ዋዜማ ራዲዮ- መንግስት ከሳዑዲ ዓረቢያ እስርቤቶችና ማቆያ ማዕከላት ወደአገራቸው ሊመልሳቸው ካቀደው 102 ሺ ዜጎች መካከል እስከ ሚያዚያ 12 2014 ዓ.ም ድረስ 11, 700 ዜጎች ወደ አገራቸው መግባታቸውን ዋዜማ ሰምታለች። እነዚህን ዜጎች ለመመለስም እስካሁን 27 በረራዎች ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ተደርገዋል ።
ተመላሾቹ አዲስ አበባ በሚገኙ 8 ማቆያ ማዕከላት የተለያዩ አገልግሎቶች ይቀርብላቸዋል። ተቋማት በቅንጅት የምግብ: መኝታ :አልባሳት ለህፃናት ወተት እንዲሁም የስነልቦናዊ ድጋፍ በባለሙያዎች እያቀረቡ እንደሚገኙ ለማወቅ ችለናል።
ከተመላሾች መካከል አብዛኞቹ ወደ ቀደመ አካባቢያቸው እየተመለሱ ይገኛሉ። እስካሁን ወደ አገርቤት ከተመለሱ ዜጎች መካከል 95 ከመቶው ለእያንዳንዳቸው አንድ ሺ ብር የኪስ ገንዘብ እየተሰጣቸውና እስከ ዞን ከተሞች ድረስ ነፃ የትራንስፖርት አቅርቦት ተመቻችተውላቸው ወደ ትውልድ አካባቢያቸው እንደተመለሱ ለማወቅ ችለናል ።
ይሁንና በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት 1,648 ዜጎች ወደ አካባቢያቸው መመለስ ባለመቻላቸው በማቆያ ማዕከላት ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ዋዜማ ሰምታለች።
በሳዑዲ ዓረቢያ ሰነድ ከሌላቸውና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከሚገኙ ዜጎች መካከል 102 ሺ የሚሆኑትን ከ 7 እስከ 11 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደአገራቸው የመመለሱ ስራ መጋቢት 30 2014 ዓ.ም መጀመሩ የሚታወስ ነው።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ቀን የመመለሱ ተግባር 13 ቀናት ያስቆጠረ ሲሆን በቀን በአማካይ ከ900 እስከ 1000 ያህል ዜጎች እየተመለሱ ነው ። በዚህ ፍጥነት እንኳ ቢቀጥል በ7 ወራት ከታቀደው በላይ ከ150 ሺ ዜጎች በላይ ወደአገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይቻላል ።
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትት ፍልሰተኞች በየዕለቱ የሚደረጉ በረራዎች ቁጥር እንዲጨምር እየጠየቁ ይገኛሉ።
በሳዑዲ ዓረቢያ ከ400ሺ በላይ ሰነድ የሌላቸው ዜጎች ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል። የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት እነዚህን ሰነድ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን በሙሉ ወደአገራቸው የመሸኘት ዕቅድ አለው።
የኢትዮጵያ መንግስት ከደህንነት እና ከቅድመ ዝግጅት ጋር በተያያዘ ዘግይቶ በተጀመረው ዜጎችን የመመለስ ተግባር ከ7 እስከ 11 ወራት ውስጥ ለመመለስ የታቀደው ሰነድ ከሌላቸው ዜጎች መካከል አንድ አራተኛውን ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]