ዋዜማ- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የሀገሪቱን የባንኮች ከቀውስ ይታደጋል፣ መረጋጋትም ያሰፍናል ያላቸውን አምስት አዳዲስ መመሪያዎች ይፋ አድርጓል። መመሪያዎቹ ከዚህ ቀደም የተወሰዱ ብድሮችንም ሆነ አዲስ የሚሰጡ ብድሮች ላይ ገደብ እና ተጨማሪ ተጠያቂነትን ይዟል። መመሪያው በሀገሪቱ ባሉ ባንኮች ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖና በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የሚከሰቱ አዳዲስ ለውጦችን ለመገንዘብ የመመሪያዎቹን አንኳር ይዘት እንደሚከተለው አሰናድተነዋል። አንብቡት
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የሀገሪቱን የባንክ ዘርፍ ጤንነት ያስጠብቃል ያላቸውን አምስት መመሪያዎችን አሻሽዬ አውጥቻለሁ ባለው መግለጫ ላይ የንግድ ባንኮች ለደንበኞቻቸው ብድርን የሚያራዝሙበትን መንገድ የሚገድብ መመሪያን አሻሽሎ ማውጣቱን ገልጿል።
ማዕከላዊ ባንኩ የብድር ጊዜ ማራዘምን የሚገድበው የተሻሻለው “የንብረት ምደባ እና ለተዛማጅ ስጋቶች ስለሚያዝ የመጠባበቂያ ፕሮቪዥን” ፣ የሚለው መመሪያ ነው። በተሻሻለው መመሪያ መሰረትም ንግድ ባንኮች የአጭር እና የመካከለኛ ጊዜ ብድሮችን የመክፈያ ጊዜ ማሻሻል የሚፈቀድላቸው ሶስት ጊዜ ብቻ እንዲሆን ገድቧል።
ከዚህ ቀደም ንግድ ባንኮች የአጭር እና መካከለኛ ጊዜ ብድሮችን አምስት ጊዜ ማራዘም ወይንም የብድር ውልን ማሻሻል ይፈቀድላቸው ነበር። ንግድ ባንኮች የረጅም ጊዜ ብድርን የመክፈያ የውል ጊዜን ማሻሻል የሚፈቀድላቸው ለአራት ጊዜ ብቻ እንዲሆን በብሄራዊ ባንኩ በተሻሻለው መመሪያ ደንግጓል። ከዚህ ቀደም የረጅም ጊዜ ብድር መክፈያ ጊዜን ለስድስት ጊዜ ማራዘም ይፈቀድ ነበር።
ማዕከላዊ ባንኩ የብድር መክፈያ ጊዜ የማራዘምያ ድግግሞሽን መገደብ ያስፈለገው በንግድ ባንኮች ዘንድ ብድሮችን ሁል ጊዜ ጤናማ አድርጎ የማቅረብ ልማድን ለማስቀረት መሆኑን ገልጿል። በተለይ የብድር መክፈያ ጊዜን በተደጋጋሚ ማራዘምን በርካታ ባንኮች በየአመቱ ያልተገባ ትርፍን ለማግኘት እንደሚጠቀሙበት ብዙ ጊዜ ይነሳል።
አንድ ተበዳሪ ብድሩን በወቅቱ መክፈል ካልቻለ አበዳሪው ባንክ መመለስ ያልቻለውን ያክል ገንዘብ በመጠባበቂያነት መያዝ ይጠበቅበታል።ሆኖም የብድር መክፈያ ጊዜው የሚራዘም ከሆነ ግን ለመጠባበቂያነት የሚያዘው ገንዘብ ወደ ትርፍነት የመሄድ ዕድሉ ከፍ ያለ ነው።
በተሳሳተ ሁኔታ ሁል ጊዜ ብድርን ጤናማ አስመስሎ ማቅረብ ለባንኮች ለጊዜው ትርፍ ማግኛ ይሁን እንጂ በጊዜ ሂደት ለፋይናንስ ዘርፉ አደጋን ማምጣቱ አይቀርም። ለዚህም ብሄራዊ ባንኩ የብድር ማራዘሚያ ድግግሞሽን እንዲገደብ አድርጓል። ማዕከላዊ ባንኩ አንድ ብድር የመክፈያ ጊዜው ሳይደርስ በተለያየ ሁኔታ ሳቢያ የመከፈል እድሉ የጠበበ መሆኑን አመላካች ነገር ካለ እንደ ተበላሸ ብድር ተቆጥሮ ቢያንስ አጠራጣሪ ብድሮች ውስጥ እንዲገባ ባሻሻለው መመሪያ ደንግጓል።
