• የውጭ ምንዛሬ ጥቁር ገበያ ህጋዊ የሚሆንበት መንገድ ታስቧል
  • ሀገሪቱ ከአይ ኤም ኤም ለሶስት አመታት ሊሰጣት የተዘጋጀው ገንዘብ ከዚህ ቀደም ለሶስት አመት ከነበራት ኮታ የ700 መቶ በመቶ ብልጫ አለው።
PM Abiy Ahmed and IMF President Kristalina Georgieva- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በሶናሊ ጄን ቻንድራ የተመራው የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የልዑካን ቡድን አመታዊውን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተለምዶ ” article 4 consultation ” የሚባለውን ምክክር ከፈረንጆቹ ጥቅምት 29 እስከ ህዳር 8 በአዲስ አበባ ካደረገ በሁዋላ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት 2.9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ለቀጣይ ሶስት አመታት መንግስት ” የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ” ብሎ ለሰየመው መርሀ ግብር ለማቅረብ ቅድመ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጿል።የአለማቀፉ ገንዘብ ተቋም ቦርድ ጥር ወር ላይ ተሰባስቦም ብድርና ፈንዱን ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ከውሳኔ እንደሚደርስ ሰፊ ግምት እንዳለም ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።


የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምና የኢትዮጵያ መንግስት የደረሱት ስምምነት በኢትዮጵያ በብዙ መልኩ በኢኮኖሚው ላይ ብርቱ ተፅዕኖ የሚፈጥር ውሳኔ መሆኑ በባለሙያዎች እየተነገረ ነው።የገንዘብ ተቋሙ በስራ አስፈጻሚ ደረጃ ለሶስት አመታት ለኢትዮጵያ ለመስጠት የተስማማው 2.9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድርና ፈንድ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ድርሻ ነው ብሎ ያስቀምጥ ከነበረው ኮታ የሶስት አመታቱ ቢደመር እንኳ የአሁኑ የ700 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው የዋዜማ ምንጮች የገለጹልን።

በዚህም ምክንያት በእዳ ጫና ፣ በወጪ ንግድ ቀውስና በዋጋ ግሽበት መለኪያነት የማክሮ ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ በአይ ኤም ኤፍ የቅርብ ክትትል ውስጥ መግባቷ በግልጽ ይፋ የሆነበት መሆኑን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ለዋዜማ ራዲዮ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋምን መርተው ከወር በፊት ኢትዮጵያ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን ጋር የመከሩት ሶናሊ ቻንድራ ባወጡት መግለጫም በሶስት አመታት ውስጥ ለኢትዮጵያ ሚለቀቀው ብድርና ፈንድ ማእቀፍ የሚረዳው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አምስት ጉዳዮችን ይነካል ብለው የመጀመርያው የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ ማገዝና የውጭ ምንዛሬ ተመን አወጣጥና ገበያን ወደ አዲስ ስርአት ማሸጋገር የሚል ነው።


በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ተመን አወጣጥ ስርአቱንና የገበያ አሰራሩን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በሚተገበርባቸው ሶስት አመታት ውስጥ ለመቀየር መስማማቱን ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮች ሰምታለች።

በኢትዮጵያ የምንዛሬ ተመን በየእለቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በሚያወጣው ዋጋ ግብይት የሚፈጸምበት ሲሆን ፣ ብሄራዊ ባንክ ካወጣው ዋጋ ውጭና ከንግድ ባንኮች ውጭ የሚፈጸመው የውጭ ምንዛሬ ግብይት ወንጀል ነው። በቀጣይ ግን የምንዛሬ ዋጋ በገበያ እንዲተመንበጥቁር ገበያ የሚደረገው ግብይት ይፋዊ ሆኖ ፍቃድ አውጥተው ግብር በሚከፍሉ የምንዛሬ አገልግሎትን ብቻ ለመስጠት በሚከፈቱ ተቋማት ለመተካት መንግስት አስቧል ተብለናል።

ይህም የአሜሪካ ዶላርና መሰል ምንዛሬዎች በንግድ ባንኮችና በጥቁጥ ገበያ በሚሸጡበትና በሚገዙበት ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት ምክንያት ተንሰራፍቶ የቆየውን የምንዛሬ አቀርቦት ና ህገ ወጥነትን ይቀንሰዋል ተብሎ ታምኗል።የምንዛሬ ተመን በገበያ ሲወሰን በባንኮችን ከባንኮች ውጭ በሚፈጸም የምንዛሬ ዋጋ መካከል መቀራረብ ስለሚፈጠር ገበያው ጤናማ ይሆናል ተብሎ በመታመኑ ነው። የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትንም የተሻለ ያደርጋል ተብሏል። አሁን የውጭ ምንዛሬን በተለያየ መልክ የሚያገኙ ሰዎች አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በባንክ መመንዘር ምርጫቸው እንዳልሆነ ይታወቃል።


