ዋዜማ ራዲዮ– በኢትዮጵያ ግልጽና ተዓማኒነት ያለውና የምርመራ ጋዜጠኝነት በስርዓት ሊመራ የሚችል መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ኢድሪስ ገለጹ፡፡
የዋዜማ ሪፖርተር ከፓርላማ እንደዘገበው የምርመራ ጋዜጠኝነት በጥሩ ስነ-ምግባር እና ቀድሞ በሚታይ አሰራር በጥንቃቄ የሚመራ ካልሆነ ማህበራዊ ፍትህን በማምጣት ፋንታ የግል ጥቅማቸውን ማስከበር ለሚፈልጉ አካላት ያለአግባብ ሊውል ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ዋና ዳሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከስነ ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም ከህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጋር በመሆን ኮሚቴ ተዋቅሮ የምርመራ ጋዜጠኝነት እንዴት ሊመራ እንደሚገባ የሚያሳይ የአዘጋገብ መመሪያ እያዘጋጁ መሆኑን የተገለጸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤተ የህግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንን የ 9 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ግምገማ ባደረገበት ሚያዚያ 21 ቀን 2014 ዓ.ም ነው፡
የምርመራ ጋዜጠኝነት በመመሪያና በአሰራር ካልተመራ የታሰበለትን ዓላማ ሊያመጣ ስላማይችልና የሚፈጥረው ችግር ከፍተኛ በመሆኑ፣ እንዲሁም ወደ ምርመራ ጋዜጠኝነት የሚሰማሩ ጋዜጠኞች ተገቢው ጥበቃና ከለላ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ረቂቁ ይህንን አሰራር ሊያግዝ በሚቸል መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ረቂቁ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤትን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ሚና ምን መሆን እንዳለበት የሚያመላከት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ረቂቅ መመሪያው ተዘጋጅቶ እንደተጠናቀቀ የሚዲያ ተቋማትን በማሳተፍ ግብዓት ተጨምሮበት ጸድቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዶ.ር አቢይ አህመድ ከሁለት ወራት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አዳራሽ ባደረጉት ንግገር የመገናኛ ብዙሃን የምርመራ ጋዜጠኝነትን በስፋት በመስራት ሌቦችን ማጋለጥ እንዳለባቸው በመጥቀስና የተመወሰኑ ሚዲየዎችን ስም በመጥቀስ የምርመራ ጋዜጠኝነት በስፋት እንደሚሰሩና እያንዳንዱን መስሪያቤትና ኮንትራት እየበረበሩ ማውጣት ይጀምራሉ ማለታቸው ይጣወሳል፡፡
በዚህም የምርመራ ዘጋባ ወቅት ምርመራን ሊያስቆም የሚሞክር ማንኛውም ባለስልጣን ጊዜ አልፎበታል ስራቸሁን በሚታይ መልክ ግልጽ አድርጋቸሁ ስሩ በሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]