- ቤተ ክርስቲያን መንግስትን ማብራሪያ ጠይቃለች
- መስቀል አደባባይ እየፈረሰ ነው ወይስ እየታደሰ? ባለሙያዎች ጥያቄ አላቸው
ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀትና የመስቀል ዳመራ የሚከበሩበት መስቀል አደባባይና ጃንሜዳ ላይ መንግስት ፈቃደኝቴን ሳይጠይቅ ሳያማክረኝ በወሰዳቸው እርምጃዎች “የባለቤትነት” መብቴን ተጋፍቷል ለዚህም ማብራሪያ እንዲሰጠኝ ስትል ጠየቀች።
ለዋዜማ ራዲዮ የደረሰው ከቤተ ክርስቲያኒቱ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት የተላከው ደብዳቤም ይህንኑ ይገልጻል።
በአቡነ ያሬድ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ እንደሚለው እነዚህ ከመንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶች በተጨማሪ ለሀገሪቱ ትልቅ የገቢ ምንጭ በመሆን የታወቁትን በአላት ማክበሪያ ቦታዎችን የበለጠ በመንከባከብና እሴቶቻቸውን በመጠበቅ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምርና የሀገሪቱ ገቢ አድጎ የህዝቡን ተጠቃሚነት በበለጠ ሁኔታ እንዲረጋገጥ ለቦታዎቹ ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ፈንታ ይባስ ብሎ የበአለ ጥምቀቱን ቦታ ለገበያ ማእከልነት እንዲሁም የበአለ መስቀል ማክበሪያውን ቦታ ደግሞ “ምንነቱ ላልታወቀ” ፕሮጀክት እንዲውል ሲያደርግ የበአሉም ሆነ የቦታው ጥንተ ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያኒቱ ሳትጠየቅና በጉዳዩ ላይ ሳታምንበት ግልፅነት በጎደለው ሁኔታ ወደ ትግበራ በመገባቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን በእጅጉ ያሳዘነ ተግባር ነው።
እንዲሁም በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታና ቁጣን በማስከተሉ የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈጠረብን ነውም ይላል ደብዳቤው። ደብዳቤው አክሎም የከንቲባ ጽህፈት ቤት የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት በማስገባትና ልዩ ትኩረት በመስጠት በጉዳዩ ላይ ተገቢውም አፋጣኝ ምላሽ ይስጠን ሲል ይጠይቃል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ያግዘኛል በሚል ፒያሳ ያለውን የአትክልት ተራ መጨናነቅ ለመቀነስ ገበያውን ወደ ጃንሜዳ መቀየሩ ይታወቃል። ከቀናት በፊት ደግሞ አዲስ አበባን የማስዋብ እቅድ አካል ነው የተባለ የመስቀል አደባባይ ማዘጋጃ ቤት ፕሮጀክትን ለመስራት የመስቀል አደባባይን መቆፈር ተጀምሯል።የዋዜማ ሪፖርተር ስፍራው ላይ ተገኝቶ እንደተመለከተው የቁፋሮው ስራ እጅጉን እየተፋጠነ ነው።
