ዋዜማ- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች እንደ አገልግሎታቸው ዓይነት “ወጥ ቀለም” እንዲይዙ እና አሽከርካሪዎችም የራሳቸው የስራ የደንብ ልብስ እንዲኖራቸው ለማድረግ እቅድ እንደተያዘ ዋዜማ ሠምታለች።
የክልል ከተሞችም በሚወስኑት የቀለም ዓይነት አሠራሩን በአገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎቻቸው ላይ ተግባራዊ ያደርጋሉ።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚንስቴር በባለፈው ሳምንት ሚያዚያ 24 የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ ውይይት ካደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ፣ የተጠሪ ተቋማት “የብራንድ ለውጥን” የተመለከተው ይገኝበታል።
በከተማዎች የሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች “ወጥ ቀለም” እና “መለያ ኮድ” እንዲኖራቸው የማድረግ ጉዳይም የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ላይ የተነሳ ሌላኛው አጀንዳ ነበር።
የትራንስፖርት አገልግሎቶች የተቀናጁ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት በአዋጅ የተጣለበት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር፤ የመስሪያ ቤቱን ኃላፊነት የሚወክል አዲስ አርማ እንዳዘጋጀ በውይይቱ ላይ ተገልጿል። በአዲስ መልክ የተዘጋጀው የተቋሙ መለያ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚንስትሩ ዓለሙ ስሜ ተናግረዋል።
ሚንስትሩ፤ እርሳቸው በሚመሩት መስሪያ ቤት የተጀመረው “የብራንዲንግ” ሂደት ወደ ተጠሪ ተቋማት እና ተሽከርካሪዎችም መውረድ እንዳለበት ተናግረዋል። በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ እየተገነባ ያለውን የኮሪደር ልማት የጠቀሱት ዓለሙ፤ ልማቱን የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ለኀብረተሰቡ የሚመጥነውን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማቅረብ እንዲቻል ያረጁ ተሽከርካሪዎች ከሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ውጭ መደረግ እንዳለባቸው ሚንስትሩ በአጽንኦት መናገራቸውን ዋዜማ ሰምታለች።
“በኮሪደር የለሙ ከተሞችን ማሰብ አለባችሁ። ትራንስፖርቱ ከተማውን ይምሰል። አደራጁ፣ ብድር እናመቻች፣ ከኩባንያዎች ጋር እንነጋገርና አሮጌ መኪናዎች ከመንገድ ላይ ይውጡ። አዲስ አበባ ውስጥ ያለ ትራንስፖርት ከተማዋን አይመጥንም” በማለት ዓለሙ በውይይቱ ለታደሙ የተቋማት አመራሮች አሳስበዋል።
ሚንስትሩ አክለውም፣ “መንገዶች ተስተካክለዋል፤ የእግረኛ መንገዶች ተውበዋል፤ ተሽከርካሪዎች ግን መንገዱን የሚመጥኑ አይደሉም” ብለዋል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚንስትሩ አያይዘውም፤ በከተማዎች ውስጥ ያሉ የሕዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ቀለም መለየት እና ወጥ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። “አስር ሰው የሚጭነው ተሽከርካሪም ሆነ አውቶብሱም መመሳሰል የለበትም” ያሉት ዓለሙ፣ የተሽከርካሪ ቀለም ልየታው “በሌሎች አገራት የተለመደ” አሰራር መሆኑንም አብራርተዋል።
“ሌላ አገር አይታችሁ ከሆነ የየከተማው ታክሲ የየራሱ ብራንድ አለው። የማን ታክሲ እንደሆነ፣ የየትኛው ከተማ ታክሲ እንደሆነ በቀለም ነው የሚታወቀው፤ ስለዚህ እሱን እንድታስቡበት ነው” በማለትም አስተያየት ሰጥተዋል።
ይህ አሰራር ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎችም የክልል ከተማዎች ወርዶ ተግባራዊ እንደሚሆን እና የየከተማዎቹ ተሽከርካሪዎች የራሳቸው መለያ የሆነ ቀለም እንደሚኖራቸውም ዓለሙ ጠቁመዋል።
“የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች አንድ ዓይነት ቀለም ይኖራቸዋል ማለት ሳይሆን፣ አዳማ የራሱን፣ ቢሾፍቱ የራሱን፣ ጎንደር የራሱን ባሕርዳር የራሱ መለያ ይኖረዋል ማለት ነው” በማለትም ዓለሙ አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ፤ በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚንስቴር የተነሳውን ይህንን የሕዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን ቀለም የማስተካከል ሒደት ውይይት እያደረገበት እንደሆነ የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ያብባል አዲስ ለዋዜማ ነግረዋታል።
እቅዱ ከተማዋን ወደ “ስማርት ሲቲ” የመለወጥ አንዱ አካል መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ ረገድ በከተማዋ “አሁን ያለው የተሽከርካሪ ቀለም ዥንጉርጉር ነው” ያሉት ያብባል፤ “የትኛው የሕዝብ ትራንስፖርት ይሁን፣ አገር አቋራጭ ይሁን በደንብ የሚታወቅ አይደለም” በማለት ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም፤ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ “ታክሲዎች፣ ሚኒባስ፣ ሚዲ ባስ፣ ባስ እና ባጃጅ አሉ። እስካሁን ባለው ሁኔታ ኮድ አንድ ከሚባሉት ታክሲዎች ውጭ፣ ይሄ ሁሉ የተለየ ቀለም የለውም። ስለዚህ ለዚህ ሁሉ አዲስ መለያ መስጠት አስፈላጊ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የሜትር ታክሲና የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ታክሲዎች ቀለምም መወሰን እንዳለበትም ሃላፊው ለዋዜማ ነግረዋታል። ከወጥ ቀለም በተጨማሪ ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት ተሽከርካሪዎች የሚሰጣቸው ኮድ እንደሚኖር እና አሽከርካሪዎችም የየራሳቸው አልባሳት እንደሚኖራቸው ዋዜማ መረዳት ችላለች።
ያብባል፤ “ይህ መደረጉ፣ ባንድ በኩል አገልግሎቱ ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆን ያደርጋል፤ በሁለተኛ ደረጃ፣ ግልጽ የሆነ የደንብ ልብስ የለበሰና ግልጽ የሆነ አግልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ ሲኖር፣ ለተጠቃሚውም ደኅንነት አመቺ ነው” ሲሉ አስፈላጊነቱን አብራርተዋል።
የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን ቀለም የመለወጡን አፈጻጸም አስመልክቶ ከዋዜማ ጥያቄ የቀረበላቸው ያብባል፤ ገና በውይይት ላይ ያለ እንጂ ጸድቆ ወደ ስራ እንዳልገባ በመግለጽ፤ “የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት ተግባራዊ ሲሆን የምናየው ነው የሚሆነው” የሚል ምላሽ ሠጥተዋል። [ዋዜማ]