Malik Ambar
Malik Ambar

በብዙ የዓለማችን አገሮች የዘር ግንዳቸውን ታሪክ ቆጥረው ከኢትዮጵያ ጋር ዝምድና እንዳላቸው የሚናገሩ ግለሰቦች ወይም የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖራቸው የተለመደ ክስተት ነው። ከአጎራባች አገራት ራቅ ብለን እንኳን ሔደን ይህ ክስተት ብዙ ጊዜ ያጋጥማል። ከሁሉ የሚያስገርመን በሩቅ ምስራቋ ሕንድ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን መገኘታቸው ብቻም ሳይኾን እስካሁንም ድረስ ሐበሻ ወይም አቢሲኒያን የሚባሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው ነው።

(መዝገቡ ሀይሉ በዚህ ዘገባው ማሊክ አምባርን ያስተዋውቃችኋል አድምጡት)


ለዚህ ምክንያት የኾነውን በጥንቱ ዘመን ኢትዮጵያውያን ከአገር ውጪ ያደርጉት የነበረውን የውዴታም የግዴታም ጉዞ የያዘ የታሪክ መዝገብ በኢትዮጵያ ባይኖርም የአንዳንዶቹ ግለሰቦች ታሪክ ግን የዓለምም የነበሩበትም አገር ታሪክ እንዳይዘነጋው የሚያደርግ ትልቅ ተጽእኖን በመፍጠራቸው ምክንያት ሲታወሱ ይኖራሉ።
የማሊክ አምባርም ታሪክ ከነዚህ አንዱ ነው። ማሊክ መገኛው ከኢትዮጵያ ቢኾንም በልጅነቱ በተለያት ኢትዮጵያ ስሙ አይነሳም። ኑሮውን በመሰረተባት በሕንድ ግን የማይረሳ ትልቅ የታሪክ ሰብእና ያለው ሰው ነው። ከተወለደባት ከኢትዮጵያ እስከሞተባት ቀን ድረስ ሲከተለው የኖረው ነገር ቢኖር ሐበሻ የሚለው መለያውና በልጅነቱ የተዳረገበት የባርነት ሕይወት ብቻ ነበር። ባርያ ኾኖ ሲሸጥ ሲለወጥ ቢኖርም ማሊክ ወይም ንጉስ ተብሎ ተጠርቶ እንደንጉስም ኖሮ ያለፈ አስገራሚ ሰው ነበር። የሕይወቱ ውጣ ውረድ በታሪክ ለመመዝገብ የሚያበቃ ገድል ስለነበረው ስለማሊክ ብዙ ስለተጻፈ እርሱ በነበረበት ዘመን የነበሩ የርሱን መሰል ታሪክ የነበራቸው በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ባሮች ታሪክ ለመነሳት ምክንያት ኾኗል።

እኤአ በ2005 በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የታተመው ከ14ኛው እስከ 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረውን የሕንድን ታሪክ የያዘው መጽሐፍ ከያዛቸው የዘመኑ 8 ዋነኛ ማኅበራዊ ታሪኮች መካከል ይህንኑ የኢትዮጵያውያኑን ባሮች ታሪክ የያዘው ክፍሉ አንዱ ኾኖ ቀርቧል። በዋነኝነት በወታደርነትና በአስተዳደር ያገለግሉ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ባሮች መካከል ማሊክ አምባር የተለየ ሥፍራ የተሰጠው ሰው ነበር።

በተለምዶ የግራኝ አሕመድ ጦርነት የሚባለውን የ16ኛውን መቶ ክፍለዘመን ጂሐድ የዘገበው ሲሐባዲን ወይም አረብ ፋቂ፤ ፉቱህ አል ሐበሻ ብሎ በሰየመው የውጊያው ታሪክ ላይ አጽንኦት ሰጥቶ ከሚዘግባቸው ነገሮች መካከል አንዱ በጦርነቱ የሚማረኩትና ሐይማኖታቸውን አልለውጥም ብለው አሻፈረኝ ያሉትን የተሸናፊውን ወገን ሕዝብ እጣ ፈንታ ነበር። በሞት ከመቀጣት በተጨማሪ ተሸናፊዎቹን በባርነት መሸጥ ለአሕመድ ገራድ ሰራዊት ትልቅ ትርፍ የሚያስገኝላቸው ገቢያቸውም ነበር። ሲሐበዲን ይህ የባሪያ ንግድ እስከ ሕንድ ድረስ ይደርስ እንደነበረም መስክርሯል።

ይህ የባሪያ ፍንገላ ታሪክ ግን በአሕመድ ገራድ ብቻ የተጀመረ አልነበረም። ከ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ብዙ ባሮች ከኢትዮጵያ እየተጋዙ ይሸጡ እንደነበረም ታሪክ አይረሳውም። በእስልምና እምነት ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውም የመጀመሪያው ሙዋዚን ቢላልም እንዲሁ በባርነት የተሸጠ ኢትዮጵያዊ ነበረ።

