ዋዜማ- ኢትዮጵያ ካሏት ስምንት ስኳር ፋብሪካዎች በምርት ሥራ ላይ ያለው አንድ የስኳር ፋብሪካ ብቻ መሆኑን ዋዜማ ከየፋብሪካዎቹ ካሰባሰበቻቸው መረጃዎች መረዳት ችላለች። ከስምንቱ ስኳር ፋብሪካዎች መካከል በምርት ሥራ ላይ ያለው ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ብቻ መሆኑን ያስረዱት የዋዜማ ምንጮች፣ ቀሪዎቹ ሰባቱ ፋብሪካዎች ስኳር ማምረት ካቆሙ ሰነባብተዋል ብለውናል። ምርት ያቆሙት ሰባቱ ስኳር ፋብሪካዎች መተሐራ፣ ፊንጫ፣ አርጆ ዲዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ ቁጥር አንድ፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ እና ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት መሆናቸውን ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት ተረድታለች።
ዋዜማ በየፋብሪካዎቹ ያሉ ሠራተኞችን እና ለሥራው ቅርብ የሆኑ ሰዎችን ያነጋገረች ሲሆን፤ ለአብነትም የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ምንጮች፣ ፋብሪካው ለ 55 ዓመታት የዘለቀ ትልቅ ተቋም ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፈ ይገኛል ብለዋታል። ፋብሪካው አሁን ላይ “ስቲም ጄኔሬሽን ፕላንት” ወይም በተለምዶ አጠራር “ቦይለር” የሚባሉ ማሽኖቹን ለማንቀሳቀስ የሚረዳው መሳሪያ ጥገና ስላልተደረገለት ሥራ ለማቆም መገደዱን ተናግረዋል።
መተሐራ ትልቅ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፣ ከ10 ሺሕ 230 ሔክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ በማልማትም፣ በዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም የነበረው ነው። በተጨማሪም ፋብሪካው ከ2003 ዓ.ም. ባካሄደው የማስፋፊያ ፕሮጀክት፣ የስኳር ተረፈ ምርት የሆነውን ኤታኖል፣ በዓመት እስከ 12.5 ሚሊዮን ሊትር በሚደርስ መጠን ያመርት ነበር ። በሌላ በኩል፣ “ባጋስ” ተብሎ ከሚጠራው የሸንኮራ አገዳ ገለባ 9 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የራሱን የኃይል ፍላጎት እያሟላ የሚገኝ ፋብሪካ እንደነበርም ሠራተኞች ገልጸዋል።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት ራሳቸውን በቦርድ እንዲያስተዳድሩ ከተደረጉት አምስት ስኳር ፋብሪካዎች መካከል አንደኛው መተሐራ ስኳር ፋብሪካ መሆኑን የጠቀሱልን ምንጮቻችን ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ ለመጣው የምርት ሥራው ዋነኛው ምክንያት ከስኳር ኮርፖሬሽን ስር እንዲወጣ መደረጉ ነው ይላሉ። ፋብሪካው አስፈላጊው ጥገና ተደርጎለት ከአንድ ወር በኋላ ሥራ ይጀምራል የሚል ጭምጭምታ በፋብሪካው አሥተዳደር በኩል ቢኖርም፣ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የሚሆን አይመስልም ሲሉ ሰራተኞቹ ስጋታቸውን ለዋዜማ ነግረዋታል።
ምርት ካቆሙ ፋብሪካዎች መካከል ሌላኛው ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሲሆን፣ ፋብሪካው በተለያዩ ችግሮች ውስጥ እያለፈ መሆኑን የሚገልጹት ሠራተኞቹ፣ ለዓመታት በአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር ዋነኛው ፈተና መሆኑንም አስረድተዋል።
ፊንጫ በ2016 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ጥገና ይደረግለታል ተብሎ ከቆመ በኋላ እስከ አሁን ድረስ ምርት አለመጀመሩን የሚገልጹት ምንጮች፣ ይልቁንም ሠራተኞቹ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ ወዳሉ ሌሎች የግብርና ሥራዎች እንዲያዘነብሉ በፋብሪካው አሥተዳደር በኩል ጫና እየተደረገ መሆኑን ነግረውናል። ከሦስት ዐሥርታት በላይ ያስቆጠረው የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ፣ የግንባታ ሥራው ሲወጠን በዓመት እስከ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር እንዲያመርት ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ምርት እስካቆመበት ጊዜ ድረስ ግን በዓመት ያመርት የነበረው ከ 3 መቶ እስከ 4 መቶ ሺሕ ኩንታል ብቻ ነበር ።
