በአንዴ መዳከም ? ወይንስ ለገበያ መተው ?

ዋዜማ- የኢትዮጵያ የብር  የውጭ ምንዛሬ ተመን የመዳከሙ(Devaluation) ወይንም ሌላ አማራጭ እርምጃ የመወሰዱ ነገር በእጅጉ መቃረቡን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮቿ መረዳት ችላለች።በተለይ ከሰሞኑ በዶላር የሚከፈላቸው የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ተቋማት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ሰራተኞች በእጃቸው ያለ የውጭ ምንዛሬን ወደ ባንክ ለመመለስ ሩጫ ላይ መሆናቸውን አስተውለናል። ይህም የሆነው መንግስት የብርን የውጭ ምንዛሬ ተመንን የሚያተካክል ከሆነ የተለያዩ ህጋዊ እርምጃዎችን ሊከተሉ ይችላሉ የሚል ስጋት በመፈጠሩ እንደሆነ ግምታቸውን የሰጡን አሉ።

የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ቦርድ የፊታችን ሰኞ ለኢትዮጵያ በሚሰጥ ብድር ላይ ይወያያል መባሉም ግምቶችን አጠናክሯል። ለወትሮ አይኤም ኤፍ ለሀገራት ብድርን በቦርድ ከማጽደቁ በፊት በታችኛው አደረጃጀት(staff level) ጉዳዩን ይፋ አድርጎ ነው ወደ ቦርድ ማጽደቅ የሚሄደው። በኢትዮጵያ ጉዳይ ለሰኞ የተቀጠረው የአይኤምኤፍ የቦርድ ስብሰባ ግን ከቅደም ተከተል አንጻር ያልተለመደ ነው።

ስለ ብር የውጭ ምንዛሬ ተመን መጻኢ እድል ምን ሰምተናል?

የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ መንግስት ገና ከጅምሩ የውጭ ምንዛሬ ተመንን ማዳከም “ለወጪ ንግድ ማበብ ያግዛል” በሚል መርህ ፤ የፋይናንስም ሆነ ሌሎች ዘርፎችን ለውጭ ገበያ በመክፈት የሚያምኑ መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል። ገና አስተዳደራቸው ሁለት አመት ሳይሞላው ነበር ፤ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በፍጥነት እየተዳከመ እሳቸው ሲመጡ 27 ብር የነበረው የአንድ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ 57 ብር የደረሰው። በወቅቱ የአንደኛው “የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” ትግበራ ላይ በነበረበትና ከእነ አይኤምኤፍም እስከ አስር ቢሊየን ዶላር ብድር ይጠበቅ ስለነበር ነገሮች ሁሉ ተፋጥነው ነበር። ሆኖም የህዳሴ ግድብ ፖለቲካ በጣም ተካረረ ፤ የሰሜኑ ጦርነትም ተነሳ ፤ ስለዚህም በአሜሪካ ፊትአውራሪነት ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋማት ልታገኝ የነበረው ብድር ተስተጓጉሎ ቆየ።

ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ እንደገና በተጀመረው የኢትዮጵያ መንግስት እና የእነ አይኤምኤፍ ድርድር በበርካታ ሂደቶች ውስጥ አልፎ ዛሬ ላይ ደርሷል።ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ከቀናት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከእነዚህ ተቋማት ጋር ስምምነቱ ሲያልቅ 10 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ኢትዮጵያ ታገኛለች ማለታቸው ይታወሳል።

ስለ ጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ኢትዮጵያ ድርድሩን በስምምነት ብትቋጭ ራሱ ግፋ ቢል ከስድስት እስከ ሰባት ቢሊየን ዶላር ብታገኝ ነው ይላሉ። የኢትዮጵያ መንግስት የታክስ ፤ የባንክ ስራ አዋጅን ፤ መንግስት ከብሄራዊ ባንክ ገንዘብ የሚያገኝባቸው ሁኔታዎች እንዲገደቡ እንዲሁም ብሄራዊ ባንክን በወለድ ተመን ምጣኔ የሚመራ ባንክ ማድረግን ጨምሮ በአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የሚቀርቡ በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቷል ፤ እያሟላም ነው። አሁን ላይም ቀረ የሚባል ነገር ቢኖር የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ጉዳይ ብቻ ነው።

