ዋዜማ- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት፣ ለብዙ ጊዜያት ሲጠበቅ የነበረውን የፍትሕ ፖሊሲ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ማፅደቁ ተሰምቷል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀውን ይህን ከፍተኛ አገራዊ ትርጉም ያለው ፖሊሲ የተመለከተችው ዋዜማ፣ ለአንባብያኖቿ ይሆን ዘንድ የፖሊሲውን አንኳር ነጥቦች እንደሚከተለው አሳጥራ አዘጋጅታለችና እንዲያነቡት እንጋብዛለን።
ብዙዎች በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው ይኽ ፖሊሲ፣ ከዐቢይ መምጣት ጀምሮ
የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ለማፋጠን፣ ፍትሐዊ የሆነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ልማትን እና አሳታፊና አካታች ፖለቲካዊ ሥርዓትን ለመገንባት ያስችላሉ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ የህግ እና ተቋማዊ ማሻሻያ ስራዎችን ተግባራዊ መደረጉን ያነሳል። ያም ሆኖ ግና፣ ባለፉት አመታት እና ከዚያም ቀደም ብሉ ባለፉት ዘመናት በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠሩ አለመግባባቶች፣ ቅራኔዎች፣ ከባድ ግጭቶች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ለንብረት ውድመት፣ ለአካል ጉዳት እና ለሞት ተዳርገዋል፤ የሚለው ፖሊሲው፣ በጥቅሉ በየጊዜው የሚነሱ አለመግባባቶች፣ ጦርነቶች፣ ግጭቶች እና ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አገሪቱን ለከፋ አደጋ የዳረጉበት ሁኔታ ተፈጥሯል ሲል በመጀመሪያዎቹ ምዕራፎቹ ይደመድማል።
በሰነዱ ዙሪያ የቀረቡትን ትችቶች በዚህ ማስፈንጠሪያ ማንበብ ይችላሉ
በአገሪቱ በተለያዩ ዘመናት የተከሰቱ እና የቀጠሉ ተደራራቢ እና ሰፊ የተጎጂና የአጥፊ ወሰን ያላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ያልጠሩ ትርክቶች እና በደሎችን ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች መደረጋቸውን ተቀብሎ የሚነሳው ይኸው ፖሊሲ፤ ሆኖም እነዚህ አሰራሮች በእውነት፣ በዕርቅ፣ በምህረት እና በፍትሕ ላይ የተዋቀረ እና በግልፅ ፖሊሲ የሚመራ ሁለተናዊ የሽግግር ፍትሕ ስልትን አካታች፣ ሰብአዊ መብት−ተኮር በሆነ እና በተሰናሰለ መንገድ ባለመተግበራቸው የሚፈለገውን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት አልቻሉም ሲልም ሌላኛውን ድምዳሜውን ያስነብባል።
ከዚህ አኳያም፣ ለችግሮች እና አገራዊ ፈተናዎች ስር-ነቀል እልባት ከመስጠት አንፃር በሚል የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መውጣትን አስፈላጊነት ሲያነሳም፣ አግባብነት ያላቸው የዓለም-አቀፍ ሰነዶች ስለሽግግር ፍትሕ አካሄድ ያስቀመጧቸውን ደረጃዎች ግምት ውስጥ በማስገባት የተሟላ የሽግግር ፍትሕ ሂደትን በአገሪቱ በመተግበር በየጊዜው ከሚከሰቱ ችግሮች መውጣት እና ዘላቂ ሰላም እና ፍትሕን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ይገልጣል።