ማሊክ አምባር የተወለደው አሕመድ ገራድ ከሞቱ ከ 5 ዓመት በኋላ ነበር። የትውልድ ስፍራውም በሐረር አካባቢ እንደነበረና የመጀመሪያ መጠሪያ ስሙም ካፑ ይባል እንደነበረም በታሪኩ ተነግሮለታል። በምን ኹኔታ ለባርነት እንደበቃ ርግጠኛ ታሪክ ባይኖርም ከሐረር እስከ የመን፣ ከዚያም እስከ ኢራቅና ሕንድ በባርነት ያደረገው ጉዞው በታሪክ ተቀምጦለታል። በኢራቅ እስልምናን እንደተቀበለና በነበረውም ልበ ብሩህነት የተነሳ ብዙ ትምህርት እንደተማረም ታሪኩ ይናገራል። እስከ እለተ ሞቱም ድረስ በሕንድ የነበረው ታላቅ ገድል የሕይወቱ ትልቅ ምዕራፍ ነበር።

በሕንድ አገር በባርነት የገዛው ቼንጊዝ ካሕን የተባለ እና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ላይ የነበረ ሰው ነበር። አስገራሚው ነገር ይህም ማሊክን የገዛው የሕንድ ባለስልጣን በባርነት መጥቶ ነፃነትን ያገኘ ሌላ ኢትዮጵያዊ መኾኑ ነበር። አሁን ላይ ኾነው ሲያስቡት ይህ የሚያስገርም ቢኾንም በዘመኑ ኢትዮጵያውያን ባሮች በሕንድ የነበራቸውን ስፍራ ለሚያጠኑት ግን ይህ የተለመደ ክስተት እንደነበረ ይነገራል። በሺህ የሚቆጠሩ ባሮች በዓመት ከኢትዮጵያ የሚጋዙበትም ምክንያት ግልጽ ነበር። በሕንድም ይኹን በሌላው የዓለም ክፍል ኢትዮጵያውያኑ ባሮች የነበራቸው ስፍራ በውድ እንዲሸጡና በተለይም የነበራቸው የጦርነት ብቃት ተመራጭ እንዲኾኑ ያደርጋቸው እንደነበረም ጉዳዩን ያጠኑት የታሪክ ባለሞያዎች ይናገራሉ። ማሊክ አምባር ደግሞ በዚህ ጉዳይ ስሙ የተጠራ ገናና የጦር መሪ ነበር።

በሕንድ ድርሳናት እንደሚነገርለትም ይህ ሰው የ17 ዓመት ወጣት እያለ የገባበት የውትድርና ሕይወት አሕመድ ናጋር ይባል የነበረውን ግዛት ሙግሐል ተብሎ በሚጠራው መንግስት የተቃጣበትን ወረራ በመመከት ከጥፋት አድኗል። ይህም ለዚህ ወጣት ተዋጊ ሕይወት አዲስ ፈር ቀዳጅ አጋጣሚ ነበረ። ከዚህም በኋላ የፈጸመው ጀብዱ እንዲሁም አስተዋይነቱ የሚነገርበት መንገድ በሕንድ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ሚና መጫወቱን የሚያጎላ ነበር።

ከቼንጊዝ ካሕን ሞት በኋላ በባርነት ያገለገለው ቢጃፑር በምትባለው ግዛት የነበረውን ንጉስ ነበረ። ንጉሱም የጦሩ አለቃ አድርጎ ማሊክን ከመሰየሙም በላይ ማሊክ ወይም ንጉስ የሚለውንም የአድናቆት ስም የሰጠው እርሱ እንደነበረ ይነገራል። ከንጉሱ ሰራዊት ተነጥሎም እንደነፃ ሰው የራሱን ሰራዊት አቋቋመ። በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ብቻ የያዘ የቅጥረኛ ወታደሮች ጦር አደራጅቶም አገልግሎቱን ለሚፈልጉ የወቅቱ ገዢዎች በቅጥረኝነት ሲያገለግል ቆይቷል።

በምን ኹኔታ በስልጣኑ ላይ እንደተቀመጠ ታሪኩ ግልጽ ባይኾንምከጊዜ በኋላም አሕመድ ናጋር በምትባለዋ ግዛት ላይ በገዢነት ወንበርም ላይ ተቀምጧል። አንዳንዶች በግዛቲቱ ላይ ንጉስ ባለመኖሩ የነበረውን የስልጣን ክፍተት ለመሙላት ስፍራውን ይዞታል ይላሉ። የአሕመድ ናጋርን ንጉስ በማሰር አስገድዶ ስፍራውንም እንደያዘው የሚያምኑ የታሪክ ባለሞያዎችም አሉ። የማያሻማው ታሪኩ ግን ማሊክ ሴት ልጁን ከንጉሳዊ ቤተሰብ አባል ጋር በማጋባት እርሱ ስልጣኑን በዋነኛ ሹምነት ማስተዳደር መቀጠሉ ነው።
በስልጣን ዘመኑም ክሃድኪ የተባለ አዲስ ዋና ከተማ ከመቆርቆርም ባሻገር በሰፊው ዘርግቶት የነበረው የሥነሕንጻና የውኃ ፕሮጀክት ልዩ የሚያደርጉት ስራዎቹ ነበሩ። በ1626 ዓም በ80 ዓመቱ ሲሞት ለጥቂት ጊዜም ቢኾን የተካው ፋቴህ ካህን የተባለው ልጁ ነበር።