጠናቀቀ መኾኑን አስታውቋል።
እድሳቱን እያከናወነ የሚገኘው የቱርክ የትብብርና ቅንጅት ኤጀንሲ (Turkish Coopration and Coordination Agency) በመባል የሚታወቀው የቱርክ የተራድዖ ድርጅት ነው። በእድሳቱ በእስልምና ሐይማኖት ተከታዮች ዘንድ ነጃሺ በሚል ስም የሚታወቁት የአክሱም ንጉስ መቃብር እና በአካባቢው የሚገኘው የ አልነጃሺ መስጊድ ዳግመኛ ከመታደሳቸው በተጨማሪ ስፍራውን ለሚጎበኙ ተሳላሚዎች የሚያገለግል የምግብ እልፍኝ (food court) እና 500 ሰዎችን በአንድ ጊዜ ሊይዝ የሚችል የመሰብሰብያ አዳራሽም እንደሚገነባለት ታውቋል። የመቃብር ስፍራው የሚገኝባትን የ ነጋሽ ከተማ ያለባትን የውኃ ችግር የሚቀርፍም የውኃ ማጠራቀሚያ እንደሚገነባ ኤጀንሲው አስታውቋል።
የነጃሺ መቃብር ለዓለም ዓቀፍ ሙስሊሞች ትልቅ ክብር ከሚሰጣቸው የሐይማኖታዊ ጉዞ መዳረሻዎች አንዱ እንደመኾኑ መጠን የቱርክ መንግስት ይህን ታሪካዊ ስፍራ ለማደስ ያደረገው ድጋፍ ሐይማኖታዊ ተልእኮ ተደርጎ የሚታሰብ ነው። የንጉስ አርማህን ባለውለታነት በዓለም አቀፍ ሙስሊሞች ዘንድ እንዲታሰብ ያደረገውም የእስልምና ሐይማኖት በተጀመረበት በሰባተኛው መቶ ክፍለዘመን የመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች በአገራቸው በደረሰባቸው ስደት ምክንያት መጠጊያ ሲሹ እጃቸውን ዘርግተው የተቀበሏቸው ብቸኛ የዓለም መሪ ስለነበሩም እንኾነ የእስልምና የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዘንድ የንጉስ አርማህ ታሪክ በተለየ ሁኔታ መወሳት ም ጀምሯል። ንጉስ አርማህ ለብዙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ንጉስ ተደርገው በመወሰድ የኩራት ምንጭ እንደኾኑም ይነገርላቸዋል።
ምንም እንኳን የንጉስ አርማህም ኾነ የሌሎች የዚያ ዘመን የአክሱም ነገስታት ታሪክ ከመረጃ መጥፋት ምክንያት ብዙ የማይታወቅ ቢኾንም ንጉስ አርማህ ግን እንደ እስልምና እምነት ባለውለታነታቸው በእስልምና ድርሳናት ውስጥ በተሰጣቸው ስፍራ ምክንያት እስካሁን ድረስ ስማቸው ለመጠራት የበቁ አክሱማዊ ንጉስ ኾነዋል። ምናልባትም በእስልምና እምነት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ከተሰጣቸው ቀደምት ኢትዮጵያውያን መካከል ከእስልምናው ነቢይ ሙሐመድ ጋር የቀረበ ትውውቅ ከነበራቸው ኢትዮጵያዊቱ የነብዩ አሳዳጊና የጸሎት ማንቂያ የኾነውንና አዛን በመባል የሚታወቀውን ጥሪ የጀመሩት ሌላው ኢትዮጵያዊ ቢላል ጋር ተጨምሮ በነቢዩ ሙሐመድ ዘንድ ስለኢትዮጵያ መልካም ዝናን ሳያተርፉላት እንዳልቀሩም ይገመታል።
በእስልምና የታሪክ መዛግብት ስለንጉስ አርማህ የተጻፈውን ትውፊት በመመልከት ብቻ እንኳን ንጉሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያስመሰግናቸው የሚያስችላቸው ብዙ ጉዳይ አለ። በሐይማኖታቸው ምክንያት በግፍ ተሰደው የነበሩትን ሰዎች ተቀብለው ጥበቃ በመስጠታቸውና በሐይማኖታቸው ምክንያት ተጽእኖ ሳይደርስባቸው እንዲኖሩ በመፍቀዳቸው ዓለም ከብዙ ዘመን በኋላ ተስማምቶ የደረሰበትን የስደተኞችን የሰበአዊ መብት የማስጠበቅ ተግባር ፈጽመዋል። በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ የዘለቀውንም በሁለቱ ሐይማኖቶች መካከል ያለውን ወንድማማችነት ፈር ቀዳጅ ኾነውም አኩሪ ተግባር ፈጽመዋል። በዚህ ሁሉ ሐይማኖታዊም ሐይማኖታዊ ያልኾነም ተግባር ምክንያት የንጉሱ ታሪክ የበለጠ ገናናነት የሚገባው ኾኖ ሳለ እንደ ብዙዎቹ የአገሪቱ መልካም መለያዎች ሁሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገባውን ያህል የታወቀ አይደለም።
የቱርክ መንግስት ይህን ታሪካዊ ቦታ በማሳደስ ለጎብኚዎች የሚስማማ እንዲኾን ያደረገው ከዚህ ሐይማኖታዊ ተልእኮ በመነሳት ብቻ አለመኾኑንም መገመት ይቻላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቱርክ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ከበፊቱ በተለየ እያጠናከረ የሚገኝበትም ፖለቲካዊ ምክንያት እንዳለውም ግልጽ ነው።