በሌላ በኩልም አንድ ተበዳሪ ከአንድ ባንክ የተለያዩ ብድሮች ወስዶ ከብድሮቹ አንዱ የተበላሸ ሆኖ፣ ይህ የተበላሸው ብድር ለደንበኛው ከተሰጠው ብድር ውስጥ ከ20 በመቶ እና ከዛ በላይ ከሆነ ሁሉም ብድሮች ወዲያው በተበላሸ ብድር መደብ ውስጥ እንዲካተቱ ታዟል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በሌላ በኩል የባንኮች ብድር ውስን ቦታ ውሎ ፣እነዚያ ውስን ተበዳሪዎች የብድር መክፈል ውላቸውን በጊዜው መወጣት ባለመቻላቸው ባንኮች ላይ ሊመጣ የሚችል አደጋን ለመቀነስ ለአንድ ተበዳሪ ሊሰጥ የሚችል ብድር ላይ ጣርያ አበጅቷል። በተሻሻለው “የከፍተኛ ብድር ተጋላጭነት ገደብ መመሪያ” በሚለው ውስጥ ተካቷል። በዚህም መሰረት አንድ ባንክ ለአንድ ተበዳሪ የሚሰጠው ብድር ከባንኩ ጠቅላላ ካፒታል ከ25 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት መመሪያው ያዛል።
መመሪያው ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር አንድ ተበዳሪ ቢወስድ እና ተበዳሪው መክፈል ባይችል ባንኩ ላይ ሊከሰት የሚችል ውድቀትን እና ባለ አክስዮኖችን እና ተያያዥ አካላት ላይ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት ለመቀነስ ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል።
ብሄራዊ ባንክ በቅርቡ ያወጣው የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት (stablity) ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ ባንኮች እስከ ዛሬ ከሰጡት ከሁለት ትሪሊየን ብር በላይ ብድር ከ20 በመቶ በላይ ማለትም ከ400 ቢሊየን ብር በላይ የሆነውን የወሰዱት ከ10 ተበዳሪዎች አይበልጡም ማለቱ፣ ብዙ ብድር ለጥቂት ተበዳሪዎች በመሰጠቱ ለፋይናንስ ዘርፉ ስጋት ፈጣሪ ነው አስብሏል። ስለዚህ ለአንድ ተበዳሪ ከአንድ ባንክ የሚሰጥ ብድር ገደብ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው ተብሏል።
ብሄራዊ ባንክ ካሻሻላቸው መመሪያዎች ውስጥ ከባንኮች ጋር ተዛማጅነት ላላቸው አካላት የሚሰጥ ብድር ላይም ገደብ ያስቀመጠ መመሪያም ይገኛል። ይህም የአንድ ባንክ ባለ አክስዮን ሆነው ከባንኩ የሚበደሩ ግለሰቦችንም ሆነ ኩባንያዎችን ሊያካትት ይችላል። በዚህ መልኩ የሚሰጥ ብድር ላይ ገደብ ማስቀመጥ ያስፈለገውም ብድር በአግባቡ እንዳይሰጥ እና የጥቅም ግጭትን ለማስቀረት ነው ተብሏል። በዚህም ከባንክ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተዛማጅነት ላላቸው አካላት በማንኛውም ጊዜ የሚሰጠው ብድር ከባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ከ15 በመቶ እንዳይበልጥም በተሻሻለው መመሪያ ገደብ ተቀምጧል።
ባንኮች ብድር ሲሰጡ ከነሱ ጋር ተዛማጅነት ላላቸው አካላት(ለባለ አክስዮኖችም ሆነ ሌላ) ሆነ ከባንኮቹ ጋር ተዛማጅ ላልሆኑ ግለሰቦችም ሆኑ ኩባንያዎች ተመሳሳይ መስፈርትን ይጠቀሙ ተብሏል። ይህም አንዳንድ ባንኮች ተዛማጅ ላልሆኑ ግለሰቦችም ሆነ ኩባንያዎች ብድር ለመስጠት የብድር መያዣንም ሆነ ሌሎች መስፈርቶችን ጠበቅ እያረጉ ለባለ አክስዮኖች እና ተዛማጅ አካላት ብድር የመስጫ መስፈርትን በማላላት የሚፈጽሙትን ኢ-ፍትሀዊነት ለማስቀረት በማሰብ ነው ። [ዋዜማ]