የሽግግር ፍትሕን ዋጋም ሲጠቅስ፣ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ከእርስ በእርስ ጦርነት፣ ግጭት እና ጭቆና በመውጣት በፖለቲካ እና ዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትርጉም ያለው ሽግግር ለማድረግ በሞከሩ በርካታ ሀገራት ተተግብሯል፤ ከፍተኛ አስተዋፅኦም አበርክቷል ይለናል። ከዚህ ባለፈም፣ አገሪቱ በተሟላ የሽግግር ፍትሕ ሂደት እንድታልፍ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ስለመሆኑ በገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን የተደረገ ጥናት ማረጋገጡንም ያነሳል።
ከእነዚህ ባለሙያዎች ጥናት በተጨማሪም፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ባወጡት ጣምራ የምርመራ ውጤት ላይ በግጭቱ ማእቀፍ የተፈጸሙ ወንጀሎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትሕ ማእቀፍ ሊታዩ እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ ማቅረቡን በማንሳት፣ የፖሊሲውን እጅጉን አስፈላጊ መሆን አበክሮ ያስታውሳል። በፕሪቶሪያው ፊርማ ላይም፣ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የተፈፀሙ ወንጀሎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትሕ ሂደት ሊፈቱ እንደሚገባ መመላከቱን ያክላል።
ይህ ተጠባቂ ፖሊሲ፣ በፍትሕ ሂደቱ እመለከታቸዋለሁ ያላቸውን የወንጀል ዓይነቶች ሲዘረዝር፣ በዋናነት ያነሳው ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያለውን ሲሆን፣ ለሱም ፍቺውን አስቀምጧል። ስልታዊ፣ መጠነ-ሰፊ ወይም ተከታታይነት ባለው ሁኔታ የተፈጸመ ወንጀል ነው ሲል ይህንኑ ፍቺውን ያስቀምጥና፤ በዚህ ስር የሚጠቃለሉ ወንጀሎችን ሰፋ አድርጎ ይዘረዝራል።
በዋናነትም የሰው ዘር የማጥፋት ወንጀል፣ የጦር ወንጀል፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ ወንጀል፣ አስገድዶ ሰውን የመሰወር ወንጀል፣ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እና ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ ሰውን ከመደበኛ የመኖሪያ ቦታ ከሕግ አግባብ ውጭ የማፈናቀል ድርጊት፣ በሕፃናት ላይ የሚፈፀም ወንጀል፣ በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚፈፀም ወንጀል፣ ብሔርን፣ የፖለቲካ አመለካከትን ወይም ኃይማኖትን መሰረት በማድረግ የሚፈፀም ወንጀል፣ ወይም ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ዓለም-አቀፍ ስምምነቶች መሰረት ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ዓለም አቀፍ ወንጀል ህግ ጥሰት ወይም ከባድ የሰብዓዊነት ህግ ጥሰት ተብሎ የተለየ ማንኛውም ሌላ ወንጀልን እንደሚያካትት ያስቀምጣል።
በብዙ ፖለቲከኞች እና ልሂቃን ሲነሳ የሰነበተውን የዕርቅን ጉዳይም ዋና ማዕከሉ ያደርጋል። ዕርቅን ሲበይንም፣ ጥላቻ፣ አለመተማመን እና መከፋፈል የሚወገድበት አሰራርን የሚመለከት አንድ የሽግግር ፍትሕ ሂደት እና ግብን የሚያመለክት ፅንሰ-ሀሳብ መሆኑን ያነሳል። ከዚህ የዕርቅ ጉዳይ ጋር ስለሚተሳሰረው እና ፖሊስው ፈውስ ብሎ የሚጠራውን ሂደት አስመልክቶም፤ ተጎጂዎች ለደረሰባቸው ጉዳት በተገቢ መልኩ ይፋ የማውጣት፣ ለደረሱ ጥሰቶት እውቅና የመስጠት እና በይፋ ይቅርታ የመጠየቅ፣ ተገቢ የመታሰቢያ እና ማስታወሻ ክንዋኔዎችን የማድረግ እና የቀጠሉ ተመሣሣይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የማስቆም እርምጃዎችን የሚያካትት ተግባር መሆኑን ጠንከር አድርጎ ያነሳል።
አዲስ ዐቃቤ ሕግ እና ልዩ ችሎት. . . .
