ዋዜማ- ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ብርቱ ደጋፊም ተቺም ያተረፉት እንድርያስ እሸቴ ነሐሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል። በምሁራዊ ብስለታቸው አንቱታን ያተረፉት እንድርያስ ዛሬ ሀገሪቱ ለተጋፈጠችው ችግር በአዋላጅነትም በጠንሳሽነትም “እጃቸው አለበት” የሚሉ ባላንጣዎችም አላጡም። እንድርያስ ከትችትና ፖለቲካዊ አተካሮ በዘለለ “ከስንት አንድ የሚመጡ ጥንቅቅ ያሉ ምሁርነታቸው” ግን አያከራክርም። ዋዜማ እንዲህ ታስታውሳቸዋለች

ስመጥር በሆኑ አለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ጽሁፎቻቸው የታተሙላቸው ፕሮፌሰር አንድርያስ፤ በፖለቲካል ኮሜንተሪ ዘውግ (Genre) ያሳተሟቸው ጽሁፎች ቢሰበሰቡ እስከ ሶሰት መጽሀፍ ሊወጣው ይችላል በማለት የቅርብ ወዳጆቻው ይናገራሉ፡፡ በፍልስፍናው ዘርፍ በርካታ ጽሁፎችን ያረከቱት እንድርያስ በህይወት ከሰነበትኩ አንድ ደህና መጽሀፍ የመጻፍ ሃሳብ አለኝ ይሉ ነበር፡፡ መፃፉ የሰመረላቸው አይመስልም፣ቢያንስ በህይወት እያሉ።

ፕሮፌሰሩ ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅር እና ቁጭት ሲገልጹ አገራችን ጽሁፍ ከተጀመረባቸው ጥቂት አገራት አንዷ ብትሆንም፤ ነገር ግን ስነ-ጽሁፍ የዕድሜውን ያክል አለማደጉን በመግለጽ ሌሎች የአፍሪካ አገራትን ያክል እንኳ እድገት አለማሳየቱን ያስረዳሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ እንኳን አምስት የሚያክሉ የስነ-ጽሁፍ የኖቤል ተሸላሚዎችን ስታፈራ ረጅም የጽሁፍ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ግን ይህ ነው የሚባል እውቅና እንደሌላት ያስረዳሉ፡፡ 

ፕሮፌሰር አንድርያ እሸቴ የካቲት 23 ቀን 1937 አባታቸው አቶ እሸቴ ተሰማ እና ወ/ሮ መንበረ ገብረ ማርያም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ፡፡ እስከ ሶስት አመታቸው ወላጆቻቸው ጋር ኖረው ከ3 አመታቸው ጀምሮ ደግሞ አጎታቸው አቶ ጀማነህ አላብሰው ጋር አድገዋል፡፡

አንድርያስ ገና በልጅነታቸው ጥልቅ የንባብ ፍቅር ነበራቸው፡፡ አጎታቸው አቶ ጀማነህ የቤተ መጻህፍት ባለሙያ  ስለነበሩ በንባብ ታንጸው እዲያድጉ አመቺ ሁኔታ የፈጠረላቸው ሲሆን በተጨማሪም ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ የሪቻርድ ፓንክረስት ቤተሰብ ጥብቅ ወዳጅ መሆናቸው ለቀጣዩ ዘመን ምሁራዊ ህይወታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ከአንደኛ እስከ 12 ኛ ክፍል  በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የተማሩት አንድርያስ ገና በልጅነታቸው ባመጡት የላቀ የትምህርት ውጤት ከቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ እጅ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ ብሩህ አዕምሮ እና ልዩ የንባብ ፍቅር የነበራቸው ስለነበሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በ16 አመታቸው ሲያጠናቅቁ ባገኙት ነጻ የትምህርት እድል ወደ አሜሪካን አገር በመሄድ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተከታትለው በዊሊያምስ ኮሌጅ በፍልስፍና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1958 ዓ.ም በማዕረግ ሲያጠናቅቁ ከፕሬዘዳነት አይዘንሃወር እጅ ዲግሪያቸውን በመቀበል ተመርቀዋል፡፡ ቀጥሎም ለድህረ ምረቃ ፕሮግራም ወደ የል ዩኒቨርሲቲ የሄዱ ሲሆን በየል ቆይታቸው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር በሰሜን አሜሪካ ሲመሰረት በማህበሩ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥም ተሳትፎ እንደነበራቸው የሚታወቅ ሲሆን “እሰካሁን አገሪቱን የሚመራው የፖለቲካ አጀንዳ የተቀየሰው በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት ነበረ” የሚሉት ፕሮፌሰር አንድሪያስ የተማሪዎች እና የምሁራንን እንቅስቃሴ ሲገልጹ “አገሪቱን ከጠቀምነው ይልቅ የበደልነው ነገር ከፍተኛ ይመስለኛል በፖለቲካ እልቂቶች አገሪቱ የተማረውን ዜጋዋን በማጣቷ እስካሁን ድረስ ተጎድታለች” በማለት በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸው ነበር፡፡  

በ1950ዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በማስተማር ስራ ላይ ተሰማርተው የነበረ ሲሆን እንደገና ወደ አሜሪካ ተመልሰው በመሄድ ከፍተኛ ተቀባይት በነበራቸው የልሂቃን (Elite) በሚባሉ የትምህርት ተቋማት አስተምረዋል፡፡ ካስተማሩባቸው ተቋማት ውስጥም ዩሲኤልኤ UCLA (ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ፣ ሎስ አንጀለስ)፣  በርክሌ፣  ፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲ፣ ብራውን  ዩኒቨርሲቲዎች ይገኙበታል፡፡

ኢህአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር ወደ አገራቸው ተመልሰው በመምጣት በ1980ዎቹ በሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን እና በኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ውስጥ የሰሩ ሲሆን ፤ ከ1995 – 2003 ዓ.ም ድረስ ለስምንት አመታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው የካቲት 25 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ወደ ጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት በመዛወር በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካሪ ሆነው ተሹመው ሰርተዋል፡፡ [ዋዜማ]