በቤተክርስቲያኒቱ ለጉዳዩ ከፍተኛ ቅርበት ያላቸው ግለሰብ ከዋዜማ ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ መንግስት በፈጸመው ድርጊት የቤተ ክርስቲያኒቷን ህጋዊ መብት ተጋፍቷል ብለውናል። የጃን ሜዳውን እና የመስቀል አደባባዩ ጉዳይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ስጋት መፍጠሩን ያነሳሉ። የጃን ሜዳውን የአትክልት ግብይት ቦታ መሆኑን በተመለከተ ፣ መንግስት ይህን ያደረገው የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ነው መባሉ በራሱ ችግር ባይሆንም ፣ እንደተባለው ጃን ሜዳ ለገበያ ቦታነት የተፈለገው በጊዜያዊነትና የወረርሽኙ ጊዜ እስኪያልፍ ለመሆኑ ምን ማረጋጫ አለ ? የሚል ጥያቄ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዘንድ አለ ይላሉ። አሁን ጊዜያዊ ተብሎ ቀጣይ የሚኖር አስተዳደር ቦታውን በቋነሚት ወደ ግብይት ቦታ ልቀይር አለማለቱ በምን ይታወቃል? ይህም በቀጣይ ግጭትና አላስፈላጊ ንትርክ ሊያስከትል ስለሚችል ከተማ አስተዳደሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሳያማክርና አስተያየቷን ሳይቀበል : ይሁንታንም ሳያገኝ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰበትን ህጋዊ መሰረት እንዲያስረዳም ነው ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገው ብለውናል ምንጫችን።
የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ቅሬታ እንደገባትም ጠቁመውናል። የመስቀል በአል በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ ሲሰፍር ያለው አረደዳድ የተመዘገበው በዓሉም ብቻ ሳይሆን የዳመራ ስነስርአቱና የሚከበርበት ቦታ እንደመሆኑ ታዲያ የአዲስ አባበ ከተማ አስተዳደር የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትን አስመልክቶ ይፋ ያደረገው በቪድዮ የተደገፈ ዲዛይን ለቤተ ክርስቲያኒቱ እንግዳ ነገር ሆኖባታልም ።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት ግለሰብ እንዳሉን በቪድዮ የተደገፈው ዲዛይን ደመራው የሚተከልበትን ቦታ እና የተለያዩ መንፈሳዊ ትርኢቶች የሚታዩባቸው ስፍራዎች ላይ ዛፍ ተተክሎበት ስለሚያሳይ የመስቀል ደመራ እንዴት እንዲከበር ታስቦ ዲዛይኑ እንደተሰራም ግራ አጋቢ በመሆኑ ለቤተ ክርሰቲያኗ ማብራሪያ አስፈጓታል።
በሌላ በኩል የግንባታ ስራውስ ለመስቀል ደመራ በአል ይደርሳል ወይ የሚለው ጉዳይም ምላሽ የሚፈልግ ነው። የቤተ ክርስቲያኗ የዚህ ስጋት መነሻ ከፊት የሚመጡት ወራት የክረምት ወራት በመሆናቸውና በነዚህ ጊዜያት ደግሞ ግንባታን ማከናወን ከባድ መሆኑ እየታወቀ እንዴት በዚህ ሰአት ተጀመረ የሚል ነው ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ፌቨን ተሾመ ቅዳሜ እለት ፕሮጀክቱን ይፋ ባደረጉበት ከሁለት ደቂቃ ባነሰ መግለጫ “መስቀል አደባባይ ከመስከረም ወር በፊት አሁን እየሰጠ ያለውን አገልግሎት መስጠት ይችላል” ሲሉ ደጋገመው ያነሱት ይሄው ጥያቄ ሊነሳ ይችላል በሚል ቅድመ ግምት ይመስላል። ፕሮጀክቱ ከአሁን ጀምሮ ስምንት ወራት የሚወስድ መሆኑንም ገልጸዋል።
በቤተ ክርስቲያኗ በኩል የተነሳው መሰረታዊ ጥያቄ ግን መስቀል አደባባዩ መቼም ቢጠናቀቅ ይፋ የሆነው ዲዛይን የመስቀል ደመራን ስፍራው ላይ ለማክበር ምቹ ስላልሆነ ምን ታስቦ ፕሮጀክቱ እየተሰራ እንደሆነም ጭምር ነው የተረነዳው።
ቤተ ክርስቲያኗ ባለፈው ሳምንት ለተላከው ደብዳቤም ቤተክርስቲያኗ ከከተማ አስተዳደሩ ምላሽ እየጠበቀች መሆኑንም ነው የሰማነው።
መስቀል አደባባይ እየፈረሰ ነው ወይስ እየታደሰ?
የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ድብቅነቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን ከሙሉ የኢትዮጵያ ህዝብም ነው። አንድ ወቅት “አብዮት አደባባይ” በሚል ስያሜ ሲጠራ የነበረው “መስቀል አደባባይ” ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ሲፈርስና ሲቆፈር ለባለሙያዎችም ሆነ ለማህበረሰቡ ግልፅ ያልሆነው ጥያቄ ከሀይማኖት አልፎ የሀገሪቱ ታሪክ አካል የሆነው ይህ አደባባይ ፈርሶ አዲስ አደባባይ ሊገነባበት ነው? ወይስ ያለውን አደባባይ የማደስ ስራ እየተከናወነ ነው? የሚለው ነው ።
ዋዜማ ባሰባሰበችው መረጃ ይህን ታሪካዊ አደባባይ ለማደስ የከተማው መስተዳድር ከአንዳንድ የትምህርት ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች ገለፃ አድርጓል።
“ውይይቱ የተደረገው ባለቀለት የስራ ዕቅድ ላይ እንጂ በጉዳዩ ላይ ሀሳብ እንድንሰጥ አልነበረም” ይላሉ ስማቸውን የሸሸጉ በአዲስ አባባ ዩንቨርሲቲ የስነ ሕንፃ መምህር። በከተማዋ የስነ ህንፃና ምህንድስና ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ሁለት የሙያ ማህበራት ስለ ግንባታው ምንም አይነት ነገር ቀድመው እንዳልሰሙ ምክክርም መደረጉን እንደማያውቁ ይሁንና ከመገናኛ ብዙሀን በመስቀል አደባባይ ግንባታ ሊደረግ መሆኑን መስማታቸውን አስረድተውናል።
ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር በጀት የተያዘለት የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ቅዳሜ ዕለት ይፋ የተደረገው የመስተዳድሩ ቃል አቀባይ ፌቨን ተሾመ በምስልና በድምፅ የተቀረፀ ሁለት ደቂቃ የማይሞላ መረጃ ለተመረጡ መገናኛ ብዙሀን ባሰራጩት መግለጫ ነው። በተመሳሳይ ሰዓት የከተማው ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ የፕሮጀክቱን ዲጂታል ንድፍ በማህበራዊ ገፃቻው ይፋ አድርገዋል። ስለምን ጉዳዩን ለመገናኛ ብዙሀን ጥያቄና ጉብኝት ክፍት እንዳልተደረገም ግልፅ አይደለም።
ባለፈው ሳምንት ግንባታውን የጀመረው ሲሲሲሲ(CCCC) የተባለ የቻይና ኩባንያ ሲሆን ስራውን ግልጽ ባልሆነ መንገድ እንዳገኘው ተረድተናል። ይህን ሀገራዊ ፋይዳ ያለው አደባባይ የዲዛይንም ሆነ የግንባታ ስራው ውስጥ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እንዲሳተፉ አልተደረገም።
አደባባዩ ከሀይማኖታዊ ጉዳይ ባሻገር ያልተቋጩ የታሪክ የባህልና የፖለቲካ ክርክሮች ያሉበት ነው ። እንዲህ አይነት ፕሮጀክት ሲጀመር ሁሉን አቀፍ ውይይትና መግባባት መኖር ነበረበት ይላሉ ባሉሙያዎቹ። የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን ከዋና ዋና ግንባታዎች የማግለል ዝንባሌ እያደገ ነው ያሉት ባለሙያዎቹ የመስቀል አደባባይ ግንባታ የጨረታ ሂደትን ያላለፈና ግልፅነት የጎደለው ነው።
የአዲስ አበባ መስተዳድር እንደሚለው ግንባታው አደባባዩን በማደስ አንድ ሺ አራት መቶ መኪና መያዝ የሚችል የምድር ውስጥ የመኪና ማቆሚያን ጨምሮ መፀዳጃ ቤት፣ የካፌና ሬስቱራንት አገልግሎቶች ይኖሩታል። ይህ አይነቱን ውድ ግንባታ ግን ሀገሪቱ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የኢኮኖሚ ፈተና በገጠማት ወቅት ቅድሚያ የሚሰጠው ፕሮጀክት ነው ወይ? በሚል ለመስተዳድሩ ላቀረብነው የፅሁፍ ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘንም።
የከተማው የፕላን ኮሚሽን ያሰናዳው የከተማ ማዕከላት ማስፋፊያ መርሀግብር ላይ ይህ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት አለመካተቱንና ምናልባትም በቅርብ ወራት በከተማው መስተዳድር ውሳኔ ብቻ እንዲተገበር የተደረገ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
የዲሞክራሲ መገለጫ የሆነው ይህ አደባባይ ኢ-ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲፈርስ መደረጉ አርቆ አስተዋይነት የጎደለው ነው ይላል ሌላው ወጣት የስነህንፃ ባለሙያ።
አሁን በመስቀል አደባባይ የቁፋሮና የማፍረስ ስራ ተጀምሮ ተመልክተናል። ፕሮጀክቱ እንደተባለው የቀድሞውን አደባባይ የማደስና ለተጠቃሚዎች ምቹ የማድረግ ነው? ወይስ አፍርሶ አዲስ አደባባይ መስራት ? አፍርሶ ለመስራት ከተማዋን ነዋሪና የሀገሪቱን ዜጎች ይሁንታ መጠየቅ የለበትም ወይ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]
You can write to Wazema —-wazemaradio@gmail.com