በመላ አገሪቱ ተፈጻሚ እንደሚሆን ፖሊሲው ራሱም የሚያነሳው ይኽ ሰነድ፣ በአገሪቱ የወንጀል ሕግ ውስጥ ያልተካተቱ ዓለም-አቀፍ ወንጀሎችን በተመለከት ሀገሪቱ ከተቀበለቻቸው ዓለም-አቀፍ ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ አዲስ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚዘጋጅም ጠቀስ አድርጎ ያልፋል።
ከአጥፊዎቹ ብዛት፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ከሚተገበርበት የጊዜ ወሰን ስፋት፣ እንዲሁም በአጥፊዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እና ክስ ስራዎችን ለማካሄድ ከሚያስፈልገው ረጅም ጊዜ እና ከሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ አንፃር የምርመራ እና ክስ የመመስረት ስራው ትኩረት ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ባላቸው አጥፊዎች ላይ ብቻ እንደሚሆንም ፖሊሲው ጠበቅ አድርጎ አስቀምጧል።
ከዚህ አኳያም፣ በፖሊሲው የተካተቱ ወንጀሎችን በተመለከተ በአጥፊዎች ላይ የወንጀል ሙሉ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ያለመከሰስ መብት ተፈፃሚነት እንዳይኖረው ከመደረጉ ባለፈ፣ በአገር ውስጥ የማይገኙ ከፍተኛ ደረጃ የወንጀል ተሳትፎ ያላቸው አጥፊዎች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ከሚገኙበት አገር ተላልፈው እንዲሰጡ ለማድረግ ተገቢ ስራ ይሰራል ሲልም ከበድ ያለውን ቀጣይ የመንግሥትን ስራ ይጠቅሳል።
ከላይ በጠቀስነው ከባድ ወንጀል ብሎ ፖሊሲው ባነሳው ውስጥ፣ በምርመራ ሂደት ሊደረስበት የማይችል ከፍተኛ ደረጃ የወንጀል ተሳትፎ ያለው አጥፊ የሚገኝበትን ቦታ ለጠቆመ ወይም አጥፊው በጉልሕ የሰብአዊ መብት ጥሰት መሳተፉን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ላቀረበ ሰው የማበረታቻ ድጋፍ ወይም ሽልማት የሚሰጥበት ሥርዓት እንደሚመቻችም ያብራራል።
ይህ የወንጀል ምርመራ እና ክስ የመመስረት ተግባር፣ አሁን ካለው የወንጀል ምርመራ እና ዐቃቤ ሕግ ተቋም ውጪ በሆነ ሌላ አዲስ የልዩ ዐቃቤ ሕግ ተቋም አማካኝነት እንደሚመራ ፖሊሲው ውሳኔውን አስቀምጧል። ከዚህ ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ይቋቋማል ከተባለው የዐቃቤ ሕግ ተቋም በተጨማሪ የፍርድ ሂደቱን የሚመለከት ልዩ ችሎት እንደሚቋቋምም የውሳኔ ሃሳቡን አስቀምጧል።
የዚህን፣ ፖሊስው ልዩ ችሎት ብሎ የጠራውን ተቋም አስመልክቶም መልኩን ሲያብራራ፤ አቅም እና ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ያካተተ፣ የተጎጂዎችን ተሳትፎ የሚያረጋግጥ፣ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ስር የተለየ የራሱ አደረጃጀት የሚኖረው ልዩ ችሎት የሚደራጅ እንደሚሆን ገልጧል። ይኽው ልዩ ችሎት፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስር እንደሚቋቋም ሲወሰን፣ የይግባኝና የሰበር የዳኝነት ስልጣንን በተመለከተ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር ተመሳሳይ ልዩ የይግባኝና የሰበር ሰሚ ችሎት ይደራጃል ብሏል።
የምህረት እና የጊዜ ገደብ ጉዳይ
ይህ የሽግግር ፖሊሲ፣ ወንጀሎችን ብቻም ሳይሆን ሌሎች ጉዳዮችንም እንደሚመለከት ሰነዱ ያብራራል። ለግጭቶች መንስኤ የሆኑ የታሪክ አረዳዶች እና ትርክቶች የተከሰቱበት የጊዜ ማእቀፍ ወሰን ሳይደረግበት ሁሉንም በመመርመር፣ ትርክቱን በማጥራት እና በመለየት እውነትን ይፋ የማውጣት እና እውቅና የመስጠት ተግባር ይከናወናል ሲልም፣ ወንጀሎችን ከማየት ሻገር የሚል ስራ እንደሚኖር አስቀምጧል።
