ዋዜማ- ትምሕርት ሚንስቴር በመጪው 2017 ዓ.ም የትምሕርት ዘመን በመላው አገሪቱ ከ 11ኛ ክፍል ጀምሮ የቴክኒክና ሙያ ትምሕርት ሥልጠና መስጠት ሊጀምር መሆኑን ዋዜማ ከሚንስትር መስሪያ ቤቱ ካገኘችው ሰነድና መረጃ መረዳት ችላለች።

ሰነዱ ላይ እንደተብራራው ለተማሪዎቹ በስምንት የትምህርት ክፍል ስር ካሉ አስራ ሁለት የትምህርት አይነቶች አንዱን መርጠው እንዲማሩ እንደሚደረግ ይገልጻል።

ሆኖም የየአካባቢዉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሁኔታ፣ ትምህርት ቤቶች ያሉበት ቦታ፣ለሥልጠናዉ የሚያስፈልጉ ግብአት አቅርቦት ዉስንነት ሁሉንም የሙያ ዓይነቶች በሁሉም ትምህርት ቤቶች በአንድ ጊዜ ለመጀመር የማያስችል በመሆኑ፣ አጀማመሩን በተመለከተ አሰራር መዘርጋት እና በሂደት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ዋዜማ የደረሳት ሰነድ ላይ ተመላክቷል።

ትምህርቱን ለማስጀመር ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከክልል ክልል እንዲሁም ከትምህርት ቤት ትምህርት ቤት የሚለያይ በመሆኑ፣ እንደየአካባቢው ሁኔታ ሥልጠናው እንደሚሰጥም መመሪያው ያትታል። 

በመሆኑም በቀላሉ ሊሟሉ የሚችሉትን የትምህርት ዓይነቶችን ግብዓት በማሟላት በቀጣዩ ዓመት ትምህርቱ እንደሚጀመር ከሚንስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በመጀመሪያው ዙር የሚመረጡ የሙያ አይነቶች በትምህርት ቤቱ በቀላሉ ለመጀመር የመማሪያ ቁሳቁሶችን ማግኘት፣ ወይም ማሟላት የሚቻልበት እና መምህራንን በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበት እንደሚሆኑ፣በሁለተኛው ዙር የሚመረጡ የሙያ አይነቶች በትምህርት ቤቱ አንድ ዓመት የመማሪያ ቁሳቁሶችን እና መምህራንን ለማሟላት ጊዜ የሚጠይቁ ሲሆኑ፣በሶስተኛው ዙር በአንድ ትምህርት ቤት ለመማር ማስተማር የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችም ሆኑ መምህራን ለማሟላት ጊዜ እና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ እንደሆኑ በሰነዱ ተብራርቷል።

በእያንዳንዱ ዙር በትምህርት ቤት ደረጃ የሚመረጡ እና ለተማሪዎች ለምርጫ የሚቀርቡ የሙያ ዓይነቶች ብዛት እንደትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ፍላጎት፣ ብዛት፣ የመማሪያ ቁሳቁሶች እና መምህራንን የመሟላት ሁኔታን ሊለያይ እንደሚችልም ዋዜማ ከሰነዱ ተመልክታለች።

በ2017 የትምህርት ዘመን ትምህርት የሚጀመርባቸው 12 የሙያ ዓይነቶች እንጨት ስራ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የማህበረሰብ ጤና፣ ጋዜጠኝነት፣ ግብርናና የእንሰሳት እንክብካቤ፣ የሂሳብ መዝገብ አያያዝና ዳንስ እንደሚገኙበት በሰነዱ ተመልክቷል።

ትምህርት ቤቶች አርባውንም የትምህርት ዓይነቶች የግድ ከፍተው ያሰለጥናሉ ማለት እንዳልሆነና የሚከፈቱት የትምሕርት ዓይነቶች በተማሪዎቻቸው ፍላጎትና ዝንባሌ ላይ የተመሰረት እንደሚሆን መረጃው ይጠቁማል።

የትምህርት ሚንስቴር፣የሥራና ክህሎት ሚንስቴር፣የክልል ትምህርት ቢሮ፣የዞን እና የክፍለ ከተማ ትምህርት መምሪያዎች፣የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት እና ራሳቸው ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ መሳካት በየደረጃው ያለባቸውን ዝርዝር ኃላፊነትም ዋዜማ ከመመሪያ ተመልክታለች።

በተጨማሪም በየደረጃው ያሉ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆችና ተቋማት በልዩ ሁኔታ ድጋፍና ትብብር ሥልጠናውን መስጠት ለሚጀምሩ ትምህርት ቤቶች እንዲያደርጉ መመሪያ ያዛል።

መመሪያው እንደሚያትተው ትምህርት ሚንስቴር የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ባስጠናው የፍኖተ ካርታ ጥናት መሠረት፣ አጠቃላይ ሥርዓተ ትምህርቱ ሀገር በቀል እውቀት፣ የሙያና እና የግብረገብ ትምህርትን ያላካተተ መሆኑን አመላክቷል፡፡ 

በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎችን በአነስተኛ ደረጃ ለሥራ ብቁ ለማድረግ፣ እንዲሁም የተወሰኑትን ለከፍተኛ ትምህርት ለማብቃት ዓላማ የተቀረፀ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጨርሰው ወደ ሥራ ሲሰማሩ አይታይም ብሏል ሰነዱ፡፡ 

በዚህም ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን የሚጨርሱ ወጣቶች መሠረታዊ እውቀት የጨበጡ ነገር ግን ሥራ የማይፈጥሩ እና የተማሩ ሥራ አጦች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ሲል ያለፈውን የትምህርት ፖሊሲ ኮንኗል፡፡ ይህን ችግር በመሠረታዊነት ለመቅረፍና ሥራ ፈጣሪ ዜጐችን ለማፍራት እንዲቻል አዲሱን የትምህርትና ሥልጠና ፓሊሲ ማርቀቅ አስፈላጊ ሆኖ ተግኝቷል ተብሏል። [ዋዜማ]