Photo credit-The Reporter

ዋዜማ- የስጋ አምራችና ላኪ ኩባንያዎች የገቢዎች ሚኒስቴር በግምት በሚጥልባቸው ከፍተኛ ግብር የተነሳ ስጋ ወደውጪ መላክ ማቋረጣቸውን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ተረድታለች።


በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠር ግብር እንዲከፍሉ የተጠየቁ ኩባንያዎች መኖራቸውንና በዚህም ሳቢያ አጠቃላይ ስጋ አምራችና ላኪ ኩባንያዎች ችግሩ እንዲሰተካከል መንግስትን መጠየቃቸውን እሁን ባለው አሰራር ግን ስጋ ወደውጪ ለመላክ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር የስጋ ላኪ ኩባንያዎች ላይ አድርጌዋለሁ ያለው ኦዲትን ተከትሎ በስጋ ላኪ ኩባንያዎች ላይ በመቶ ሚሊየኖች በላይ ግብር በመጣሉ ስጋ ላኪ ኩባንያዎቹ የተጣለብን ግብር ተገቢ ካለመሆኑም በላይ ከካፒታላችን በላይ በመሆኑ ስራ ለመቀጠል እንቸገራለን ብለዋል።

ዋዜማ በስጋ አምራችና ላኪዎቹ እና በገቢዎች ሚኒስቴር መካከል በግብር አተማመን ዙርያ የተፈጠረውን ያለመግባባት ምንጭ ለማጣራት ባደረገችው ጥረት፣ ያለ መግባባቱ መነሻ ስጋ ላኪዎች ከአቅራቢዎች ለእርድ የሚሆነውን እንስሳ በሚገበያዩበት ወቅት የደረሰኝ አለመኖር መሆኑን ተረድታለች።

በኢትዮጵያ ውስጥ የቁም እንስሳ ግብይት ዙርያ እስካሁን ያልተፈታ የደረሰኝ አሰጣጥ ችግር አለ። በሀገሪቱ ያሉ 12 የሚደርሱ የኤክስፖርት ቄራ ያላቸው ስጋ ላኪ ኩባንያዎች ደግሞ ለሚልኩት ስጋ እንስሳት የሚረከቡት ከአቅራቢዎች እና ከአርብቶአደሮች ነው። አቅራቢዎቹ ደግሞ እንስሳቱን የሚረከቡት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ ካሉ አርብቶ አደሮች ነው።

እነዚህ ለኤክስፖርተሮች እንስሳት የሚያቀርቡ አካላት ከአርብቶ አደሮች እንስሳቱን ሲገዙ ከአርብቶ አደሩ የአኗኗር ሁኔታ አንጻር ለገዟቸው እንሰሳት ከአርብቶ አደሮች ደረሰኝ አይሰጣቸውም። አቅራቢዎቹም ያለ ደረሰኝ የገዟቸውን እንስሳት ፣ ለውጭ ገበያ ለሚያቀርቡት ለባለ ኤክስፖርት ቄራ ኩባንያዎች ያለ ደረሰኝ ለመሸጥ ይገደዳሉ ።ተገቢውን ደረሰኝ የማቅረቡ ችግር መነሻውም ከአርብቶ አደሩ የሚጀምር ነው።

አስካሁን ለግብር አወሳሰን ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ ያለው እንስሳቱን የገዛው አካል የሚያቀርበው የግዥ ሰነድ ነው።

በዚህ ጊዜ ደግሞ ገዥው ኩባንያ ወይንም ግለሰብ ግብር እንዲቀንስለት ለግዥ ያወጣውን ወጭ ከፍ ያደርጋል በሚል ገቢዎች ሚኒስቴር በ2014 አ.ም አንድ መመሪያን ተግባራዊ አድርጓል።

መመሪያውም የግዥ ደረሰኝ የማያቀርብ ኩባንያ ወይንም ግለሰብ ለግዥ አወጣሁት ካለው ገንዘብ ውስጥ 65 በመቶው ብቻ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ይደነግጋል። ቀሪው 35 በመቶውን ገንዘብ ለግዥ ቢያወጣውም እንደወጪ ሳይቆጠርለት ይቀርና ነጋዴው  ከዚሁ ውድቅ ከተደረገበት 35 በመቶው ወጭ ላይ 30 በመቶውን ግብር እንዲከፍልም የ2014ቱ መመሪያ ያዛል።

