ዋዜማ- ንግድ ባንኮች ብሔራዊ ባንክ ከሚያወጣው ጨረታ የገዙትን የውጭ ምንዛሬ ለሌሎች ንግድ ባንኮች ከመሸጥ ሊታቀቡ እንደሚገባ ባንኩ አሳስቧል።
ይህ የተባለው፣ ሰኞ’ለት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ በገበያ-መሩ የምንዛሬ ተመን የእስካኹን አፈጻጸም ላይ ባጋጠሙ ችግሮችና ወደፊት መደረግ ባለባቸው ተግባራት ዙርያ ከንግድ ባንኮች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር በመከሩበት ጊዜ ነው።
በዚሁ ምክክር ወቅት፣ አንዳንድ ንግድ ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ በጨረታ የገዙትን የውጭ ምንዛሬ ለሌሎች ባንኮች የመሸጥ አካሄድ እየታየባቸው እንደሆነ የተነሳ ሲሆን፣ ይህም የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በማናር ገበያውን የመረበሽ አዝማሚያ ያለው መኾኑን ዋዜማ በስብሰባው ላይ ከተሳተፉ የንግድ ባንኮች የሥራ ሃላፊዎች ሰምታለች።
ንግድ ባንኮች ብሔራዊ ባንክ የሚያወጣውን የምንዛሬ ጨረታ መሳተፍ ያለባቸው፣ ደንበኞቻቸው ላቀረቡላቸው የውጭ ምንዛሬ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንጂ በጨረታ ያገኙትን የውጭ ምንዛሬ ለሌሎች ባንኮች ከፍ ባለዋጋ በመሸጥ ዋጋ ማናር እንዳልሆነ ተገልጧል ። ይሄም ከምንዛሬ ፈላጊ ነጋዴዎች የሚደርሰውን የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በማስወደድ ገበያውን ስለሚረብሽ፣ በዚህ ድርጊት እየተሳተፉ ያሉ ንግድ ባንኮች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ከስምምነት እንደተደረሰ ሰምተናል።
የውጭ ምንዛሬ ጨረታው ዓላማ፣ የደንበኞች የምንዛሬ ጥያቄ ያለባቸው ባንኮች ለደንበኞቻቸው ምላሽ የሚሰጡበትን መንገድ ማመቻቸትና ዋጋን ማረጋጋት እንጂ፣ የተወሰኑ አቅም ያላቸው ባንኮች የተሻለ ዋጋ ሰጥተው ምንዛሬን በመሰብሰብ መልሰው ለሌሎች ባንኮች መሸጥ እንዳልሆነም በስብሰባው እንደተነሳ ታውቋል።
ባንኮች ለደንበኞቻቸው የሚያቀርቡት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ካላጋጠማቸው በስተቀር፣ በየጨረታው መሳተፍ እንደሌለባቸውም የብሔራዊ ባንኩ ገዥ በስብሰባው ላይ አንስተዋል። የምንዛሬ ችግር የሌለባቸው ባንኮች በየጨረታው የሚሳተፉ እና የሚያቀርቡት ዋጋም ተወዳዳሪ ከኾነ፣ ምንዛሬው ቀጥታ ለተጠቃሚዎች ከመድረስ ይልቅ በባንኮች የመከማቸት እድልን እየፈጠረ መምጣቱም ተወስቷል።
ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠር፣ ባንኮች የምንዛሬ ክምችታቸውን በሌሎች መንገዶች በማሳደግ፣ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው ጨረታ የምንዛሬ እጥረት ያለባቸው ባንኮች ብቻ ቢሳተፉ እንደሚሻል ከስምምነት መደረሱን ዋዜማ ሰምታለች።
ለዚህም ይመስላል፣ ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን ብሔራዊ ባንክ ባወጣው የ50 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጨረታ ላይ የተሳተፉት ንግድ ባንኮች ቁጥር ከባለፉት ሁለት ጨረታዎች አንጻር ከእጥፍ በላይ ቀንሶ የታየው። ለአንድ የአሜሪካ ዶላር አማካይ ዋጋ 131 ብር አካባቢ በተሰጠበት የማክሰኞው የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ላይ የተሳተፉት ባንኮች 12 ሲሆኑ፣ ከዚህ ቀደም በተደረጉት ሁለት የምንዛሬ ጨረታዎች ላይ በእያንዳንዱ ጨረታ የተሳተፉት ባንኮች ቁጥር ግን 27 ነበር።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአንድ ባንክ ፕሬዝዳንት፣ “ባሁኑ ጨረታ የተሳታፊዎች ቁጥር የቀነሰው ለደንበኞቻቸው የሚያስፈልግ የውጭ ምንዛሬ በእጃቸው የሌላቸው ባንኮች ብቻ ይሳተፉ ስለተባለም ሊሆን ይችላል፤ ሌሎች ባንኮች ደሞ የገንዘብ እጥረት ስላለባቸው ባለመሳተፋቸው የተጫራቾች ቁጥር ቀንሶ ሊሆን ይችላል” በማለት ለዋዜማ አስተያየታቸውን ሠጥተዋል።
ብሔራዊ ባንክ ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን ባወጣው የ50 ሚሊዮን ዶላር ጨረታ፣ ለአንድ የአሜሪካ ዶላር የቀረበው ዋጋ ከዚህ ቀደም ከቀረበው 135 ብር ዝቅ ብሎ ወደ 131 ብር ወርዷል። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ቢችሉም፣ ባንኩ ከዚህ በኋላ የምንዛሬ ጨረታን በየ15 ቀኑ ለተከታታይ ወራት እንደሚያቀርብ መግለጹ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል።
ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ባንክ የምንዛሬ ጨረታ የሚያወጣበት ጊዜ የማይተነበይ እና የቀደሙት ኹለት ጨረታዎች የወጡት በተራራቀ ጊዜ መሆኑ፣ ጨረታዎችን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመቁጠር፣ ለአንድ ዶላር የተሰጡ ዋጋዎች ከፍተኛ እንዲሆኑ አድርጓል የሚሉም አሉ።
ባሁኑ ወቅት ብሔራዊ ባንኩ በተከታታይ የምንዛሬ ጨረታ አወጣለሁ ማለቱም፣ ለጨረታው የተሰጠውን አማካይ ዋጋ በመጠኑ ዝቅ እንዳደረገውና ወደፊትም ሊከሰቱ የሚችሉ አላስፈላጊ ግመታዎችን እንደሚያስቀር ታምኖበታል። ይህም የሚሆነው፣ ብሔራዊ ባንክ ለጨረታ የሚያቀርበው የውጭ ምንዛሬ መጠን ትንሽ ቢመስልም፣ ማዕከላዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሬ የሚሸጥበት ዋጋ ግን የምንዛሬ ገበያ ዋጋን እጣ ፈንታ ጠቋሚ በመሆኑ ነው ተብሏል። [ዋዜማ]
ተጨማሪ ዘገባዎች በድምፅ ከታች ይመልከቱ