በሌላ በኩል ፋብሪካው ከፍተኛ የሆነ የመለዋወጫ ዕቃ ችግሮች አሉበት የሚሉት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የፋብሪካው ሠራተኞች፣ በቂ የሆኑ መለዋወጫዎች ከገቡለት ከሰባት ዓመታት በላይ መቆጠራቸውን አስረድተዋል። ፋብሪካው ከዚህ ቀደም ያስፈልገው የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል በራሱ ያመነጭ እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች፣ የኃይል ማመንጫው መበላሸቱንና ጥገና ሳይደረግለት መቅረቱን ተከትሎ ኃይል ማመንጨት ካቆመ ስድስት ዓመታት አልፈውታል ። ፋብሪካው ካለው የሸንኮራ አገዳ ማልሚያ መሬት ላይ በአካባቢው ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እስካሁን ከ15 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት በእሳት መውደሙን ለዋዜማ ያስረዱት ምንጮች፣ ከቀናት በፊትም የፋብሪካው ንብረት የሆነ ሸንኮራ አገዳ በእሳት መውደሙን ያወሳሉ።
የአርጆ ዲዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ ቁጥር አንድ፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ እና ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ፋብሪካዎችም ተመሳሳይ የመለዋወጫ ዕቃዎች እና የፋይናንስ ችግር ያለባቸው ፋብሪካዎች መሆናቸውን ዋዜማ ካሰባሰበቻቸው መረጃዎች መረዳት ችላለች። የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካ የምርት ሥራ ያቆመው በ 2015 ዓ.ም. መሆኑን የሚያስረዱት የፋብሪካው ሠራተኞች፣ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት እና ዝርፊያ እንደደረሰበት አስረድተዋል።
አርጆ ዲዴሳ በቀጣዩ 2018ዓ.ም. ምርት ሊጀምር እንደሚችል የሚገልጹት ሠራተኞቹ፣ የፋብሪካው ሠራተኞች በግብርና እና ተጓዳኝ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል። ፋብሪካው በስኳር ምርት ሥራ ላይ በነበረበት ወቅት፣ ከዘጠኝ መቶ በላይ ቋሚ እና ከ ስድስት መቶ በላይ ጊዜያዊ ሠራተኞች ነበሩት ፣ አሁን ላይ 340 ግድም የሚሆኑ ሠራተኞች ብቻ እንዳሉት አስረድተዋል። በ2007 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው እና በቀን 8 ሺሕ ቶን የሸንኮራ አገዳ የመፍጨት አቅም ይኖረዋል ተብሎ የነበረው የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካ፣ አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ የስኳር ምርት ካቆመ ሦስት ዓመታት ተቆጠረዋል ሲሉ ምንጮች ይናገራሉ።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች በበኩላቸው፣ ፋብሪካው ከ2016 ዓ.ም. እስከ አሁን ድረስ ምርት አምርቶ አያውቅም ብለዋል። እኒሁ ምንጮች፣ በመንግሥት በኩል በዚህ ዓመት ምንም ዓይነት በጀት እንዳልተመደበለት የገለጹ ሲሆን፣ በጀቱ እስካልተመደበ ድረስ በዚህ ዓመትም ሥራ የመጀመሩ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ብለውናል።
በግንቦት 29/ 2013 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው እና በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ የሚገኘው የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ፣ ከዚህ ቀደም የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኝ የነበረበት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ በደረሰ ስርቆት ፋብሪካው አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደሌለውም እነዚሁ የዋዜማ የመረጃ ምንጮች አስረድተዋል።
ፋብሪካው ከ1 ሺሕ 400 በላይ ቋሚ እና ከ1 ሺሕ 600 በላይ ጊዜያዊ ሠራተኞች እንዳሉት የገለጹት የዋዜማ ምንጮች፣ የሠራተኞቹ ደምወዝ ከተቋረጠ ሦስት ወራት መቆጠሩንም ተናግረዋል። ፋብሪካው ከዚህ ቀደም በቻይና ዜጎች ተይዞ ሲሰራ መቆየቱ ሲታወስ፣ ከአንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያውያን እንዲተዳደር መደረጉንና በሚንስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሰረትም ራሱን በራሱ በቦርድ እንዲያስተዳድር መደረጉን ገልጸዋል።
የከሰምና ኦሞ ኩራዝ ፋብሪካዎችም በተመሳሳይ ችግር ምርት ካቆሙ ፋብሪካዎች መካከል ሲሆኑ፣ የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ከአንድ ወር በኋላ ምርት ይጀምራል መባሉንም ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።
ዋዜማ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕን ለማግኘት ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት ሊሳካ ባለመቻሉ ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም። [ዋዜማ]