Photo- SM

ዋዜማ- በሸገር ከተማ ሥር ባሉ ሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የመምህራን ምገባ መርኃግብር እንደተጀመረ ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።

የምገባ አገልግሎቱ በሸገር ከተማ አሥተዳደር በሁሉም አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ሲሆን ፣ በመርሃ ግብሩ በ256 ትምህርት ቤቶች ስር ያሉ 3 ሺሕ 707 መምህራን ነፃ የምግብ አቅርቦት እንደሚያገኙ ዋዜማ ተረድታለች።

መምህራኑ በሁለት ፈረቃ ጠዋትና ከሰዓት የሚያስተምሩ ሲሆን፣ የጠዋት ፈረቃ መምህራን በተማሪዎች የእረፍት ሰዓት ረፋድ 4 ሰዓት ላይ እንደሚመገቡና የከሰዓት ፈረቃ መምህራን ደሞ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ የሚመገቡ መኾኑን መምህራኑ ነግረውናል።

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው መምህራንም ከኑሮ ውድነቱና ከሚከፈላቸው ደምወዝ አነስተኛ መሆን አንጻር ምገባው መጀመሩ መልካም እንደሆነ ያነሳሉ። መምህራኑ እንደተናገሩት ከሚቀርቡላቸው የምግብ አይነቶች መካከል እንደ ሩዝ፣ መኮሮኒ፣ፓስታ እንዲሁም የተለያዩ የአትክልት አይነቶች ይገኙበታል።

የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ፊረኪያ ካሳሁን፣ የመምህራን ምገባ መርሃ ግብሩን መጀመር ያስፈለገው በዋናነት በትምህርት ጥራት ላይ ለማምጣት ለሚታሰበው ለውጥ ቁልፍ ድርሻ እንዳለው ስለታመነበት ነው ብለዋል።

በአገሪቱ በትምህርት ስርዓቱ ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ያወሱት ፊረኪያ፣ ያንን ለመጠገን መምህራን ላይ በሰፊው መስራት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል። ለዚህም ሲባል የመምህራን ምገባ መርኃ ግብሩን መጀመር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንና መምህራንም ኃላፊነታቸው በአግባቡ ለመወጣት በተወሰነ መልኩም ቢሆን እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል። በተጨማሪም መምህራን ከትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ሳይወጡ ተማሪዎቻቸውን በቅርበት ለማግኘትና ለመርዳት እንዲሁም ተረጋግተው ሥራቸውን ለመስራት የምገባ መርኃግብሩን መጀመሩ መልካም የሚባል ጅማሮ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በሌሎች አገራትም መምህራንን የመመገብ መርኃ ግብር እንዳለ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ያወሱት የትምህርት ቢሮ ኃላፊው፣ በእነዚሁ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ስርዓቱ ላይ የሚታየው ለውጥ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማዋ ከመምህራን በተጨማሪ በሁሉም አንደኛ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ መርኃግብር መጀመሩንም ዋዜማ ተረድታለች። በከተማዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ስር ባሉ አንደኛ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ፣ በስሩ ለ148 ሺሕ 795 ተማሪዎችን ማቀፍ መቻሉን ዋዜማ ከትምህርት ቢሮው ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ የምገባ መርኃ ግብርም በምግብ አቅርቦት እጥረት የሚመጣ የተማሪዎችን ትምህርት የማቋረጥ ችግር ማስወገድ የተቻለ ሲሆን፣ መምህራንም በመማር ማስተማር ሥራው የበለጠ እንዲተጉ አድርጓቸዋል ተብሏል። [ዋዜማ]