ዋዜማ ራዲዮ- ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ የኦሮሚያ ተወላጆች የሚሆኑ ሰፋፊ ሄክታሮችን ከየትም ብለው በተቻለው ፍጥነት እንዲያዘጋጁ ለአዲስ አበባ የአስሩም ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊዎች ታዘዙ፡፡ ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለአስሩም ክፍለ ከተሞች በተበተነ ደብዳቤ ነው ይህ ትዕዛዝ የተላለፈው፡፡ ሰፋፊ መሬቶቹ የሚዘጋጁት ከወራት በፊት ከሶማሌ ክልል የድንበርና የብሔር ግጭትን ተከትሎ የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሚያ ተወላጆችን በቋሚነት ለማስፈር ነው ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች እንዲሰፍሩ የሚደረጉት ተፈናቃዮች ትክክለኛ ቁጥር በውል ባይታወቅም ወደ ሶማሌ ክልል ከመሄዳቸው በፊት በአዲስ አበባ ኗሪ እንደነበሩ መረጃ ማቅረብ የቻሉ ተወላጆች ብቻ የፊንፊኔ ቋሚ ነዋሪ እንዲሆኑ እንደሚደረግ በመሬት ዝግጅቱ ተሳታፊ የሆኑ አንድ የድርጅት አባል ትናንት ማምሻውን ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ ለነዚህ ተፈናቃዮች መጠለያ የሚውል ቦታ እንዲያቀርቡ ከሚጠበቅባቸው ክፍለ ከተሞች መሐል አቃቂ ቃሊቲ፣ ኮልፌ ቀራንዮና የቦሌ ክፍለ ከተሞች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ክፍለ ከተሞቹ እያንዳንዳቸው ከ15 ሄክታር ያላነሰ መሬት እንዲያፈላልጉ ነው የተነገራቸው፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኮልፌ ቀራንዮ አሸዋ ሜዳ አቅራቢያ በሚገኙ ሰፈሮች ለተፈናቃዮች ቦታ ለማዘጋጀት በተደረገ እንቅስቃሴ ከአካባቢው ቀደምት ነዋሪዎች ጋር መጠነኛ ግጭት ተፈጥሮ የሰው ሕይወት መጥፋቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ቀድሞ ከገበሬ ቦታ ገዝተው ይዞታቸውን ወደ ሕጋዊነት ለማስቀየር ሲጠባበቁ የነበሩ እነዚህ ዜጎች ይዞታቸው ለተፈናቃዮች እንዲውል መታሰቡ ጭራሽ ያልጠበቁት ዱብዕዳ ኾኖባቸዋል፡፡ ይህን እንቅስቃሴ ለመግታት ያደረጉት ጥረትም የጸጥታ ኃይሎችን ያሳተፈ ግጭት እንዲያስተናግድ አድርጎ ነበር፡፡
1400 ኪሎ ሜትሮችን የሚጋሩት የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላቸው ክልሎች ሲሆኑ የድንበር ቀበሌዎቻቸውን አከላለል በተመለከተ በጥቅምት 1997 ሕዝበ ውሳኔ አድርገው ነበር፡፡ ኾኖም ሕዝበ ውሳኔው ለአስር ዓመታት ወደ መሬት ሳይወርድ ቆይቷል፡፡
በ27 ዓመታት የኢህአዴግ አመራር ታሪክ እጅግ በርካታ ሕዝቦችን ለሞትና መፈናቀል የዳረገው ይህ ውዝግብ በትንሹ ግማሽ ሚሊዮን ዜጎችን ከቀያቸው አሸሽቷቸዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ በአጎራባች ከተሞች፣ በመስጊድና አብያተ ክርስቲያን፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በጦር ካምፖች፣ በስቴዲየሞች፣ በግል ኮሌጆችና በግለሰብ ቤቶች ጭምር ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ የኦሮሚያ ክልል ባለሀብት የሆኑት አቶ ድንቁ ደያስ የተወሰኑ ተፈናቃዮችን በባለቤትነት በሚያስተዳድሩት የሪፍት ቫሊ ኮሌጅ ቅጥር ውስጥ በማቆየትና ከኪሳቸው 12 ሚሊዮን ብር በመለገስ አጋርነታቸውን አሳይተው ነበር፡፡ በርካታ ተፈናቃዮች ዛሬም ድረስ የተጠለሉት በላሜራ በተሠሩ ትልልቅ መጋዘኖች መሆኑ ቀን ቀን ለከፍተኛ ሙቀት፣ ምሽት ለከፍተኛ ቅዝቃዜ ተጋልጠው አስቸጋሪ ሕይወት እየገፉ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡
