Fana CEO Admasu Damtew- FBC

ዋዜማ ራዲዮ- የቀድሞ ገዢው ፓርቲ ንብረት የሆኑት ዋልታ አዲስ ሚዲያንና ፋና ሚዲያ ኮርፖሬት (ራዲዮ ፋናን) በአንድ አጠቃሎ “ጠንካራ ሚዲያ” ለማድረግ በመንግስት አካላት ሲደረግ የነበረው ሂደት ተገባዶ ርክክብና ሽግግር እየተከናወነ መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች።


ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ የማዋሀድ ስራው የተጀመረ ሲሆን የሁለቱን ሚዲያዎች አዲስ ጥምረት በቦርድ ስብሳቢነት እንዲመሩ የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተመድበዋል። በስራ አስፈፃሚነት ደግሞ የራዲዮ ፋና ስራ አስኪያጅ አድማሱ ዳምጠው እንዲቀጥሉ ተወስኗል።

ሌሎች የበታች አመራሮችን የመመደብ ስራ በዚህ ሳምንት የሚቀጥል ሲሆን የዋልታ ሚዲያ ስራ አስፈፃሚ የነበሩት አቶ መሀመድ ሀሰን እስካሁን አልተመደቡም። አቶ መሀመድ ከውህደቱ ወራት አስቀድሞ ሀላፊነታቸውን ውክልና ሰጥተው በአብዛኛው በስራ ገበታ ላይ እንደማይታዩ የሰራ ባልደረቦቻቸው ለዋዜማ አረጋግጠዋል።


ከውህደቱ ጎን ለጎን የስራ አስፈፃሚውና የፋይናንስ ቢሮው ታሽጎ የሂሳብ ሰነዶች ምርመራ መጀመሩን ለጉዳይ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ነግረውናል። ይህ አሰራር የድርጅቱን የግብር ሀላፊነት ለመዝጋትና ለርክክብ የሚደረግ መሆኑን ጉዳዩን በሀለፊነት ከሚመሩት አካላት ሰምተናል። ሰራተኞች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ወደ ስራ ሲገቡና ሲወጡ በጥብቅ እንደሚፈተሹ እንዲሁም ላፕቶፕ ኮምፒተሮችን ይዞ መግባትም ሆነ መውጣት መከልከሉን ነግረውናል።


አቶ መሀመድ ዋልታን በመሩበት አመታት በሚሊየኖች ብር የሚቆጠር የፕሮጀክት ስራዎች ያስጀመሩ ሲሆን ዘመናዊ አውቶሞቢሎችን በመግዛትና ከሚዲያ ስራ ውጪ በርከት ያለ ገንዘብ መድበው እንደነበር ለጉዳይ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለዋዜማ ይናገራሉ።


በዋልታ ሚዲያ ስለነበረው የፋይናንስ እንቅስቃሴ አውቃለሁ የሚሉ የቀድሞ የድርጅቱ ባልደረባ “ዋልታ ከሚያገኘው ገቢ በአስር እጥፍ የሚበልጥ” ወጪ ያወጣ እንደነበረና አብዛኛው ገንዘብም ከመንግስት ምንጮች የሚመጣ እንደነበር ይመሰክራሉ።


የስራ አስፈፃሚውና የፋይናንስ ቢሮዎች የታሸጉት በሽግግር ወቅት መረጃዎች እንዳይጠፉ ለማድረግ እንጂ “የተለየ የሙስና ጥርጣሬ ኖሮ አይደለም” የሚሉት አሁን በስራ ላይ ያሉ የድርጅቱ የአስተዳደር ሰራተኛ ደግሞ ቀደም ባሉ አመታት የተገዙ አራት ውድ መኪናዎችና አንዳንድ ፕሮጀክቶች ጉዳይ የመንግስት አካል ባለበት ተገምግሞ ስህተት እንደነበረ ተማምነን ተፈቷል ይላሉ።

አቶ መሀመድ ሀሰን በጠቅላይ ሚንስትሩ የህይወት ታሪክ ዙሪያ “ሰውየው” በሚል ርዕስ መፅሐፍ የፃፉና የቀድሞ የራዲዮ ፋና ጋዜጠኛ ናቸው። አራት መቶ ስራተኞች ያሉት ዋልታ ሚዲያ ከአንድ ሺህ በላይ ሰራተኞች ካሉት ራዲዮ ፋና ጋር ተዋህዶ በሀገሪቱ “ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ” ለመሆን ግብ ማስቀመጡን የውህደት አመቻች ከሆኑት ምንጮች ተረድተናል።


በውህደቱ ስራችንን እናጣለም የሚል ስጋት ያላቸው ሰራተኞች በዚህ ሳምንት ስለ ዕጣ ፈንታቸው ለመስማት በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ውህደቱን ከሚመሩት ወገኖች እንደሰማነው ግን ዋልታም ሆነ ፋና ከስመው በአዲስ መልክ የሚመሰረትና የፋናን ስም ይዞ የሚቀጥል ተቋም ይኖራል። በዚህ ሂደትም ከስራው የሚሰናበት እንደማይኖር መረጃውን አጋርተውናል።


የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግስት ወደ ስልጣን እንደመጣ የፓርቲ ንብረት የሆኑትን ሚዲያዎች ለመዝጋት ከውሳኔ ተደርሶ የነበረ ቢሆንም አፈፃፀሙ አስቸጋሪ ስለነበር እንዲዘገይ ተደረጎ ነበር። በሂደት ግን የራዲዮ ፋናን አመራር በመከለስ የህዝብ ሚዲያዎችን እንዲገዳደር በርካታ ገንዘብ ተመድቦለት እንዲጠናከር ተደርጓል።

ፋና የሕወሓት-ኢሕአዴግ የትጥቅ ትግል ሚዲያ ሆኖ የተጀመረና በኋላ በንግድ ራዲዮ ስም የቀጠለ ሲሆን ዋልታ ደግሞ “የኢሕአዴግ የመረጃ ማዕከል” በሚል ይታወቅ ነበር። ዋልታ መጀመሪያ የዜና ወኪል ሆኖ ለዓመታት የሰራ ሲሆን በቅርብ አመታት ወደ ኤሌክትሮኒክ ሚዲያ ዘርፍ ተሸጋግሯል። [ዋዜማ ራዲዮ]