ዋዜማ- ግዙፉ መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተለያዩ ዘርፎች በሰጠው እና ወደፊት በሚሰጠው ብድር ላይ የወለድ ጭማሬ ማድረጉን ዋዜማ ባንኩ ጭማሬውን ተግባራዊ ሊያደርግበት ካዘዋወረው ሰነድ መረዳት ችላለች።
አዲሱ የባንኩ የወለድ ተመንም ከፊታችን አርብ የካቲት 28 ቀን 2017 አ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም ዋዜማ ተገንዝባለች።
የቁጠባ ማሰባሰቢያ ወጪ ከፍተኛ መሆኑ ፣ ከሌሎች ባንኮች አንጻር የሚያስከፍለው ወለድ አነስተኛ መሆኑ እና የባንኩን ዘላቂ ትርፍ ማሳደግ ለወለድ ተመኑ ማሻሻያ እንደ ምክንያትነት ተቀምጧል። በዚህም እስከ ስድስት በመቶ የወለድ ተመን ጭማሬን ተግባራዊ እንደሚሆንም ባንኩ አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተግባራዊ ሊያደርገው ከተዘጋጀው የወለድ ጭማሬ ሰነድ ላይ እንደተረዳነውም የወጪ ንግድ ዘርፍ ላልሆኑ ለጅምላ የሸቀጦች ንግድ ተበዳሪዎች ሲያስከፍል የነበረውን የ15.5 በመቶ ወለድን ወደ 16.5 በመቶ ከፍ አድርጎታል።
በሸቀጦች የወጪ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ተበዳሪዎች ሲያስከፍል የነበረው 8.5 በመቶ ወለድ ወደ 12 በመቶ ፣በዚሁ በወጪ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ተበዳሪዎች የሚሰጠው የቅድመ ጭነት(pre shipment ) ብድር ላይ በተመሳሳይ የነበረውን የ8.5 በመቶ ወለድ ወደ 12 በመቶ አሳድጎታል።
የውጭ ምንዛሬ ለባንኩ ለሚያመጡ ግለሰብ ደንበኞች እና ተቋማት እንዲሁም የተቋማት ተቀጣሪዎች ይጠይቅ የነበረው የ7 በመቶ ወለድን ከአራት እስከ ስድስት በመቶ ነጥብ(percentage point) በመጨመር የወለድ ተመኑን ወደ 11 እና 13 በመቶ ከፍ እንዲል በባንኩ ተወስኗል።
ነገር ግን ባንኩ ለግብርና ዘርፍ ተበዳሪዎች የወለድ ቅናሽን አድርጓል።
በዚህም ፣ ማዳበሪያን ጨምሮ ለግብርና ከተሰጠ እና ከሚሰጥ ብድር ላይ የአጭር ጊዜ ብድሩ የ14 በመቶ ወለድ ባለበት እንዲቀጥል፣ የመካከለኛ ጊዜ ብድር ከ15.5 በመቶ ወደ 14.5 በመቶ ዝቅ እንዲል፣ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ በሚከፈለው የግብርና ብድር ላይ ደግሞ ይጠየቅ የነበረው ወለድ ከ16.5 በመቶ ወደ 15.5 በመቶ ዝቅ እንዲል መወሰኑን ተረድተናል።
በመንግስት በተሰሩት የጋራ መኖርያ ቤቶች ላይ ሲከፈል የነበረው የ12 በመቶ ወለድም ባለበት ይቀጥል ተብሏል።
መንግስታዊው የፖሊሲ ፋይናንስ ተቋም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግብርና ዘርፍ ላይ ለሚሰጠው እና ለሰጠው ብድር ከሚጠይቀው ወለድ ላይ ቅናሽን ቢያደርግም በሸቀጦች ንግድ እና ሌሎች ዘርፎች ላይ የጨመረው ወለድ ራሱን የቻለ የዋጋ ንረትን የመፍጠር አቅም እንደሚኖረው ከባለሙያዎች ያሰባሰብነው አስተያየት ያመለክታል።
ባንኩ የሚሰጠው ብድር መጠን ከሌሎች ንግድ ባንኮች አንጻር ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር የወለድ ጭማሪው ተጽእኖ በበርካታ ምርቶች ላይ መታየቱ አይቀርም ይላሉ ባለሙያዎች።
ባንኩ እስካሁን የሰጠው ብድር 1.35 ትሪሊየን ብር የደረሰ ሲሆን በዚህ በጀት አመት ስድስት ወራት ውስጥ ደግሞ 153 ቢሊየን ብር ብድርን ሰጥቷል። (ከታች ይቀጥላል)
ባለሙያዎች የሚያቀርቡት አስረጂ፣ የባንኩ የብድር አቅርቦት ሌሎች የግል ባንኮች አጠቃላይ ካበደሩት መጠን በእጅጉ ከፍ ያለ በመሆኑ በወለድ ተመኑ ላይ የሚያደርገው ጭማሬ ብድርን በማስወደድ ጥቅል ኢኮኖሚው ላይ የዋጋ ንረት ተጽእኖን ለማምጣት አቅም ይኖረዋል።
የግል ባንኮች አማካይ የብድር ወለድ ጣሪያ 18 በመቶ አካባቢ የነበረ ሲሆን ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ አብዛኞቹ የግል ባንኮች የወለድ ጭማሬ በማድረግ አማካይ ወለዳቸውን ወደ 22 በመቶ አድርሰውታል።
የኢትዮጵያ መንግስት የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ባንኮች ክፍት ካደረገና ከአለማቀፍ አበዳሪዎች ጋር ዘርፉን ገበያ መር ለማድረግ ከወሰነ ወዲህ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በተስፋና በስጋት መካከል እየዋለለ ይገኛል።
መንግስት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃ እየወሰደ መሆኑን ቢናገርም በርካቶች ግን በኣበዳሪዎች ጫና መንግስት መዳረሻው ወዳልታወቀ አስጊ የኢኮኖሚ አቅጣጫ እያመራ ነው ሲሉ ይተቹታል። [ዋዜማ]