ዋዜማ እንደሰማችው ከሆነ የአብይ አስተዳደር ብድሩን ለማግኘት  በሚዳከምበት ምጣኔ ላይ እንጂ በብር የውጭ ምንዛሬ ተመን መዳከም ላይ ከስምምነት ከደረሰ ሰንበትበት ብሏል። መጀመርያ ላይ የእነ አይ ኤም ኤፍ ፍላጎት የኢትዮጵያ ብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ነበር። ይህን የኢትዮጵያ መንግስት በፍጥነት የሚተገብረው እንዳልሆነ በግልጽ ማስቀመጡ ይታወሳል። ቀጥሎም የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን እስከ 90 በመቶ እንዲዳከም የአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ፍላጎት ነበር ። አሁን ላይ ግን ከበርካታ ድርድሮች በኋላ  የኢትዮጵያ መንግስት የብር የውጭ ምንዛሬ ተመንን ከ15 እስከ 20 በመቶ ሊያዳክም ፤ በተጨማሪም በየጥቂት ጊዜው ብርን ለማዳከም መስማማቱንም ጉዳዩን እናውቃለን ያሉ ምንጮች ነግረውናል። ይህም እጅግ በጥቂት ጊዜ የሚፈጸም መሆኑን ነው ዋዜማ መረዳት የቻለችው።

ለብር መዳከም ስጋት የነበሩ ነገሮች

የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን መዳከሙ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ዋና ዋና ምርቶችን ከውጭ ገዝቶ ለሚያስገባ ሀገር ከባድ የዋጋ ንረትን ማምጣቱ አይቀሬ ነው። ነገር ግን እነዚህ ሀገራት ለኢኮኖሚ ተሀድሶ እንዲህ አይነት ቅድመ ሁኔታዎች መታለፍ አለባቸው ብሎ በማመን ይተገብሩታል ።

የኢትዮጵያ በድርድሮቹ ወቅት አሳሳቢው ነገር የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ሲዳከም የመንግስት የልማት ድርጅቶች የእዳ መጠን በእጅጉ የሚጨምር መሆኑ እና የእነ ንግድ ባንክ እና መሰል የልማት ድርጅቶች ሀብት በዶላር ሲተመን በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑ ነው ። ለዚህም ይመስላል መንግስት በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካፒታል በ650 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማሳደግ እና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ያለባቸውን 900 ቢሊየን ብር እዳ ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲወርሰው ያደረገው።

የብርን የውጭ ምንዛሬ ማዳከም የወጪ ንግድን ያሳድጋል ወይ ?

ሀገራት የዋጋ ንረታቸው ምርቶቻቸውን ከሚሸጡላቸው ሀገራት የዋጋ ንረት የሚበልጥ ከሆነ ፤ መገበያያ ገንዘባቸው ጠንክሯል ፤ የወጪ ንግዳቸው እንዲያድግም የገንዘባቸውን የምንዛሬ ተመን ማዳከም አለባቸው ሲባል ይሰማል። ኢትዮጵያ ውስጥ በ2003 ዓ/ም ፤ በ2010 ዓ/ም የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ሲዳከም ተመሳሳይ አመክንዮዎች ቀርበዋል ። ሆኖም የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በመዳከሙ ሳቢያ አድጎ እንደማያውቅ በነዛ ጊዜያት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ይሰሩ የነበሩና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሙያተኞች ለዋዜማ ተናግረዋል።

ከሁለት አመት በፊት የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ አራት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላርን ሲሻገር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የብርን ምንዛሬ ካልተገባ ጥንካሬው ስላወረድነው የአንድ ቢሊየን ዶላር ተጨማሪ ገቢን ከወጪ ንግድ አግኝተናል ብለው ነበር ። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ግን ወቅቱ የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያትን ጨምሮ የቡና ዋጋን ጨምሮ የግብርና ምርቶች ዋጋ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዶ ነበር ፤ ኢትዮጵያም የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆና እንጂ ብሯን ማርከሷ አይደለም ገቢዋን ያሳደገላት ይላሉ። ከዚህ በመነሳትም የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን የወጪ ንግድን ከማሳደግ ይልቅ ለኢትዮጵያ ገቢ ምርትን በማስወደድ የዋጋ ንረትን ማምጣቱ ይብሳል ።

እርግጥ የረከሰ ገንዘብ አምራች ለሆኑ ሀገራት ጥሩ የሆነ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን አስገኝቷል።እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ነዳጅን በአራት ቢሊየን ዶላር አስገብተው ቡናን በአንድ ቢሊየን ዶላር ለሚሸጡ ሀገራት ግን የመገበያያቸውን ገንዘብ የምንዛሬ ተመን ማዳከም ውጤቱ ወደ ዋጋ ንረት እንደሚያደላ ያለፉት ጥቂት አመታትም ምስክር ናቸው። [ዋዜማ]