ዋዜማ- ሼኽ መሐመድ ሁሴን አል-አሙዲ፣ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በፍርድ ቤት የተወሰነባቸውን ከስምንት መቶ ሃምሳ ሁለት ሚሊየን ብር በላይ መክፈል ካልቻሉ፣ በናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኅ/የተ/የግ/ማኅ/ ውስጥ ያላቸው የ15 በመቶ የአክሲዮን  ድርሻቸው ተሽጦ እንዲከፈላቸው ለፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ባስገቡት የአፈፃጸም ማመልከቻ መጠየቃቸውን ዋዜማ ከማመልከቻው ተረድታለች። 

 የፍርድ ባለመብት ናቸው የተባሉት ሼኽ አል-አሙዲ፣ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ኅዳር 11 2017 ዓ.ም. በፃፉት ማመልከቻ፣ ፍርድ ያረፈበት የተባለውን 852,462,650 ሚሊዮን ብር ጨምሮ፤ ከኅዳር 27 2014 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 12 2017 ዓ.ም. የተሰላ የሁለት ዓመት ከ11 ወራት ከ15 ቀናት 9 በመቶ ሕጋዊ ወለድ ብር 226,968,180፣ የፍርድ ባለ እዳ የተባሉት አብነት ገ/መስቀል እንዲከፍሏቸው መጠየቃቸውን ማመልከቻው ይጠቅሳል።  

ዋዜማ የተመለከተችው እና ሳውዲ አረቢያ ጅዳ ይገኛሉ የተባሉት ሼኽ አልአሙዲ የላኩት ይኸው የውሳኔ አፈፃፀም ማመልከቻ እንደሚለው ከሆነ፣ በተሰጠው ፍርድ ላይ ይግባኝ ስለመባሉ ሼኽ አል-አሙዲ እንደማያውቁ፣ ፍርዱ ከተሰጠ በኋላ በፍርዱ መሠረት የተፈፀመ ክፍያም ሆነ መቻቻል አለመኖሩን ያነሳል። ከዚህ ባለፈም፣ ፍርድ ለማስፈፀም ከዚህ ቀደም የተከፈተ የአፈፃፀም መዝገብ አለመኖሩንም ጨምሮ ይገልጻል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሓ ብሔር ምድብ ችሎት ኅዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም ለአቶ አብነት በጻፈው ደብዳቤ፣ አቶ አብነት ፍርድ ቤቱ ጥቅምት 5 2017 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ የማይፈጽሙበት ምክንያት ካለ፣ ታኅሳስ 18 ቀን 2017 ዓ.ም በችሎቱ ቀርበው እንዲያስረዱ ማዘዙንም ዋዜማ ተረድታለች። 

የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት አቶ አብነት ለብልጽግና ፓርቲ 75 ሚሊዮን ብር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሶሻል ትረስት ፈንድ 120 ሚሊዮን ብር፣ ለፌደራል ፖሊስ 5 ሚሊዮን ብር፣ ለኢንፎርሜሽን ደኅንነት መረብ ኤጀንሲ 7 ሚሊዮን ብር፣ ለሙጋድ ትራቭል ኃ.የተ.የግል.ማ ከ241 ሚሊየን ብር በላይ፤ በአጠቃላይ በስጦታ መልክ የሰጡትን ከ852 ሚሊየን ብር በላይ ለአል-አሙዲ እንዲከፍሉ ውሳኔ መስጠቱን እና አቶ አብነት የይግባኝ መብት እንዳላቸውም ዋዜማ መዘገቧ ይታወሳል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ክፍያዎችን አስመልክቶም፣ ስማቸው የተጠቀሰው እነዚሁ ተቋማት ከአቶ አብነት እና ከሜድሮክ ማኔጅመንት እና አመራር መቀበላቸውን በማመን፣ ገንዘቡን የተቀበሉባቸውን የባንክ ደረሰኞች ፍርድ ቤቱ ላዘጋጀው ገለልተኛ ኦዲተር ማረጋገጣቸውን ዋዜማ የተመለከተቻቸው የእነዚሁ ተቋማት ደብዳቤዎች አረጋግጠዋል።

አቶ አብነት ለብልጽግና ፓርቲ የተጠቀሰባቸውን 75 ሚሊየን ብር መስጠታቸውን ፓርቲው ክርክር እየተካሄደበት ላለው ችሎት በፃፈው ደብዳቤ መመስከሩን ዋዜማ ብልጽግና ፓርቲ ከፃፈው ደብዳቤ ተረድታለች። አለባቸው ኃይሉ ወሌ በተባሉ የድርጅቱ የፋይናንስ ግዥና ንብረት አስተዳደር ቡድን መሪ ፊርማ መጋቢት 18 2016 ዓ.ም. ለችሎቱ የተፃፈው ደብዳቤ፣ በአብነት ገ/መስቀል ስም በጥር 13 2020(እ.ኤ.አ.) 75 ሚሊየን ብር ወደ ብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ አካውንት መግባቱን አረጋግጧል። [ዋዜማ]