ዋዜማ- እያንዳንዳቸው አንድ መቶ ሚሊየን ብር የወጣባቸው ስድስት የካንሰር የጨረር ህክምና መሳሪያዎች መካከል አራቱ ያለፉትን አምስት ዓመታት ያለ አገልግሎት መጋዘን ተቆልፎባቸው ይገኛሉ።
የካንሰር ሕሙማን የጨረር ሕክምና ለማግኘት ከአንድ ዓመት በላይ ወረፋ እንዲጠብቁ የሚገደዱ ሲሆን ብዙዎች በወቅቱ ህክምናውን ባለማግኘታቸው ሕይወታቸው ያልፋል። ዋዜማ እነዚህ ውድ መሳሪያዎች ለምን አገልግሎት ላይ መዋል አልቻሉም? ስትል የሚመለከታቸውን አካላት ጠይቃለች።
ከአምስት ዓመት በፊት ስድስት የጨረር ህክምና መሳሪያ /Linear Accelerator /LINAC / በጤና ሚኒስቴር እያንዳንዳቸው በወቅቱ ምንዛሪ ተመን 100 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎባቸው የተገዙ ሲሆን አገልግሎት ላይ የዋሉት ግን ሁለት መሳሪያዎች ብቻ ናቸው፡፡
ለጅማ ፣ሐሮማያ፣ጎንደር፣ሐዋሳ ፣መቀለ እና ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መሳሪያዎቹ ተሰጥተዋል፡፡ የጨረር ሕክምና መስጫ መሳሪያዎቹ የካንሰር ሕሙማን ሕክምና ለማግኘት እስከ አመት የሚደርሰውን ወረፋ ለማስቀረት ታስቦ የተገዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን የሕክምና መስጫ ማዕከል አስገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የሐሮማያ እና የጅማ ዩንቨርስቲ ሆስፒታሎች ብቻ ናቸው፡፡
የጨረር ህክምና መሳሪያዎቹ ግድግዳው እስከ ሁለት ሜትር ድረስ ውፍረት ባለው ግድግዳ በሚሰራ የተለየ ህንፃ የሚቀመጡ ሲሆኑ ይህን የተለየ ክፍል ለመስራት ደግሞ ለአንዱ መሳሪያ ማስቀመጫ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ የግንባታ ዋጋ እየናረ በመሄዱ ዩንቨርሲቲዎቹ ግንባታውን ለማከናወን እንደተቸገሩ የጤና ሚኒስቴር ለዋዜማ ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጨረር ሕክምና ሲሰጥበት የነበረው የሊናክ መሳሪያ በብልሽት ምክንያት ለወራት ስራ አቁሞ ታካሚዎች ወደ አማራጭ የህክምና ቦታዎች ለመሄድ እጅግ አሳዛኝ መከራን መጋፈጥ ግድ ሆኖባቸዋል።
አንዳንዶች ወደ ቤታቸው ተመልሰው የሕይወታቸውን ፍፃሜ ሲጠበበቁ ነበር። አሁን የህክምና መሳሪያው ተጠግኖ ወደ ስራ ተመልሷል።
መሳሪያው ተበላሽቶ በቆየባቸው አራት ወራት በሆስፒታሉ የጨረር ህክምና ይሰጣቸው የነበሩ በቀን ቁጥራቸው እስከ 150 የሚደርሱ ሕሙማን ሕክምናቸው ተቋርጧል፡፡
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ሕክምና ስፔሻሊስትና የክፍሉ ክሊኒካል ሰርቪስ ሃላፊ የሆኑት ዶክተር አዱኛ ፈቃደ አንድ ሕመምተኛ የሚጠበቅበትን አንድ የጨረር ሕክምና ሲያቋርጥ የመዳን እድሉ 14 በመቶ እንደሚቀንስበት ገልፀው፤ ይህ ሕክምና በተደጋጋሚ ሲቋረጥ ደግሞ ሕሙማኑ ከነበሩበት ደረጃ ወደ ከፋ እየተሸጋገሩ መዳን ወደ ማይችሉበት ደረጃ ይደርሳል ብለዋል፡፡
በአንድ ሆስፒታል የጨረር ሕክምና ለመስጠት የሚጠበቀው ደረጃ ቢያንስ ሁለት መሳሪያዎች ቢሆኑም እስከአሁን የሊናክ ማሽን በገባባቸውና ስራ በጀመሩና ባልጀመሩ ሆስፒታሎች ውስጥ በእያንዳንዱ አንድ ማሽን ብቻ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት አንዱ የሊናክ ማሽን ከተበላሸ የጨረር ሕክምና ስራ ሙሉ በሙሉ ይቆማል፡፡
ሰለሞን ንጉሴ የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር እንደገለፁልን አስመጭው ለአንድ አመት ማስተማማኛ ዋስትና የሰጠ ሲሆን ሌላ አምስት አመት ደግሞ የእቃው ባለቤት ክፍያውን እየሸፈነ አስመጭው እቃውን ያቀርባል፡፡
ተበላሽቶ የነበረው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጨረረ ህክምና ማሽን አንዱ የኤሌክትሪክ ቦርድ እስከ 20 ሚሊዮን ብር የጠየቀ ነው፡፡ ማሽኑ መልሶ እንዲሰራ ሁለት የኤሌክትሪክ ቦርዶች አስፈልገዋል።
ሊናክ የጨረር ህክምና መሳሪያዎችን ከውጭ ያስመጣው፣ የሚተክለውና የጥገና ስራ የሚያከናውነው ኤልስሜድ የተሰኘ ድርጅት ነው።
የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ውበቱ ወርቁ ከመሳሪያዎቹ ጋር ተያይዞ ሁለት መሰረታዊ ችግሮች መኖራቸውን ለዋዜማ ገልጠዋል፡፡ በየሆስፒታሎቹ የሚገኙት የጨረር ህክምና መስጫ መሳሪያዎች በተለይ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በቀን ከ100 በላይ ለሆኑ ሕሙማን ያለማቋረጥ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ በመሳሪያዎቹ ላይ ከፍተኛ ጫና ስለሚፈጠር አላቂ እቃዎቹ በአጭር ጊዜ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ፡፡
ከዚህ ሌላ ያለው ችግር ለመሳሪያዎቹ መቀያየሪያና መተኪያ እቃዎች ከውጭ የማስገባት ስራ ሲከናወን ደግሞ እንደማንኛውም እቃ አስቸጋሪውን የጉምሩክ የአሰራር መስመር ስለሚከተሉ ጊዜ ይወስዳል፡፡ በዚህ በኩል የጤና ሚኒስቴር ያለምንም መጓተት እንዲገባ ፈቃድ ቢያገኝና የሕሙማኑን ስቃይ መቀነስ ቢቻል መልካም ነው የሚል ሀሳብ አንስተዋል፡፡
በሃገራችን በአመት እስከ 70ሺ የካንሰር ክስተቶች ይታያሉ፡፡ ለህክምና ደግሞ አቅም ያላቸው ወደ ውጭ ይሄዱ የነበረ ሲሆን ይህን ችግር ለማቃላል በተለይ የጅማ ሆስፒታል ከመደበኛ ስራ ውጭ ጤና ሚንስቴር በፈቀደለት መሰረት ከመደበኛው ክፍያ ከፍ ባለ ሁኔታ ከየትኛውም አካባቢ ለሚሄዱ ህሙማን አገልግሎት እንደሚሰጥ የሆስፒታሉ የካንሰር ህክምና ባለሞያና የክፍሉ ሃላፊ ዶ/ር አማረ አሰፋ ገልፀዋል፡፡