ዋዜማ- ንግድ ባንኮች በየአመቱ የሚሰጡት ብድር እድገት አሁን ካለበት 14 በመቶ ወደ 18 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ዋዜማ ከምንጮቿ መረዳት ችላለች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በ2015 አ.ም ሐምሌ ወር ላይ ወደ 30 በመቶ ተጠግቶ የነበረውን የሀገሪቱን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የብድር ስርጭት ላይ ገደብ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱም ንግድ ባንኮች በየአመቱ የሚሰጡት ብድር ቀደም ብሎ ካለው አመት ከ14 በመቶ ብልጫ እንዳይኖረው ገደብን አስቀምጧል።
የፌዴራል መንግስትም በ2016 አ.ም ከብሄራዊ ባንክ በቀጥታ የሚወስደው ብድር 2015 አ.ም ከወሰደው አንድ ሶስተኛውን ብቻ እንዲሆንም ደንግጓል።
ሆኖም አዲስ በጸደቀው የብሄራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ የፌዴራል መንግስት ከማእከላዊ ባንኩ ምንም አይነት ብድር መውሰድ እንደማይችል እና መንግስት የበጀት እጥረት ካጋጠመው ኦቨር ድራፍት የተሰኘውን በአንድ አመት የሚመለስ የአጭር ጊዜ ብድር ብቻ መውሰድ እንዲችል በማድረግ የ2015 መመሪያን በአዋጅ ሽሮታል። ይህም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ሁነኛ መፍትሄ ነው ተብሎ ነበር።
የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በንግድ ባንኮች በኩል የሚረጨውን ብድር እድገት በ14 በመቶ መገደቡ ለኢንቨስትመንት እና ስራ ፈጠራ የሚሰጥ ብድርን በማቀጨጭ ኢኮኖሚውን ጎድቶታል በሚል ተደጋጋሚ አቤቱታ ሲሰማ ቆይቷል።
ዋዜማ ከምንጮቿ እንደሰማችው ለዚሁ መፍትሄ ይሆናል በሚል የ14 በመቶ የብድር እድገት ገደቡን በ4 በመቶ ነጥብ(pecentage point) በማሳደግ 18 በመቶ ለማድረግ ታስቧል።
“የዋጋ ንረትን በማያመጣ ደረጃ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ፋይናንስ ከፍ በማድረግ የ8.4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገትን በበጀት ዓመቱ ለማስመዝገብ እንዲያግዝ ተብሎ ነው የብድር እድገት ምጣኔው እንዲጨመር የታሰበው” ብለውናል የዋዜማ ምንጫችን።
መመሪያው ግን ገና ተግባራዊ እንዳልሆነና በውይይት ዳብሮ ሊተገበር እንደታቀደ ምንጫችን ነግረውናል።አንዳንድ ባንኮች የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ለውጥ ከተደረገ በኋላ የውጭ ምንዛሬ ክምችታቸው ያደገውም ለባለሀብቶች የሚሰጥ ብድር አነስተኛ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬውን የመግዛት አቅምም በዛው ልክ በመውረዱ ነው ።
ሆኖም ዋዜማ ራዲዮ ያነጋገረቻቸው የሁለት ባንክ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች የባንኮች አመታዊ የብድር እድገት ምጣኔ ይጨምር መባሉ በራሱ ችግር ባይኖርበትም አሁን ያለው የባንኩ ዘርፍ ትልቁና ዋነኛው ችግር የብድር እድገት ምጣኔ “ይጨመር” ” አይጨመር” የሚል ሳይሆን ለብድር የሚውለው ገንዘብ ላይ ያለውን ከፍተኛ እጥረት መፍታቱ ላይ ነው ብለውናል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአንድ ባንክ ፕሬዝዳንት እንዳሉን “አሳሳቢው ጉዳይ አሁን ላይ ባንኮች የገቡበትን ከፍተኛ የገንዘብ እጥረትን መፍታት ነው”። የሌላ ባንክ ከፍተኛ የስራ ሀላፊም እንዲሁ “ንግድ ባንኮች በተለይም የግሎቹ የብድር ምጣኔ ቢያድግላቸውም የሚሰጡት ብድር የላቸውም ፣ ያለብን የገንዘብ እጥረት ለጊዜ ተቀማጭ ቁጠባ አስቀማጮች እስከ 25 በመቶ ወለድ ለመክፈል እያስገደደን ነው” ሲሉ የባንካቸውን ወቅታዊ ሁኔታ በማጣቀስ አስረድተውናል።
እርግጥ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሁለተኛው የፋይናንስ ዘርፉን ወቅታዊ ሁኔታ በተነተነው ሪፖርት ላይ በርካታ ንግድ ባንኮች በአሁኑ ወቅት የጥሬ ገንዘብ እጥረት ውስጥ መግባታቸውን አትቷል። በርካታ ባንኮች በአመታዊ ሪፖርታቸው ላይ ቁጠባቸው እንዳደገ በሚገልጹበት በዚህ ወቅት፣ በሌላ በኩል እነዚሁ ባንኮች ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ውስጥ ናቸው መባሉ ምናልባትም ባንኮች የሰጡትን ብድር መሰብሰብ ላይ ካጋጠማቸው ችግር ጋር የሚያያይዙት አሉ።ሆኖም ብሄራዊ ባንክ ከነዚህ ሁሉ ወቅታዊ የፋይናንስ ዘርፉ ቁመና ጎን ለጎን የባንኮች ብድር እድገት ምጣኔን ለማሳደግ እየሰራ ነው ተብሏል። [ዋዜማ]