የተፈናቃዮች ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር አበራ ደሬሳ ከሁለት ወራት በፊት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ‹‹የተፈናቃዮች የኋላ ታሪክና የወደፊት ፍላጎታቸው እየተጠና›› በተለያዩ ቦታዎች እንዲሰፈርሩ ጠቁመው ነበር፡፡ ምናልባት በርካታ ነዋሪዎችን አዲስ አበባ በቋሚነት የማስፈሩ ሐሳብ እየተተገበረ ያለው ይህን ጥናት ተከትሎ በተደረሰ ዉሳኔ ሳይሆን እንዳልቀረ የሚገምቱ አሉ፡፡ ዶክተሩ በወቅቱ ለዚሁ አለም አቀፍ የዜና አውታር በሰጡት ማብራሪያ ‹‹በንግድና ከተሞች አካባቢ የሚሰሩ ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳደሩ ሰዎችን በፊንፊኔ ዙርያ በሚገኙ ልዩ ዞኖች ለማስፈር ዝግጅት ተጠናቋል›› ብለው ነበር፡፡ ኾኖም አስተባባሪው በአዲስ አበባ ዙርያ እንጂ በአዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሚያ ተፈናቃዮችን በቋሚነት ስለማስፈር በወቅቱ ያሉት ነገር አልነበረም፡፡ በተመሳሳይ ኑሯቸውን ግብርና ላይ ያደረጉ ተፈናቃዮችም ወደተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ለመደልደል የእርሻ መሬት እየተለየ ቆይቷል፡፡
በአዲስ አበባ ዙርያ ባሉ ልዩ ዞኖችና በአዲስ አበባ የሚሰፍሩት ከሶማሊ ክልል የተፈናቀሉት ብቻ እንደሚሆኑ፣ ነገር ግን ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ በሂደት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግም ታውቋል፡፡
ይህ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስን ያስከተለን የድንበርና የብሔር ግጭት ተከትሎ ከፍተኛና ተከታታይ የገቢ ማሰባሰቢያ ጥረቶች መደረጋቸው የሚታወስ ሲሆን የኦሮሚያ ተወላጅ ባለሐብቶችን፣ ሙዚቀኞችንና ስመ ጥር አትሌቶችን ጨምሮ በተደረገ ርብርብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሎ ነበር፡፡ ኾኖም ከችግሩ ስፋት አንጻር ገቢው ችግሩን ለመቅረፍ ቀርቶ ለማቃለል እንኳ የሚተርፍ አልሆነም፡፡
የድንበር ቀውሱን ተከትሎ በተሠራ አንድ ጥናት ከኦሮሚያ ተፈናቃዮች 97 በመቶ የሚሆኑት ከደኅንነት ሥጋት ጋር በተያያዘ ወደ ሶማሌ ክልል ለመመለስ ፈጽሞ ፍላጎት እንደሌላቸው ታውቋል፡፡ ያም ሆኖ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ግጭቱን ተከትሎ ሁሉም የኦሮሚያ ተፈናቃዮቹ ወደ ክልላቸው ሶማሌ እንዲመለሱ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
በመኢሶ፣ በቦርደዴ፣ በአርሲ፣ በሞያሌ ቦረና፣ በምሥራቅ ሐረርጌ ኦሮሞዎችና አጎራባች የሶማሌ ተወላጆች፣ ከተፈጥሮ ሀብትና የግጦሽ መሬት ይገባኛል ጥያቄ ጋር ተያይዞ ግጭትን ሲያስተናግዱ የቆዩ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ግጭቶቹ ፖለቲካዊ መልክ እየያዙ በመምጣታቸው ሰፊ ሰብአዊ ጥፋት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