በእነዚህ ግጭቶችን ቀስቅሰዋል አልያም አበረታተዋል የሚባሉትን ትርክቶች ከማጥራት ባሻገርም፣ በተያያዥ ይከናወናሉ ስለተባሉት የዕርቅ እና መሰል ጉዳዮች ሌላ አዲስ ተቋም እንደሚቋቋምም ይገልጻል። የእውነት ማፈላለግ፣ ይፋ ማውጣት እና የዕርቅ ተግባራት ለጾታዊ ጥሰቶች፣ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ልዩ በደሎች እና ለሌሎች ልዩ ትኩረት የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች ጉዳቶች ተገቢ ትኩረት በሚሰጥ አግባብ ይከናወናሉ የሚለው ፖሊሲው፤ እኒህን ተግባራት የሚከውን፣ ከተጽዕኖ እና ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ የሚቋቋም አዲስ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን እንደሚኖር ያውጃል። በአዲስነት የሚቋቋመው ኮሚሽኑ፣ ከእነዚህ ተግባራት ባለፈም፣ ምህረት የመስጠት ሥራን የሚመለከት ተደራቢ ኃላፊነት ሲኖረው፤ የጾታ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት እና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ውክልና እንደሚኖረው ተነግሯል።
ይህ ሰነድ፣ ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል ከበድ ያለው የምህረት ጉዳይም አንዱ ነው። የተጎጂዎች ይሁን የአጥፊዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል ብሎ የሚንደረደረው ፖሊሲው፣ ሁሉም ጥፋቶች በወንጀል ተጠያቂነት ማዕቀፍ እንዲወድቁ ይደረግ ቢባል የእውነት ማፈላለግ፣ ይፋ ማውጣት እና የዕርቅ ተግባራትን ተፈፃሚ ማድረግ የሚቻልበትን እድል ያስቀራል ሲል የምህረትን አስፈላጊነት መነሾም ያስቀምጣል፤ ከዚህ ባለፈም፣ ሁሉንም ወንጀሎች/ጥሰቶች በክስ ሂደት እንዲያልፉ ማድረግ አይቻልም ሲልም የምህረት አስፈላጊነቱ ላይ ምክንያት ያለውን ያክላል። ስለሆነም ይላል ፖሊሲው፣ ስለሆነም በቅድመ−ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምህረትን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
ያም ሆኖ ግና፣ ምህረትን ሙሉ ለሙሉ መተግበር እንደማይቻል ሲያነሳም፣ በሌላ በኩል ለተፈጸሙ ጥሰቶች ሁሉ ምህረት የሚሰጥበትን ሁኔታ መደንገግ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስቀር እና ዓለም አቀፍ ግዴታን የሚቃረን ከመሆኑም በላይ የተሟላ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ ለማድረግ ተግዳሮት እንደሚፈጥርም ይጠቅሳል። ከዚህ አኳያም፣ በኢትዮጵያ ተግባራዊ በሚደረገው የሽግግር ፍትሕ ሂደት በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምህረት ተግባራዊ እንደሚደረግ ያውጃል። በዚህ በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምህረት እንደማያገኙ የተጠቀሱት፣ ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ያላቸው አጥፊዎች የሚባሉት ናቸው።
እንደአግባብነቱ በህግ የሚወሰኑ ሌሎች ቅድመ−ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆኖ ማመልከቻ በማቅረብ የምህረት ተጠቃሚ ለመሆን ቅድመ-ሁኔታዎች እንደሚኖሩም ሰነዱ ያብራራል።