በሌላ በኩል በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እይታ የኢትዮጵያ ብር ከንግድ አጋሮች መገበያያ አንጻር ያለ አግባብ የጠነከረ በመሆኑ ምርትን ወደ ውጭ መላክን አላበረታታም። ምርት ላኪዎችም ምርቶቻቸውን በህጋዊ መንገድ ከመላክ ይልቅ ኮንትሮባንድን እንዲመርጡ ሲያደርጋቸውም ታይቷል። አንድ የአሜሪካን ዶላርን ላመጣ ምርት ላኪ ባንኮች አሁን ባለ ዋጋ 31 ብር ነው የሚያቀርቡት ፣ ለዚሁ አንድ ዶላር ግን ጥቁር ገበያው 40 ብር አካባቢ የሚያቀርብ መሆኑም የኢትዮጵያ ብር ትክክለኛ ዋጋውን ላለማግኘቱ ከአቅርቦት ችግር ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ማሳያ መሆኑ ይጠቀሳል።

የምንዛሬ ተመንን ለገበያ በተዉ ሀገራት በባንክና ከባንክ ውጭ በሚደረግ የምንዛሬ ገበያ እንደ ኢትዮጵያ አይነት የዋጋ ልዩነት ብዙም አይስተዋልም። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከህዳር ወር ጀምሮ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመንን በየእለቱ በፍጥነት ማዳከም መቀጠሉም የዚህ እቅድ አንዱ አካል መሆኑን ሰምተናል።


ሆኖም የምንዛሬ ተመን ለገበያ ተለቆ የኢትዮጵያ ብር አሁን ካለበት ይበልጥ ሲዳከም የገቢ እቃዎችን ውድነት ማስከተሉ ስለማይቀር ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት ፈተናን መደቀኑ ስለማይቀር መንግስት ይህን እንዴት እንደሚወጣው ከወዲሁ ሊያስብበት ይገባል ተብሏል።


ነገር ግን የእዳ ጫናው ፈቅ ባላለበትና ከወጪ ንግድ የሚገኘው ምንዛሬ አመርቂ ለውጥ ባላመጣባት ሀገር ላኪዎችን የሚያበታታ የምንዛሬ ገበያ መከተል አማራጭ የሌለው ነው።


ይህም ብቻ ሳይሆን መንግስት የሶስቱን አመታት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ ግብርን በሚተገብርበት ጊዜ ጠበቅ ያለ የበጀትና የገንዘብ ፖሊሲዎችን እንደሚከተል ከወዲሁ እየገለጸ በመሆኑ እንደከዚህ ቀደሙ በሚቀርጻቸው ሰፋፊ ፕሮጀክቶች የስራ እድልን የመፍጠር አዝማሚያ አይኖረውም።

ይህ የተማረም ሆነ ያልተማረ ሀይል በገፍ ስራ ፈላጊ እየሆነባት ለመጣች ኢትዮጵያ አደገኛ እየሆነ መምጣቱ ስለማይቀር የስራ ሀይሉን የሚረከብ የግል ዘርፍን በፍጥነት ማጠናከር ላይ ብዙ ይጠበቅበታል። የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም የተጋነነ የኢኮኖሚ እድገት ለመፍጠር ከሚያገኘው ገቢ ጋር የማይመጣጠን ወጭውን ለማካካስ ባለስፈላጊ ሁኔታ ብርን በሰፊው በማተም በግሽበት አምጭነት ሲታማ ቆይቷል። አሁን በተቻለ መጠን የብር ህትመትን ገታ በማድረግ ወጪውን በገቢ ለመሸፈን የታክስ ገቢውን ለማሳደግ የሚረዱትን ህጎችን እያወጣ ነው። የግብር አሰባሰቡ ላይ ተአምራዊ የሚባል ለውጥ ካልመጣ መንግስት የሚከተለው ወጭ ቅነሳ ብዙ ማህበራዊ ቀውሶችን ማስተከተሉ አይቀርም።


የባንኩ ዘርፍም ብዙ ለውጦች ይጠብቁታል
የሚተገበሩት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በጠንካራ ተቋማዊ አፈጻጸም ታግዘው ስራ አጥነትንና የዋጋ ግሽበትን መቀነስ ከተቻለ የሚደረጉ የማሻሻያ ትግበራዎች በትንሽ ጫና በብዙ ጥቅም ሊከናወኑ ይችላሉ ።ከዓለም አቀፍ ገንዘብ ተቋም የሚቀርቀው ገንዘብም የሚመጣውን ጫና ለማካካስ ይረዳል። አፈጻጸሙ መልካም ካልሆነ ግን ተቃራኒው ይከሰታል።ኢትዮያየ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ግን አሁን እየተገበረችው ካለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ የነገሩን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አሉ። [ዋዜማ ራዲዮ]

Any comment to the Editor wazemaradio@gmail.com