ዋዜማ ራዲዮ- ሀገሪቱ ባለፈው አንድ አመት የገባችበት ጦርነት ያስከተለውን ውድመትና ቀውስ ለማካካስ የሚያስችል በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች ላይ ያተኮረ የመልሶ ማቋቋም መርሀ ግብር ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለበት የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ አቀረቡ። ከአንድ ዓመት በፊት የተዘጋጀው የ10 አመት የልማት ዕቅድ ጦርነት ባስከተለው ቀውስ ሳቢያ የታሰበለትን ግብ መምታት ስለማይችል ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ እንዲከለስም ባለሙያዎቹ መክረዋል። ዝርዝሩን ያንብቡት
የፌደራል መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ከህወሓት አማፅያን ጋር እያካሄደ ከሚገኘው ጦርነት ጎን ለጎን በጦርቱ ማግስት ጉዳት የደረሰባቸውን ክልሎች ለማቋቋም የሚያስችል አገራዊ እቅድ እንዲዘጋጅ ጠየቁ፡፡
ከአንድ አመት በላይ በዘለቀው ጦርነት በአማራ፣በአፋርና በትግራይ ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የትምህርት፣የጤና እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች አገልግት እዳይሰጡ ሆነው መውደማቸው በተደጋጋሚ መነገሩ ይታወሳል፡፡
የትምህርት ሚንስቴር ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል በህወሓት ታጣቂዎች ወደሙ የተባሉ ከ4 ሺህ የሚበልጡ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡
በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋምና ለመገንባት እንዲሁም አገሪቱ ከአንድ አመት በፊት መተግበር የጀመረችውን የአስር አመት የልማት እቅድ ከዚህ የጦርነት ሁኔታ ጋር አጣጥሞ እንዴት መሄድ ይቻላል ስትል ዋዜማ ራዲዮ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን ጠይቃለች፡፡
በዚህ ጦርነት መሰረተ ልማቶች በተለይም የትምህርት ተቋማት፣የጤና ተቋማት ፣ የግብርና ተቋማት ወደሙ ሲባል አንዳው በግርድፉ መቃጠላቸው ወይም መፈራረሳቸውና ለጊዜው አገልግሎት ባለመስጠታቸው ብቻ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ደግየ ጎሹ (ዶ/ር) ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በተዘዋዋሪ በእነዚሀ በወደሙ ተቋማት ይማር የነበረው ተማሪ ትምህርት ባለመማሩ የሚፈጠረው ማህበራዊና ተተኪ ትውልድን በአስፈላጊው ሰዓት ማፍራት አለመቻሉ፣ የጤና ተቋም አገልግሎቶች በመውደማቸው የተነሳ በህክምና እጦት ያለጊዜው የሚሞተው አምራች ሃይልና የግብርና ተቋማት በመውደማቸው ማምረት የነበረባቸው ምርት መመረት አለመቻል እንዲሁም በተቋማት ውድመትና ጥፋት ምክንያት ያለስራ የተቀመጠው የሰው ሃይል እንዲሁም መሰል በርካታ ችግሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት ችግሩን ሊያቃልል የሚችል የተለየ እቅድ መሰራት እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡
ደግየ እንደሚሉት አሁን መንግስት እየተገበረው ካለው የአስር አመት አቅድ ጋር አገሪቱ በምትፈልገው ልክ ሶስቱ ክልሎች ከዚህ ጦርነት ወጥተው ወደ ስራ እንመለስ ቢሉ የአስር አመት አቅድ ሳይሆን የመልሶ ማልማት ስራ ላይ እንደሚጠመዱና ለዚህም በርካታ አመታት እንደሚፈጅባቸው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በሌለ ትምህርት ቤት ትምህርትን እዚህ አደርሳለሁ ወይንም በሌለ የጤና ተቋም የጤና ተደራሽነትን እዚሀ አደርሳለሁ የሚል አቅድ እንደማይኖራቸው አክለው ገልጸዋል፡፡
ስለሆንም መተግበር ከጀመረው የአስር አመቱ አቅድ በተለየ መልኩ ችግር ካልደረሰባቸው አካበቢዎች በተለየ መልኩ የችግሩ ሰላባ ለሆኑት የአገሪቱ አካባዎች ራሱን የቻለ በፌደራል መንግስቱ የሚመራ የራሱ የሆነ እቅድ ተዘጋጅቶለት በአፋጣኝ ወደ ስራ መግባት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ እስከ ሰላሳ በመቶ ሀገራዊ ምርት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሊታጣ እንደሚችል ግርድፍ ግምት አላቸው።