የቱርኩ የሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን መንግስት በቅርቡ ከተሞከረበት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በብርቱ ትግል ከተረፈ በኋላ ተቃዋሚዎቹን እና የነጻውን ፕሬስ በመጨፍለቅ ዳግመኛ ጉዳት እንዳይደርስብስት የሚያደርገው መከላከል በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እያስወቀሰው ይገኛል። የቱርክ መንግስት ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራው በኋላ ከወሰዳቸው ርምጃዎች አንዱ የጉለን እንቅስቃሴ በመባል የሚታወቀውን ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ ከመሰረቱት ከሙሐመድ ፈትሁላህ ጉለን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የሚጠረጥሩ ቱርካውያንን ማሳደድ መጀመራቸው ነው። ኤርዶጋን ጉለንን የስልጣናቸው ተቀናቃኝ አድርገው በማየታቸው ምክንያት በስደት ከሚኖሩበት ከአሜሪካም ተላልፈው እንዲሰጧት እየጠየቀች ነው።
ጉለንን ከማሳደድ በተጨማሪም የኤርዶጋን መንግስት በኚሁ ግለሰብ የተመሰረቱና በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ በቁጥር 1,000 የሚገመቱ የቱርክ የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤቶችንና ልዩ ልዩ የእርዳታ ተቋማትን እንዲዘጉለት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገም ይገኛል። ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራውም በፊት ቢኾን የቱርክ መንግስት በፖለቲካ ተቀናቃኛቸው በጉለን የተያዙ የንግድና የትምህርት ተቋማት እንዲዘጉ ለማድረግ ትልቅ ጥረት ማድረግ ጀምሮ ብዙዎቹን የእንቅስቃሴው ማዕከላት የሚገኙባቸውን የአፍሪካ አገራት ደጅ ሲጠና ቆይቷል። ለብዙዎቹ የአፍሪካ መንግስታት ለረጅም ጊዜ የቱርክን ሕዝብ ወክሎ የበጎ አድራጎትና የኢንቨስትመንት ስራ ሲሰራ የኖረውን የጉለናውያኑን እንቅስቃሴ ማስቀየም ፍላጎት የላቸውም። ሶማልያንና ኢትዮጵያን ከመሰሉ ጥቂት አገራት በቀር የ ኤርዶጋን ጥያቄ ተቀባይነት ያገኘም አይመስልም።
የኢትዮጵያም መንግስት ለዚህ የኤርዶጋን ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት በኢትዮጵያ የሚገኘውን የጉለንን ትምህርት ቤት አሳልፎ ለቱርክ መንግስት ሰጥቷል። በዚህም ምክንያት በሁለቱ መንግስታት መካከል በአዲስ መልክ የተጀመረው ወዳጅነት የሰመረ መስሏል። የኢትዮጵያው ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በቅርቡ በቱርክ የተደረገላቸውም ደማቅ አቀባበል ይህን በሁለቱ መንግስታት መካከል የተጀመረ አዲስ ፍቅር የሚያሳይ ነው። ግንኝነቱንም በንግድና በኢንቨስትመንት ለማጠናከርም መሪዎቹ ቃል ሲገቡም ተስተውሏል።
የነጃሺ መቃብር እና የአልነጃሺ መስጊድ እድሳትም ላይ ድጋፍ ለማድረግ የቱርክ መንግስት ቃል የገባው ኤርዶጋን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ነበር። ኤርዶጋን በፍሪካ ያላቸውን የፖለቲካ ተሰሚነት ከፍ ለማድረግ ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ብዙዎቹን የአፍሪካ አገራት ሲጎበኙ ቆይተዋል። በኢትዮጵያ የነበራቸውም ጉብኝት የዚሁ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አንዱ አካል ነበር።
የጉለን እንቅስቃሴ ሰላማዊነትንና የትምህርትን አስፈላጊነት የሚሰብክ፥ የሐይማኖቶች ወንድማማችነት ለዓለም ሰላም ያለውን አስፈላጊነት ከፍ ባለ ድምጽ የሚያሰማ እስላማዊ እንቅስቃሴ መኾኑ ይነገርለታል። ገዢዎቿ ፍትሕ ያውቃሉ የሚል ምስክርነት በነቢዩ መሐመድ የተሰጣት የነጃሺዋ ኢትዮጵያ ግን ዛሬ የስደተኛውን የጉለንን ድምጽ የሚሰማ ገዢ ያላት አትመስልም። የጉለን አሳዳጅ ኤርዶጋን የስደተኛ ጠበቃ የነበሩትን የነጃሺን መታሰቢያ ለማሰራት ያደረጉትም ጥረት ስላቁ ከፍ ብሎ የሚታየውም ለዚሁ ነው።