- ከሕፃናት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ላለው ሥራ የውጪ ሀገር ዜጎች መቅጠር አይቻልም
ዋዜማ ራዲዮ- የውጪ ሀገር ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚንቀሳቀስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች (መንግስትታዊ ያልሆነ ድርጅት) ውስጥ ለመቀጠር መንግስት አዳዲስ መስፈርቶች ማዘጋጀቱን ዋዜማ የተመለከተችው ረቂቅ መመሪያ ያሳያል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ያረቀቀው “የውጭ ሀገር ዜጎች የሥራ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ” ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተላላፊ በሽታ ያለበትን ውጭ ዜጋ መቅጠር እንደማይችሉ በረቂቅ መመሪያው መካተቱን አንብበናል፡፡
መመሪያው ተላላፊ በሽታ ያለበትን የውጪ ዜጋ እንዴት ለመለየት እንዳሰበ ግን አላብራራም። ተላላፊ በሽታ ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ አልዘረዘረም።
የአአምሮ ህመም ያለበት የውጪ ሀገር ዜጋም በኢትዮጵያ በሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ውስጥ መቀጠር እንደማይችል ያስረዳል።
ረቂቁ አንድ የውጭ አገር ዜጋ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ለመቀጠር ብቁ የሚሆነው ሥራው በኢትዮጵያውያን ሊያከናውን የማይችል መሆኑ ከተረጋገጠ ብቻ መሆኑን፣ ለሚቀጠርበት የሥራ መደብ ብቁ የሚያደርገውን ሙያና ክህሎት ያለው እና ሥራውን ማከናወን የሚችል ኢትዮጵያዊ ካልተገኘ ብቻ መሆኑ በረቂቅ መመሪያው ተጠቅሷል፡፡
ባለሥልጣኑ ባረቀቀው መመሪያ ክልከላዎች ያስቀመጠ ሲሆን፣ ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ የሥራ ፈቃድ ሳይኖረው ወይም ከሥራ ፈቃድ ሰጪው መንግሥታዊ አካል የሥራ ፈቃድ ሳይገኝ በድርጅት ተቀጥሮ ማናቸውንም ሥራ መሥራት እንማይችል ተደንግጓል፡፡ በልዩ ሁኔታ በባለስልጣኑ ካልተፈቀደ በስተቀር፣ በሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ከሕፃናት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ባለው ሥራ የውጭ ሀገር ዜጋን ቀጥሮ ማሰራት መመሪያው አይፈቀድም፡፡
ኢትዮጵያ የፈረመችው ስምምነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በገለልተኝነቱ ላይ ጥያቄ የሚነሳበት የውጭ ሀገር ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ተቀጥሮ እንዲሰራ አይፈቀድለትም፡፡
የስራ ፈቃድ ሳይኖረው ሲሰራ የተገኘ የውጭ አገር ዜጋ ወይም ያለባለስልጣኑ እውቅና ከተፈቀደለት ስራ ውጭ፣ ሲሰራ የተገኘ የውጭ አገር ዜጋ የስራ ፈቃድ እንደሌለው ወይም ከተፈቀደለት ስራ ውጭ እየሰራ መሆኑ ከተረጋገጠ ኋላ የሚያቀርበው የስራ ፈቃድ ጥያቄ ተቀባይነት እንደማይኖረው መመሪያው ያብራራል፡፡
የስራ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲሰሩ የሚገኙ ወይም የስራ ፈቃድ እያላቸው ከተፈቀደላቸው ስራ ውጭ ተሰማርተው በሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች ላይ፣ ባለስልጣኑ የተፈጸመውን ጥፋት ካረጋገጠበት ቀን ጀምሮ ቀጥሮ በሚያሰራቸው ድርጅት ወይም ሌላ ማንኛውም የሲቪል ማበረሰብ ድርጅት ውስጥ ከ 2 አመት ላልበለጠ ጊዜ ተቀጥረው እንዳይሰሩ ክልከላ የማስቀመጥ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡
የሥራ ፈቃዱ አገልግሎቱ ያበቃ፣ የተሰረዘበት፣ የታገደበት የውጭ ሀገር ዜጋ ፈቃዱ ካልታደሰ፣ እገዳው ካልተነሳ ወይም የመሰረዝ ውሳኔው ካልተሻረ በሥራው መቀጠል አይችልም፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]