ከዚህ በተጨማሪም ከጦርቱ ባሻገር የዋጋ ንረቱ ከጊዜ ጊዜ መሻሻልን ማሳየት የተሳነው ወቅት በመሆኑ መንግስት እያንዳዱን ችግር በልኩ በመረዳትና የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ላይ ማትኮር የመጀመሪያ ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ መንግስት የጀመረውን ጦርት በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደለበትና አገሪቱ ከ 2013 ዓ.ም ጀምሮ መተግበር የጀመረችውን የአስር አመት ስትራቴጅክ እቅድ እንደገና መከለስ እንደሚገባ ለዋዜማ የጠቀሱት በአርባ ምንጭ ዩንቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ኮሌጅ ዲንና የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት መስፍን መንዛየ (ዶ/ር ) ናቸው፡፡
አሁን የተፈጠረው የዋጋ ንረት ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአጭሩ ካልተቋጨ አገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊያመጣ እንደሚችል አክለው መስፍን ጠቁመዋል፡፡
የሚወድመው ንብረት፣ ገቢ ምርቶች ላይ የሚፈጠር ጫና፣ክልከላዎችና ሌሎች በርካታ ማነቆዎች በመቀጠላቸው፣ አሁን ላይ በተባባረ ከንድ ጦነቱን በአጭር መቋጨት ካተቻለ ከፍተኛ የሆነ አገራዊ ቀውስ ያስከትላል፡፡
ይህ ማለት አሁን እንደሚታየው የህዘቡም ሆነ የመንግስትም ትኩረት ጦርነቱ ላይ በመሆኑና ምርትም ማምረት ካልተቻለና ከውጭ የሚገባውም ገቢ ምርት ከቀነሰ በዛው ልክ ለሚፈናቀሉ ወገኖች የሚወጣው ወጭ አገሪቱን እዳ ውስጥ እንደሚከታት ባለሙያው ያስረዳሉ።፡፡
በተመሳሳይ እንደ አገር የተቀመጠው የአስር አመት አቅድ ከአንድ አመት በላይ በዘለቀው በጦርነት ምክንያት ስራዎች ባለመሰራታቸው ምክንያት የታሰበውን ውጤት እንደቀላል ማምጣት ስለማይቻል አንደገና መታየትና መስተካከል ይኖርበተል ያሉት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር ስሜነህ በሴ ናቸው፡፡
የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ለዋዜማ እንደተናገሩት በጦርነት ቀጠና ያሉ አካባቢዎች ላይ የደረሰው ጉዳትና የወደመውን ሃብት ለመመለስ ረጅም ጊዜና ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ በመሆኑ እንደ ድሃ አገር እየተከፈለ ያለው ዋጋ በቀላሉ የሚተመን አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፤
በዚህም የተነሳ እነዚህን በጦርነት የወደሙ ቀጠናዎችን ከገቡበት ቀውስና ጉዳት ሊያወጣና እንዲያገግሙ የሚያስችል በአጭርና የመካከለኛ ጊዜ የተለዩ እቅዶችና ፖሊሲዎች አስፈላጊ ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አምዴሳ ተሸመ (ዶ/ር) በሌላ በኩል በርካታ አገራት በጦርነት ውስጥ እያለፉ ያሉና በጦርነት ውስጥ አልፈው የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱ አገራት ኢትዮጵያ እንደገባችበት ውስብስብ አይነት ችግር ገብተው እንዴት እንደወጡ ልምድ መውሰድ አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
በሌላ በኩል አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው የአገሪቱ ክፍሎች የፖሊሲና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የሚደረገውን የስራ እንቀስቃሴ በእጥፍና ከዚያ በላይ በማሳደግ ምርታማነትን መጨመር እንደሚቻል አክለው ገልጸዋል
ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት የአስር አመት እቅዱ እንደገና በመፈተሸ ከተከሰተው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ መስራት ያስፈልጋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]