በወቅቱ አርብቶ አደር የማህበረሰብ አካላት እንስሳቶቻቸውን ሲሸጡ ደረሰኝን ከመቁረጥ አንጻር ስለሚቀራቸው እንዴት ይደረግ የሚል ጥያቄ በመነሳቱ ፣ አርብቶ አደሩ ደረሰኝ የማያቀርብ ከሆነ ከአርብቶ አደሩ እንስሳት የሚገዙና ለኤክስፖርት ቄራ የሚሸጡ አቅራቢዎች በገቢዎች የተፈቀደ ደረሰኝ(ቫውቸር) ሊሰጧቸው ይችላል የሚል መመሪያም ወረደ። በዚሁ ደረሰኝ ላይ የእንስሳቱን ዋጋ የሚጽፈው አርብቶ አደሩ ሳይሆን ገዥው ነው።

ሆኖም ከአርብቶ አደሮች እንስሳትን ገዝተው ለኤክስፖርት ቄራ ኩባንያዎች የሚያቀርቡ ነጋዴዎች ራሳቸው በሚሰጡት ደረሰኝ ላይ “ወጭያችሁን አጋናችሁ ግብር እንዲቀንስላችሁ በደረሰኝ ላይ ትጽፋላችሁ” በሚል ከየክልሉ ገቢዎች ቢሮ ጋር መግባባት ባለመቻላቸው የደረሰኝ ግብይቱ ችግር ይገጥመዋል። በዚህም ሳቢያ ለስጋ ኤክስፖርት የሚውሉ እንስሳት ላይ የደረሰኝ ግብይትን መተግበር ባለመቻሉ ከዚህ ቀደም ለሶስት ቀናት የስጋ ኤክስፖርት ቆሞ ነበር።

ግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ባደረጉት እንቅስቃሴም ፣ ለበርካታ አመታት የቆየ የግብይት ብልሽት በአንዴ ሊስተካከል አይችልም ፣ ስለዚህም የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገው ከአርብቶ አደሩ ጀምሮ ሁሉም ደረሰኝ እስኪሰጥ ባለው አሰራር ግብይቱ ተካሂዶ ኤክስፖርቱም እንዲቀጥል ተደረገ። በቁም እንስሳቱ ግብይት ላይ ሁሉም ደረሰኝ የግድ መጠቀም እንዲኖርበት የተቀመጠው ጊዜም ትናንት ጥር 1 ቀን 2017 አ.ም ነበር።

ሆኖም ከአርብቶ አደሩ ጀምሮ ያለው የግብይት ስርአት በደረሰኝ እንዲሆን ሊደረጉ የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ የኤክስፖርት ቄራ ኩባንያዎች የደረሰኝ ግብይት ግድ የሚሆንበት የጊዜ ገደብ ከመድረሱ በፊት የፈጸሟቸው ግዥዎች በሙሉ ኦዲት እየተደረጉ ያለደረሰኝ የፈጸሟቸው ግዥዎች 35 በመቶ ውድቅ እየተደረገ ከፍተኛ ግብር እየተጣለባቸው መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች።

ሶስት ኩባንያዎችም በዚሁ አሰራር በመቶ ሚሊየኖች የሚገመት ግብር ክፈሉ የተባሉ ሲሆን ቀሪዎቹም በከፍተኛ ስጋት ኤክስፓርት ስራው እንዳይቆሞ ሲሰሩ ቆይተዋል ። ኩባንያዎቹም በዚህ ሳቢያ በደረሰኝ እንስሳት የሚያቀርብላቸው ባለማግኘታቸው ከትናንት ጀምሮ የስጋ ኤክስፖርት እንደቆመ ተረድተናል። በዚህም ሀገሪቱ በየቀኑ ከግማሽ ሚሊዬን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ የምታጣ ሲሆን የውጭ የስጋ መዳረሻ ገበያም በሌሎች ተወዳዳሪ ሀገራት የመወሰድ ስጋት ውስጥ ገብቷል።

የስጋ ኤክስፖርት ዘርፍ በተለይ ከምንዛሬ ተመን ለውጡ በኋላ እየተበረታታ የነበረ ዘርፍ ነው። በዚህ በጀት አመት የመጀመርያ ሶስት ወራት 24 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያስገኘ ሲሆን ፣ በስራ ላይ የነበሩት 12 የኤክስፖርት ቄራ ኩባንያዎች ለ6,500 ዜጎች ቀጥተኛ የስራ እድል ፈጥረዋል። [ዋዜማ]