እነርሱም፦ በጉልህ ወንጀሎች/ጥሰቶች ላይ ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ያለው አለመሆን፣ እውነት በማውጣት እና በምርመራ ሂደት መተባበር፣ ጥፋትን ማመን እና መጸጸት፣ በይፋ ህዝብን እና ተጎጂዎችን ይቅርታ መጠየቅ፣ እንዳስፈላጊነቱ እና እንደ ሁኔታው ለተፈጸመው በደል በማካካሻ ሂደት ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆን፣ በበጎ ፈቃድ ሰራ ላይ በመሳተፍ ህዝባዊ አገልግሎት ለመስጠት መስማማት፣ ወንጀሉ የተፈፀመበትን ምክንያት (motive) በማየት እንዳስፈላጊነቱ ከህዝባዊ ሀላፊነት ለመልቀቅ ፈቃደኛ መሆን፣ ተመሳሳይ የወንጀል ሪከርድ አለመኖር፣ እና ተመሳሳይ ጥሰቶች እንደማይፈጽም ቃል መግባት የሚባሉት እንደሆኑም ዘርዝሮ ያስቀምጣል።
ይህን መሰል ምህረት ያገኙም፣ የተሰጣቸው ምህረት ሊነሳ የሚችልበት ዕድል እንዳለም ሲጠቀስ፤ ምህረት ከተሰጠ በኋላ የሚነሳበት አግባብ በህግ እንዲወሰን ይደረጋል ሲል አስቀምጧል። ስለዚሁ የምህረት ርዕሰ-ጉዳይ ባተተባቸው ገጾች፣ ለተፈጸሙት በደሎች በመንግስት ደረጃ ይፋዊ ይቅርታ መጠየቅ እንደሚኖርም ያነሳል። ከዚህ የመንግስት ይቅርታ ባለፈም፣ በሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ተቋማት እና ባለሙያዎችም ውሳኔ ሊሰጥባቸው እንደሚችል ይጠቅሳል።
እንደ ፖሊሲው ከሆነ፣ የተቋማት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመሳተፍ ወይም ኃላፊነትን ባለመወጣት በተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች/ወንጀሎች ላይ እንደነበራቸው የተሳትፎ መጠን ወይም የሥነ-ምግባር/ሙያዊ ብቃት ማነስ ሁኔታ እየታየ ከስራ እንዲነሱ፣ በአስተዳደራዊ እርምጃ ወይም በወንጀል ተጠያቂ እንዲሆኑ ወይም ሌሎች አስፈላጊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ይደረጋል ይላል።
ይህን ሊፈጽም የሚችለውም፤ በሕግ የሚቋቋም ነጻ፣ ገለልተኛ እና የህዝብ አመኔታ ያለው ኮሚሽን እንደሆነ ሰነዱ ያዛል። ኮሚሽኑ ተግባሩን ለማሳለጥም፣ ተቋማትን የመለየት እና የማጥራት ስራ በማከናወን እና የማሻሻያ እርምጃዎችን በመለየት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ለማስወሰን የሚያስችል ስልጣንና ተግባር እንዲኖረው ይደረጋል ሲል የኀላፊነቱን ልክ ይጠቅሳል።
ሌላይኛው እና ምናልባትም ብዙ ሙግቶችን ይቀስቅሳል ተብሎ ከሚጠበቀው ጉዳይ አንዱ፣ የሽግግር ፍትሑ የሚሸፍነው የጊዜ ገደብ ነው። በዚህ ጉዳይ ፖሊሲው ግልጥ ያለ አቋሙን አስቀምጧል። እንደ ሰነዱ ከሆነም፣ የሽግግር ፍትሕ የጊዜ ወሰን ለወንጀል ተጠያቂነት ዓላማ ‘የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ−መንግስት ከፀደቀበት ከ1987 ጀምሮ’ ያለው የጊዜ ወሰን ተፈፃሚ እንደሚሆን በግልጽ ተቀምጧል። ፖሊሲው ይህን ብሎ ሳለም፣ “በሌላ በኩል” ሲል ተጨማሪ ነጥብ ያክላል። እንደ ሰነዱ ገለጻ፣ ‘ለእውነት ማፈላለግ፣ ዕርቅ ማስፈን እና ማካካሻ ስራዎች ዓላማ’ ጥሰቶች እና ቅራኔዎችን ከመሰረታቸው በማጥራት ለመመርመር፣ ስብራቶች እንዲሽሩ እና እንዲጠገኑ ለማድረግ እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እንዲቻል የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ የተፈፃሚነት ወሰን ‘መረጃ እና ማስረጃ እስከተገኘበት ጊዜ ድረስ’ ይሆናል።
በሰነዱ ዙሪያ የቀረቡትን ትችቶች በዚህ ማስፈንጠሪያ ማንበብ ይችላሉ
[ዋዜማ]